አንዳንድ ሰዎች ለተለያዩ ነገሮች ሲጋለጡ ሰዉነታቸዉ ይቆጣል።

የሰዉነት መቆጣት (አለርጂ)

 

Bildergalerie Nahrungsmittelintoleranzen FLASH Galerie

 

አንዳንድ ሰዎች ለተለያዩ ነገሮች ሲጋለጡ ሰዉነታቸዉ ይቆጣል። ያ ደግሞ በልዩ ልዩ መንገድ ይገለፃል። በሕክምናዉ አገላለፅ አለርጂ የሚባለዉ ማለት ነዉ። አንዳንዱን ያስነጥሳል፤ ሌላዉ ዐይኑ ይቀላል፣ ያቃጥለዋል፤ ገሚሱን ደግሞ ሲያሳክክ ይዉላል።

የሚከሰተዉ በአካባቢያችን የሚገኙ ነገሮች ስንተነፍስ ወይም አካላችንን ሲነኩ ሊሆን ይችላል። የብዙዎች ችግር ነዉ፤ አለርጂ፤ ወይም የሰዉነት መቆጣት ልንለዉ እንችላለን። መንስኤዉም እንደየሰዉ የሰዉነት የተፈጥሮ ሁኔታ ይለያያል። መፍትሄዉም እንዲሁ።

መንስኤዉ ተመርምሮ ከብዙ ሙከራ በኋላ ካልሆነ በቀር አንድን ሰዉ ለአለርጂ የሚያጋልጥ ወይም ሰዉነቱን ሊያስቆጣ የሚችለዉ ምንድነዉ የሚለዉን ለማወቅ ቀላል እንዳልሆነ ነዉ ጥናቶች የሚያመለክቱት። አንዳንዴ ከዘር ሊወረስ ቢችልም ብዙዉን ጊዜ ግን መንስኤዉ እንደየሰዉ ተጋላጭነት ሊለያይ ይችላል። እዚህ ጀርመን ሀገር የክረምቱ ወራት ዛፎቹን ቅጠል አልባ አድርጎ ያራቁትና ቅዝቃዜዉ ለቀቅ ሲል ጭራሮ መስሎ ይታይ የነበረዉ የደረቀዉ እያንዳንዱ እንጨት ቅጠሉን እንደወጉ ይለብሳል። ያኔም አበባዉ ሲያብብ ተፈጥሮን ለሚያስተዉልና ለሚያደንቅ መንፈስን በሀሴት መሙላቱ የማይቀር ነዉ፤ ግን ደግሞ ይህ ወቅት ባልመጣ የሚሉም አይጠፉም። ለምን ከዚያ ከቀን ጨለማና ደምን ከሚያረጋ ቅዝቃዜ ወጥቶ ሰዉ ይህን የብርሃንና የተስፋ ወቅት ይጠላል ሊባል ይችላል።

እነዚህ ወገኖች ግን ወደዉ አይደለም፤ ወቅቱ ለዐይን የሚያማምሩ አበቦች የሚያብቡበት፤ መሆኑም አይጠፋቸዉም ችግራቸዉ ግን የአበባዉ ብናኝ ፖለን ሰላም የከረመ ጤናቸዉ ላይ የሚያስከትለዉ እክል ነዉ። ማስነጠሱ፤ ዐይን ማሳከክ መለብለቡ፤ ጉሮሮን ለመተንፈስ መተናነቁ ሌላም ሌላም ሊዘረዘር ይችላል። ወደሀኪም መሄድ ግድ ይሆናል፤ የጤና ባለሙያዉም የሰዉነት መቆጣት ወይም አለርጂ መሆኑን ይገልፃል። አለርጂ ምንድነዉ? እዚህ ጀርመን ባድ ሪቡርግ ማርኩስ ክሊኒክ እና ኤሽቩገር ክሊኒክ አማካሪ የሆኑት የነርቭ ስፔሻሊስት ዶክተር ተሻገር ደመቀ እንዲህ ሊያብራሩልን ይሞክራሉ፤

ስለዚህ የጤና ችግር የተፃፉ የተለያዩ ጽሑፎች የችግሩን ምንነት ለማግኘት የሚደረገዉ ምርምር አሁንም እንደቀጠለ የሚጠቁሙ ከመሆን ባለፈ፤ አጠቃላይ የሆነ መንስኤ አይገልፁም። የሰዉነት መቆጣቱ ወይም አለርጂዉ እንደየግለሰቡ የሰዉነት የመጋለጥ ደረጃና ምላሽ አሰጣጥ ይለያያልና። በአብዛኛዉ ለዚህ ችግር መንስኤ ይሆናሉ የሚባሉት ነገሮችም ዶክተር ተሻገር እንደሚሉት የግድ ሰዉነትን የሚጎዱ ነገሮች ላይሆኑ ይችላሉ።

 የሰዉነት መቆጣት ወይም አለርጂ የግድ ከዕፅዋት ወይም ከእንስሳት በሚገኙ ብናኞችም ሆነ ንጥረነገሮች ጋር ላይገናኝ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች በጆሮና በእጅ እንዲሁም አንገት ላይ በሚደረጉ ጌጣጌጦች ምክንያት ለዚህ ችግር ይጋለጣሉ። ዶክተር ተሻገር ደመቀ ልዩነት መኖሩን ግን ይናገራሉ፤

ሰዉነት የሚያስቆጣዉ ነገር ወደሆድ ከገባ ነገር ጋ የተገናኘ ከሆነ ምግብ ሆነ መድሃኒት ሊሆን ይችላል፤ ማስመለስ ወይም ወደታች ማለት፤ መገለጫዉ ሊሆንም ይችላል። ከማሳከክና ከመሳሰሉት ምልክቶች በተጨማሪ። ችግሩ ጠንከር ያለ ከሆነ ደግሞ ለአደጋ እስከማጋለጥ እንደሚደርስ ዶክተር ተሻገር ደመቀ አስረድተዋል።

ምንጭ፡-http://www.dw.com/

 

  

Related Topics