ከ1ሚ. በላይ ሠራተኞች በመላው ዓለም ያስተዳድራል…

ዋል - ማርት

 

Image result for ሳም ዋልተን

 

ከ1ሚ. በላይ ሠራተኞች በመላው ዓለም ያስተዳድራል…

- ሠራተኞችን መንከባከብ ደንበኞችን መንከባከብ ነው…

በአሜሪካ በየ100 ሜትር ርቀት ላይ የምታገኙት፤ በሌሎች የዓለማችን አገራትም በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት ግዙፍ የችርቻሮ መደብር ነው - “ዋል ማርት”፡፡ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን በእርካሽ ዋጋ ለደንበኞቹ የሚያቀርበው ሱፐር ማርኬት የተቋቋመው ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ገና ከአነሳሱ በእርካሽ ዋጋ ብዙ ሸቀጦችን መሸጥ የሚል ስትራቴጂ መከተል የጀመረው ዋል-ማርት፤ ዛሬም ድረስ በትርፋማነት እንዲቀጥል ያደረገው ይሄው አሰራሩ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ዋጋን ጣራ ማስነካት የሚወዱ የአገራችን ነጋዴዎች በአነስተኛ ዋጋ እየሸጡም በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላሮች የሚያተርፍ ኩባንያ መፍጠር እንደሚቻል ከዚህ የዓለማችን ግዙፍ ሱፐርማርኬት ብዙ ሊማሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

 

የዚህ መደብር መስራች ሳም ዋልተን ይባላል፡፡ ዋልተን ይሄን መደብር ሲከፍት ቤሳ ቤስቲን አልነበረውም፡፡ የባለቤቱ አባት ባበደሯቸው 20ሺ ዶላር መደብሩን ያቋቋመው ዋልተን፤ ዛሬ በህይወት ባይኖርም የቢሊዮን ዶላር ኩባንያ መፍጠር ችሏል፡፡ የዚህ መደብር ቅርንጫፎች በመላው ዓለም ከ40 በላይ አገራት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ዛሬም ዋል - ማርት ከየትኛውም መደብሮች ዝቅ ባለ ዋጋ ነው ሸቀጦቹን ለደንበኞቹ የሚያቀርበው፡፡

ወደ “ዋል ማርት” ዝርዝር ታሪክ ከማለፋችን በፊት ባለፈው ሳምንት አንድ ሆቴል ውስጥ ሠርግ ተጠርቼ የገጠመኝን ላውጋችሁ፡፡ የአገራችንን የቢዝነስ አሰራር ያሳያል ብዬ ስላሰብኩ፡፡ የሆቴሉን ስም መጥቀስ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፡፡ ምክንያቱም በአንዱ የአገራችን ሆቴል ውስጥ የሚታዩ ችግሮችንና እንከኖችን አብዛኛዎቹ ሆቴሎች የሚጋሯቸው እንደሆነ ይገመታልና፡፡ የተጋበዝኩበት ሠርግ ላይ እራት ከተበላ በኋላ ስልክ ለመደወል ከአዳራሹ ደጋግሜ ወጥቼ ነበር - አንድ ሦስቴ ያህል፡፡ ይሄን የተመለከተ የሆቴሉ ጥበቃ፤ ከደጋሾቹ አንዱ መስዬው ነው መሰለኝ ጠጋ አለና:-

“የኔ ወንድም” አለኝ፤ ቀና ብዬ አየሁት፡፡

“እናንተ ምግቡንም ጠጁንም ካልሰጣችሁን ማንም አይሰጠንም፡፡ እዚህ ቤት ሁሌ ሽሮ ነው” ሲል ተቀጥሮ እንጀራ የሚበላበትን ሆቴል አማልኝ፡፡ ከዚህ የጥበቃው ቅሬታ (ስሞታ) ተነስታችሁ የሆቴሉ ማኔጅመንት በሠራተኞች አያያዝ እንከን እንዳለበት ብትገምቱ ፈጽሞ አልተሳሳታችሁም፡፡ በአገራችን የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ተቀጥረው ከሚሰሩ ሰራተኞች አብዛኞቹ በተደጋጋሚ በማኔጅመንቱ ላይ ከሚሰነዝሩት ቅሬታ መካከል ደካማ የምግብ አቅርቦት (ዘወትር ሽሮ) ዋነኛው ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፤ ሰርቪስ ቻርጅ፣ የቋሚና የጊዜያዊ ቅጥር ሁኔታም ይጠቀሳሉ፡፡

