በፈለጉት ጊዜ ልጅ ማግኘት አለመቻል በትዳር አለም ውስጥ እጅግ ከባዱ ነገ

የእርግዝና መዘግየት መንስኤና መፍትሄዎቹ

 

 

በፈለጉት ጊዜ ልጅ ማግኘት አለመቻል በትዳር አለም ውስጥ እጅግ ከባዱ ነገር ነው።

መኻን ሳይሆኑ የመውለዱ ነገር መዘግየት በጥንዶቹ መሃል ልዩነቶችን በመፍጠር፥ ሰላም የራቀው ትዳርና ባስ ሲልም ፍችን በማስከተል መለያየትን ያመጣል።

ፅንስ እንዲፈጠር መጀመሪያ የወንዱ የዘር ፍሬ በበቂ ሁኔታ መመረትና ተንቀሳቃሽ መሆን እንዳለበት በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ዶክተር ኤርሚያስ አለማየሁ ይናገራሉ።

በሴቷ በኩል ደግሞ እንቁላል በበቂ ሁኔታ መመረት፣ በቱቦ ውስጥ ማለፍ እና የመጣውን የወንድ የዘር ፍሬ ተቀብሎ መራባት መቻል እንዳለበትም ያስረዳሉ።

ከሶስት እና አራት ቀናት በኋላም የሴቷ እንቁላል በማህጸን ግድግዳ በመጣበቅ ሰርስሮ መግባት መቻሉ ለጽንስ መፈጠር ይረዳል ይላሉ።

 

ችግሩ እንዴት ይከሰታል

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላታቸው የመጀመሪያው ጉዳይ ሲሆን፥ በሰውነት ውስጥ የሆርሞን ማነስም ሌላው መንስኤ መሆኑን ነው ዶክተር ኤርሚያስ የሚያነሱት።

የወንድ የዘር ፍሬ ዋኝቶ መሄድ አለመቻልም ለእርግዝና መዘግየት ሌላው ምክንያት ነው።

ለዚህ ደግሞ የማህጸን ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ቆሻሻ ወደ ማህጸን እንዳይገባ የሚያግዱ ቱቦዎች (ሙከስ) መወፈርም ለዚህ መንስኤዎች ናቸው።

የሴቷ የማህጸን በር መርዘም፣ የማህጸን እጢ፣ ከልክ በላይ ውፍረትና የሰውነት መቀጨጭ ደግሞ የወንዱን የዘር ፍሬ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረግ ለዚህ ችግር ተጠቃሾች መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት።

 

መፍትሄው

የመጀመሪያው የወንዱ የዘር ፍሬ ከሴቷ ጋር እንዳይገናኝ የሚያደርገው ሙከስ ካለ፥ የወንዱ የዘር ፍሬ በሲሪንጅ አልፎ እንዲገባ ይደረጋል።

በሂደት ላይ ያለውና የወንዱን የዘር ፍሬ ወስዶ በማራባት ወደ ሴቷ ማህጸን የመክተቱ ህክምናም ሁለተኛው መፍትሄ ነው።

ይህ ህግ ግን ገና በሂደት ላይ ያለና ያልጸደቀ ሲሆን፥ በቅርቡ እንደሚጀመር ነው ዶክተር ኤርሚያስ የተናገሩት።

የሰውነት ሆርሞን ጉዳይ የሚስተካከል መሆኑን የሚያነሱት ዶክተሩ፥ ችግሩ የጋራ በመሆኑ ባልና ሚስት ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ባለሙያ ማማከር ይገባል ብለዋል።

ከሰውነት ክብደት ጋር ተያይዞም የተስተካከለ አቋም በመያዝ ችግሩን መከላከል ይቻላል።

ከላይ የተጠቀሰው መፍትሄ ለጊዜው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና በአንዳንድ የግል ህክምና መስጫ ተቋማት እየተሰጠ ይገኛል።

source : Fana

 

  

Related Topics