ለዚህ ነው የሆቴሉን ጥበቃ ቅሬታ ከማኔጅመንቱ ድክመት ጋር ያገናኘሁት፡፡ በሆቴልም ይሁን በሌላው በየትኛውም የቢዝነስ ዘርፍ፣ እንኳን የሰራተኞች አያያዝ የደንበኞች አያያዝም ገና ገና ብዙ እንደሚቀረው ምስክሮቹ ራሳችን ነን፡፡ “ደንበኛ ንጉስ ነው”፣ “ደንበኛ ሁልጊዜም ትክክል ነው” ወዘተ የሚሉ መፈክሮች ከፕሮፖጋንዳነት ያለፈ ፋይዳ በእኛ አገር የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል በውጭ አገር ያሉት የቢዝነስ ድርጅቶች ደንበኛውና ሠራተኛው የቱን ያህል የተሳሰሩ እንደሆኑ በመረዳታቸው፣ የሠራተኛ አያያዛቸው ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ከጀመሩ ብዙ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡

ለምሳሌ ከ130ሺ በላይ ሠራተኞች በመላው ዓለም ባሉ ቅርንጫፎቹ የሚያስተዳድረው ማርዮት ሆቴል፤ “Employee First” (ቅድሚያ ለሠራተኛ እንደማለት) የሚል ፖሊሲ ይከተላል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት ጄ.ደብሊው. ማርዮት ጄ አር፤ በህይወት ሳለ “The spirit to Serve: Marriott’s way” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው፤ ሠራተኞች በደንብ ሲያዙ እነሱም ደንበኞችን በደስታ ተቀብለው ያስተናግዳሉ፡፡ ሠራተኞችን በደንብ መያዝ ሲባል የተሻለ ምግብ መመገብና ሙያዊ ሥልጠና መስጠት ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ትርፍ የማጋራት ፖሊሲን ሁሉ ያካትታል፡፡ የእኛ አገር ነጋዴዎች ይሄን እንዲያደርጉ ቢጠየቁ ድርጅታቸውን ዘግተው ከመጥፋት ወደኋላ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ ግን የሚገርማችሁ የአገራችን ነጋዴዎች እንደ ጉድ የሚፈሩት ለሰራተኞች ጥቅማጥቅሞች መስጠትም ሆነ ለደንበኞች ከሌላው ባነሰ እርካሽ ዋጋ አገልግሎትን ወይም ምርትን ማቅረብ፣ ለውጭዎቹ ኩባንያዎች የስኬታማነትና የትርፋማነት ምንጭ ሆናቸው እንጂ ለኪሳራ አልዳረጋቸውም፡፡

ምናልባት የአገራችን ነጋዴዎች ገና ያልተረዱት ወይም ለመረዳት ያልፈለጉት ቁም ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ ይኸውም ደንበኛቸው ካወጣው ገንዘብ ጋር የሚመጣጠን አገልግሎት ወይም ምርት ካላገኘ ፊቱን ወደ ሌላ ማዞሩን ነው፡፡ የፎርድ አውቶሞቢል ፈጣሪ አሜሪካዊው ሔነሪ ፎርድ፤ ስለአምራቾች ወይም አገልግሎት አቅራቢዎች ሲናገር፤ “የሰዎችን ኑሮ የሚያሻሽል ነገር ማቅረብ አለባቸው” ብሏል - “My Life and work” በተሰኘ መጽሐፉ፡፡ “ዓለም ከምር የሚፈልገውን አስብ፤ በተቻለ አቅም በአነስተኛ ወጪ አምርተው፤ ከዚያም በዝቅተኛ ዋጋ ሽጠው” ሲል የሚመክረው ፎርድ፤ እናም ትርፋማነትህ የተረጋገጠ ጉዳይ ይሆናል ይላል፡፡ ደግሞም በተግባር አሳይቷል - ለአሜሪካውያን ፎርድ አውቶሞቢሎችን በዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ፡፡

በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን እንኳንስ ለሸማቹ የምንሸጠውን ዕቃ በርካሽ ዋጋ የምናቀርብበትን መንገድ ልናስብ ቀርቶ ርካሽም ሆኖ ቢገኝ እንኳ በውድ ዋጋ ብንሸጠው እንመርጣለን፡፡ ትርፋማነት የሚመጣው ዋጋን በማስወደድ ብቻ ስለሚመስለን፡፡ ግን እውነቱ እንደዚያ አይደለም፡፡ ትርፋማነት የሚገኘው ለደንበኛ የተሻለ ነገር በማቅረብ ነው - በርካሽ ዋጋ፡፡ የዴል ኮምፒውተር መስራች የሆነው ቢሊዬነሩ ማይክል ዴል፤ ለሚሸጣቸው ኮምፒውተሮች የቤት ለቤት የጥገና አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ብትሰሙ ምን ትላላችሁ? ማይክል ዴል ዛሬ ቀጭን ጌታ ነው - በቢሊዮን ዶላሮች የሚያተርፍ ኩባንያ ያለው፡፡ አሁን ወደ ዋል-ማርት መደብር ልመልሳችሁ፡፡

የዓለማችንን ባለፀጐች የሃብት መጠንና ደረጃቸውን ጭምር በየዓመቱ በዝርዝር ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መጽሔት፤ በ1985 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የዋል ማርቱን መስራች ሳም ዋልተንን “በአሜሪካ እጅግ ባለፀጋው ሰው” የሚል ስያሜ ሰጥቶት የነበረ ሲሆን ከ20 ዓመት በኋላ ይሄው መጽሔት ከዋልተን ቤተሰብ ውስጥ አራቱን አባላት “የዓለማችን አሥሩ እጅግ ባለፀጐች” መካከል አስገብቷቸው ነበር፡፡

ዋል-ማርት በዓለም ላይ ከ6ሺ በላይ የገበያ ማዕከል በመክፈት በዓለማችን ግዙፉ የችርቻሮ ንግድ ኩባንያ ለመሆን የበቃው በአንድ የትውልድ ዘመን ውስጥ ሲሆን አነሳሱም ከምንም ነው፡፡ ዋልተን “Made in America” በሚለው መጽሐፉ፤ ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለውን የቢዝነስ ፍልስፍናና ስትራቴጂ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ አለፍ አለፍ እያልን እንየው፡፡

 

የቢዝነስ አጀማመር

ሳም ዋልተን በዓለም የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ነው ልጅነቱን ያሳለፈው፡፡ የልጅነት ፍላጐቱ የሽያጭ ባለሙያ መሆን ነበር፡፡ ተማሪ ሳለ ጋዜጣ እያዞረ ይሸጥ ነበር፡፡ የኮሌጅ ትምህርቱን ካጠናቀቀና የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎቱን ከፈፀመ በኋላ ግን J.C penney ከተባለው አሜሪካዊ ቸርቻሪ ጓደኛው ጋር የችርቻሮ ንግድ ሥራ ውስጥ ገባ፡፡

ከውትድርና መልስ ከተዋወቃትና ካገባት ሄለን ሮብሰን አባት ገንዘብ በመበደርም አርካንሳስ ውስጥ ቤን ፍራንክሊን የተባለውን መደብር በፍራንቻይዝ ከፍቶ ሥራ ጀመረ፡፡

መደብሩ ከፍተኛ የቤት ኪራይና ሃይለኛ ፉክክር የነበረበት ቢሆንም ዋልተን ሽያጩን ከማበራከትና ትርፉን ከማሳደግ አልቦዘነም፡፡ የቤት ኪራዩን የማደሻ ጊዜ ሲደርስ ግን ባለቤቱ ለማደስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ - ልጃቸው መደብሩን እንዲረከብ ስለፈለጉ፡፡ ይሄኔ ዋልተን በሸቀ፡፡

ዋልተንና ሚስቱ ተስፋ ቆርጠው ግን አልተቀመጡም፡፡ በሰሜን ምዕራብ አርካንሳስ ግዛት በምትገኘው ቤንቶንቪሎ የተባለች ትንሽዬ ከተማ ውስጥ ሌላ መደብር ከፈቱ፡፡ አዲሱ የዋልተን “ፋይቭ ኤንድ ዳይም” መደብር በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ራስን በራስ የማስተናገድና መውጭያው በር ላይ ክፍያ የመፈፀምን አሰራር አስተዋወቀ፡፡

ዋልተን፤ በትናንሽ ከተሞችና ከከተማ ወጣ ባሉ ስፍራዎች ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ከተቻለ ገና ያልተነካ ብዙ የገበያ ፍላጐት መኖሩን ተገንዝቦ ነበር፡፡ እውነትም አሜሪካውያን ለእርካሽ ዋጋ ሲሉ ብዙ ኪ.ሜ ለመጓዝ ፈቃደኞች ነበሩ፡፡

በድህረ ጦርነት ወቅት የነበረችው አሜሪካ በፍጥነት እየተለወጠች ነበር፡፡ ሰዎች መኖሪያቸውን ወደ ከተማ ዳርቻዎች እያደረጉ የመጡበት ወቅት ሲሆን ወደ ከተሞችም አዘውትረው ይመላለሱ ነበር፡፡ ሆኖም በከተሞች የችርቻሮ መደብሮች አሰራር ከቀድሞው ያልተለየ ነበር፡፡ የተወሰኑ ሸቀጦችን ብቻ የያዙ መደብሮች (ለምሳሌ ስጋ መሸጫ) ይበዙ ነበር፡፡ ዋልተን ይሄን የተለመደ አሰራር የሚገዳደር ነገር ነው ይዞ ብቅ ያለው፡፡

በእርካሽ ዋጋ ብዙ ዓይነት ሸቀጦችን ማቅረብ፤ እንዲሁም ረዥም የአገልግሎት ሰዓትና የደንበኞችን እርካታ የሚያረጋግጥ አሰራር ወደ ገበያው አመጣ፡፡

ግን ዋል - ማርት ለደንበኞቹ ሸቀጦችን በእርካሽ ዋጋ የሚያቀርበው በምን ተዓምር ነበር? ዋልተን በመፅሃፉ እንደጠቆመው፤ ሁልጊዜም ሸቀጦችን የሚገዛው በቀጥታ ከአምራቾች ነበር፡፡ ለደንበኞች የምትሸጡትን ሸቀጦች በከፍተኛ ዋጋ የምትገዙ ከሆነ ውጤታማ ቢዝነስ እየሰራችሁ አይደለም ይላል - ዋልተን፡፡

ዋልተን ከዘመኑ የአገሩ ነጋዴዎች ሌላም የሚልቅበት ነገር ነበረው፡፡ ጥቂት ሸቀጦች በከፍተኛ ዋጋ ከመሸጥ ይልቅ ብዙ ሸቀጦችን በአነስተኛ ዋጋ መሸጥ ትርፋማ ያደርጋል የሚለው የዋል-ማርት ስትራቴጂ በወቅቱ የሚታወቅ አልነበረም፡፡ የስኬቱ ዋነኛ ምክንያትም ይሄ እንደነበር ዋልተን ይናገራል፡፡

በ1960 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ሳም ዋልተንና ወንድሙ ቡድ ዋልተን የዘጠኝ መደብሮች ግዛት (“ኢምፓየር”) መፍጠር ቻሉ፡፡ በወቅቱ ከዚህ በኋላ ምን ያህል ትስፋፋላችሁ ለሚለው ጥያቄ የሳም ዋልተን መልስ “በጣም ትንሽ” የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም ጥቂት መደብሮች ከጨመሩ እያንዳንዱን መደብር በአካል እየዞሩ መቆጣጠርና መምራት ያዳግታቸው እንደነበር አውቆታል፡፡ ሆኖም ግን አንዲት ትንሽዬ አውሮፕላን በመግዛታቸው ችግሩ ሁሉ ተቃለለ፡፡ እንደውም እየዞሩ መደብራቸውን መጐብኘት ብቻ ሳይሆን አዳዲስ የመደብር ማስፋፊያ ሥፍራዎችንም ለማሰስ አስቻላቸው፡፡

ዋል-ማርት የተባለው የመጀመሪያው መደብር እስከ 1962 እ.ኤ.አ አልተከፈተም ነበር፡፡ ዋልተን ደግሞ ያኔ 44 ዓመቱ ሲሆን በዚሁ ዓመት ኤስ አስ ክሬግ ኮ. “kmart” የተባለ መደብር በዚያቹ ከተማ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ነበር፡፡ ዋል-ማርት ከተከፈተም በኋላ ቢሆን የገጠር ከተማ ጀማሪ መደብር ተደርጐ የሚታይ እንጂ ከዛ ባለፈ እንደ ቁምነገር የሚቆጠር አልነበረም፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ “kmart” 500 ቅርንጫፎች የነበሩት ሲሆን ዋልተን ከ70 ትንሽ በለጥ የሚሉ መደብሮች ብቻ ነበሩት፡፡ በ1976 “kmart” መደብሮቹን በእጥፍ አሳድጐ 1ሺ ሲደርሱለት፤ ዋል ማርት ግን 150 ብቻ ነበሩት፡፡ በዚያ ላይ የመጀመሪያዎቹ የዋል ማርት መደብሮች አስቀያሚና ዝርክርክ ነበሩ፡፡ ሆኖም ከሌሎቹ መደብሮች 20 በመቶ ቅናሽ የነበረው መሆኑ ብቻ ደንበኞች እንዲጐርፉለት በቂ ምክንያት ሆነው፡፡ እቺን ዕድል በመጠቀም ስርጭቱን ያሻሻለው ዋልተን፤ ኩባንያው በዓመት ከ30-70 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አደረገ፡፡ ከ“kmart” ጋር የነበረው ፉክክርም ተጋጋለ፡፡ በ1980 የዋል ማርት መደብሮች 276 የነበሩ ሲሆን በ1990 ግን ኩባንያው 1528 መደብሮችና የ1 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አስመዘገበ፡፡ ይሄኔ “kmart” እጅ ሰጠ፡፡

ሳም ዋልተን “Made in America” የተሰኘ መፅሃፉን በፃፈበት ዓመት፣ ዋል-ማርት 27 ሚ. ጥንድ ጂንሶችና 280 ሚ. ጥንድ ካልሲዎች የሸጠ ሲሆን ይሄ በወቅቱ በአሜሪካ የሚገኝ እያንዳንዱን ወንድ፣ ሴትና ህፃን ለማልበስ በቂ እንደነበር ተዘግቧል፡፡

ዋል ማርት ዛሬ

ዋል ማርት በተደጋጋሚ ከሚተችባቸው ጉዳዮች አንዱ በሩን ለሠራተኞች ማህበር ዝግ ማድረጉ ሲሆን ከሠራተኞቹ ውስጥ 1/3ኛ ያህሉ የትርፍ ሰዓት ሠራተኞች መሆናቸውም ሌላ የሚተችበት ሰበብ ነው፡፡ በንፅፅር ሲታይ ኩባንያው የሚለግሰው የችሮታ (charity) መጠንም አነስተኛ ነው የሚል ትችት ይነሰዘርበታል፡፡

ዋልተን ግን ይሄን ትችት አይቀበልም ነበር-የኩባንያውን ዓላማ በማስረዳት፡፡ የኩባንያው አብይ ዓላማ መደብሮቹ በተከፈቱበት አካባቢዎች ሁሉ የህብረተሰቡን ገንዘብ ካልተገባ ወጪ በማዳን የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ከፍተኛ የሠራተኞች ደሞዝም ሆነ የበዛ ችሮታ ደግሞ ይሄን ዓላማውን እንደማያሳካለት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ የዋልተን ኩባንያ በመላው ዓለም ላሉ መደብሮቹ የሚፈልጋቸውን ሸቀጦች ከአሜሪካ የሸቀጥ አቅራቢዎች ብቻ በመግዛት እነሱን የመጥቀም ፖሊሲ ይከተል ነበር፡፡ ይሄም በ100ሺዎች የሚሰላ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር የአሜሪካ አምራቾችን የበለጠ ተፎካካሪ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት ነበረው፡፡ የዋል-ማርት ድርጅታዊ አወቃቀር፤ ሃሳቦች ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል እንዲመነጩ የሚፈቅድ መሆኑን የሚያረጋግጥ አሰራርም ዘርግቷል - ዋልተን፡፡ ኩባንያው ይሄን ያህል ግዙፍ የሆነው ትናንሽ ሃሳቦችን በማስተናገድ እንደሆነም ይነገራል፡፡

የሳም ዋልተን የቢዝነስና የኑሮ ዘይቤ

የሌሎችን የቢዝነስ ሃሳብ በመገልበጥ (በመኮረጅ) ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግብረው (“አብዛኞቹ የሰራኋቸው ነገሮች ከሌሎች የገለበጥኳቸው ናቸው” ሲል ፅፏል - ዋልተን)

ፉክክር እንድትሻሻል ያስገድድሃል፤ ስለዚህ አትፍራው፡፡

ቴክኖሎጂን ተጠቀም፤ ግን ወጪን ለመቀነስና ደንበኛን ለማገልገል ይሁን፡፡

ወጪ የመቆጠቢያ መንገዶችን ከመፈለግ አትቦዝን፡፡ የዋል ማርት ሥራ አስፈፃሚ ቢሮዎች የተጣበቡና የተጨናነቁ ነበሩ፡፡ ሥራ አስፈፃሚዎቹ በጉዞ ላይ ሲሆኑ አንድ የሆቴል መኝታ ክፍል ውስጥ ለሁለት በማደር ይታወቃሉ -ወጪ ለመቀነስ፡፡

ትንሽ ስለመሰለህ ብቻ ገበያህን አትመልስ፡፡

ሠራተኞችህን በደንብ ያዝ (ዋል - ማርት ሠራተኞቹን “ተባባሪዎች” ይላቸዋል) ደስተኛ “ተባባሪዎች” ደንበኞችን በቅጡ ያስተናግዳሉ፤ ደንበኞችም ተመልሰው ይመጣሉ፡፡ (የዋል - ማርት ትርፍ የማጋራት ፕሮግራም የብዙ ሠራተኞችን የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደረገው ሲሆን የንብረት መጥፋት ወይም የሰራተኞች ስርቆት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚታየው በግማሽ ይቀንሳል)

በነገሮች ፈፅሞ አትርካ፡፡ “በዚህ ዓለም ላይ ስኬታማ ለመሆን ሁልጊዜ መለወጥ አለብህ”

በህይወት ውስጥ ያንተ ሥራ ምንም እሴት ባልነበረበት ቦታ እሴት መፍጠር ነው፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ከፈለክ ዓለምን በሆነ መንገድ አበልፅግ፡፡

መሳሳትን አትፍራ፤ ሃሳብህን ለመለወጥም እንዲሁ፡፡ ዋልተን በትላልቅ ውሳኔዎች ላይ ወደፊት ወደኋላ በማለት ሌሎች ሥራ አስኪያጆችን ያበሳጭ ነበር፡፡

ሰዎች አንተን ከማናገራቸው በፊት አንተ አነጋግራቸው፡፡ ቀድመህ ሰላምታ ስጣቸው፡፡

ግቦች ይኑሩህ፤ ከፍ አድርገህም ወጥናቸው፡፡

ገና ይቀረኛል የሚል አመለካከት ይኑርህ፡፡

 

ማጠቃለያ

ቁርጠኝነትና ፅናት ዋልተን በሰፊው የሚታወቅበት መለያዎቹ ነበሩ፡፡ ቅዳሜ ጠዋት ከሥራ አስኪያጆች ጋር ለሚያደርገው ስብሰባ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ወይም 10 ሰዓት ተነስቶ የሳምንቱን ሂሳብ ያነባል፤ ይመረምራል፡፡ ዋልተን የተግባር ሰው ነበር፡፡ ዋል - ማርት በዚህ ፍጥነት በከፍተኛ ደረጃ ሊስፋፋ የቻለው “ሁሉንም ሥራዎች በአስደናቂ ፍጥነት አጠናቆ መጨረስ” የሚል መመሪያ ስለነበረው ነው፡፡

ህይወቱ ከማለፉ ጥቂት ቀደም ብሎ በፃፈው “Made in America” መፅሃፍ መጠናቀቂያ ላይ፤ ዋል ማርትን መገንባቱ ከቤተሰቦቹ ጋር ሳያሳልፍ የቀረበትን ጊዜ ያካክስለት እንደሆነ ዋልተን ይጠይቃል - ራሱን፡፡ ዋልተን ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስም “አዎ” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው በህይወት ውስጥ የሚጫወተው የራሱ ሚና አለው፤ ለእሱ የተሰጠው ደግሞ የነጋዴነት ሚና ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ለእሱ እጅግ አስፈላጊ እንደነበሩ ያልካደው ዋልተን፤ ግን ንግድ ደግሞ የነፍስ ጥሪዬ ነበር ብሏል፡፡

ዋልተን በ1992 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በ74 ዓመቱ በአጥንት ካንሰር ህይወቱ ያለፈ ሲሆን በቅርቡ “ፕሬዚዳንታዊ የነፃነት ሜዳል” ተሸልሟል፡፡ ዋልተን ከመሞቱ በፊት የነበሩትን የመጨረሻ ሳምንታት መደብሮቹን በመጐብኘት የማሳለፍ ፍላጐት ነበረው፡፡ ሆኖም መንቀሳቀስ ባለመቻሉ እንዲሁም በሥራ ተባባሪዎቹና በቤተሰቡ ማበረታታት “Made in America” የተሰኘውን መፅሃፉን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ (መፅሃፉ በጆን ሁይ ተባባሪ ፀሃፊነትም የተዘጋጀ ነው) ዋልተን ከባለቤቱ ከሄለን ሮብሰን አራት ልጆች ያፈራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ኩባንያውን በጋራ በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሳም ዋልተን እንደ አብዛኞቹ ስኬታማ የቢዝነስ ሰዎች ሁሉ፤ ሲነሳ ብቸኛ ሃብቱ ፅናቱና ቁርጠኝነቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን “ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች” እንዲሉ ከዋልተን በስተጀርባም ባለቤቱ ሄለን ዋልተን ነበረች፡፡

በፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪዋን ያገኘችው ሄለን ዋልተን፤ የትዳር ህይወቱ ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ከመታተሯም ባሻገር ዋል - ማርትን ሲጀምር አቅጣጫውን የመራችው እሷ ነበረች፡፡ ከጓደኛው ጋር ሊጀምር የነበረውን የሽርክና መደብር ያስተወችው ባለቤቱ፤ ቢዝነሱ ትናንሽ ከተሞች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ቀድማ የዋል-ማርትን የስኬት ዘር ዘርታለች፡፡ እናም ዋል-ማርት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ስኬታማ ኩባንያ ሊሆን በቃ፡፡ ከአገሬ ነጋዴዎች እንዲህ ዓይነቱን ኩባንያ በብዛት እናፍቃለሁ፡፡

 

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

 

  

Related Topics