አሁን ደግሞ ለቃለ-ምልልስ ከተጠሩ ምን አይነት ዝግጅትና ትኩረት ማድረግ

ቃለ-ምልልስና ቅድሚያ ዝግጅት፤

 

 

 

አሁን ደግሞ ለቃለ-ምልልስ ከተጠሩ ምን አይነት ዝግጅትና ትኩረት ማድረግ አንዳለብዎት በዝርዝር አብረን እናያለን። ለቃለ ምልልስ መጠራት ማለት ስራውን ለማግኘት እጩ መሆን ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ሌሎች ተቀናቃኝ አመልካቾች እንደርስዎ ለቃለ-ምልልስ ስለሚጠሩ ውድድሩ ተፋፋመ እንጂ አላለቀለዎትም፡፡ የሚዎዱትንና የፈለጉትን ስራ ማግኘት ያስደስታል፡፡ ያረካልም፡፡ የፈጠራ ችሎታዎንም ከተጠቀሙበት እድገትዎ ይጨምራል። ደመወዝም የቤተሰብ ማስተዳደሪያና የተለያዩ ወጭወችን መሸፈኛ ስለሆነ ለማንም ቢሆን ስራ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ስራ ለማግኘት እራስዎን አስማምተውና አቀራረብዎን አሳምረው ለቀጣሪው ክፍል መሸጥ አለብዎት፡፡ ቀጣሪውም ክፍል እስካሁን ድረስ በድምጽና በማመልከቻዎ ብቻ ያውቀዎታል፡፡ አሁን ግን በአካል ተገኝተው ፊት ለፊት እንዲዎያዩ ተጋብዘዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ የሆነ ዝግጅት ማድረግም አለብዎት፡፡ ለዕድልም ቦታ መስጠት የለብዎትም፡፡

 

መቼም ለቃለ ምልልስ ሲጠሩ፤ እንዳው ቀጣሪዎች ሲያዩኝ ይወዱኝ ይሆን? ምን ይጠይቁኝ ይሆን? ምን አይነት መልስ እሰጥ ይሆን? ምን ልልበስ? ወዘተ እያሉ መጨነቅ አይቀርም፡፡ እንዴት እንደሚዘጋጁ የማውቀውን በደንብ እነግረዎታለሁ፡፡ ምን አይነት መልስ እንደሚመልሱ ግን ምን አይነት ጥያቄዎች እንደሚጠየቁ ስለማላውቅ ሊጠየቁ የሚችሉትን ጥያቄዎች ብቻ አብረን እናያለን፡፡ መልሶቹም ምናልባት ለርስዎ ባይሆኑም መንደርደሪያ መልሶች ይሆኑልዎታል፡፡ በጣም ብዙ ነገሮች ግምትና ቁጥር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ለምሳሌ አቀራረብዎ አንሶ ትምህርትና የስራ ልምድ ብቻቸውን ግቡን አይመቱም፡፡ አቀራረብ ለስራ ማግኘትም ሆነ ለማህበራዊ ኑሯችን ጭምር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አቀራረብ ወሳኝ ከመሆኑ የተነሳ ስራ ለማግኘት ከመቶ ግማሹን ያህል ሊሸፍን ይችላል፡፡ ልብ ይበሉ! ልብስና አቀራረብን ከማየታችን በፊት አንዳንድ ሊጠየቁ የሚችሉ ጥያቄዎችን በዝርዝር እናያለን፡፡ ብዙ አይነት ጭያቄዎች አሉ፡፡ እንደ ስራው አይነትና ፀባይ ቢለያዩም ተደጋግመው የሚጠየቁ ጥያቄዎች እንደሚከተሉት ናቸው፤

 

1. ስለኛ መስሪያ ቤት ምን ያውቃሉ?

2. ከሌሎች ነጥለን እርስዎን ብቻ ለምን እንቀጥረዎታለን?

3. ለመስሪያ ቤታችን ምን አይነት አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ?

4. ከአምስት አመታት በኋላ እራስዎን እንዴት ያዩታል?

5. ደካማ ጎንዎ ምንድነው?

6. ጠንካራ ጎንዎ ምንድነው?

7. አሁን ምን እየሰሩ ነው?

8. ደመወዝዎ ስንት እንዲሆን ይፈልጋሉ? ወዘተ ናቸው፡፡ ስምንቱም ጥያቄወች ምሳሌወች ብቻ ናቸው፡፡

 

ስለ መስሪያ ቤቱ ለማወቅ ለቃለ ምልልስ በተጠሩ ጊዜ አንዳንድ ቁልፍ መረጃዎችን ቢያሰባስቡ በጣም ይጠቅምዎታል፡፡

ከነዚህም መረጃዎች አንዳንዶቹ፤ መስሪያ ቤቱ ከተመሰረተ ስንት ጊዜ እንደሆነው፣ ምን አይነት አገልግሎትና ምርት እንደሚያቀርብ፣ ደንበኞቹ እነማን እንዴሆኑ፣ ስንት ሰራተኞች እንዳሉት ወዘተ ናቸው፡፡ የምንኖርበት ዘመን የመረጃ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ስለመስሪያ ቤቱ በመጠኑ ለማወቅ የተለያዩ ምንጮችን መገልገል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ መስሪያ ቤቱ የራሱ የኢንተርኔት ገጽ ሊኖረው ስለሚችል ብዙ ነገር እዛ ያገኛሉ፡፡ ካልሆነም ሌሎች የጽሁፍ መረጃዎችን መሻት ይቻላል፡፡ ሰውም መጠየቅ ይቻላል፡፡

 

መስሪያ ቤቱ እርስዎን መርጦ እንዲቀጥርዎት ደግሞ ጉረኛ ሳይመስሉ ታታሪ ሰራተኛ መሆንዎን ለማሳመን ይጣሩ፡፡ ለምሳሌ ስራው ከትምህርትዎ፣ ከፍላጎትዎና ከልምድዎ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሊጠቅሱ ይችላሉ፡፡ ወደፊትም ለማደግና ለመዳበር ስለሚፈልጉ ስራው ለርስዎ ጥሩ በር ከፋች ሊሆንልዎት እንደሚችልም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ለስራው እርስዎ ተስማሚ እጩ መሆንዎን ማስመር ይችላሉ፡፡ ለመስሪያ ቤቱ ሊያበረክቱ የሚችሉት ነገር ቢኖር ደግሞ ከአዲስ ነገር ጋር እራስዎን ፈጠን ብለው ማለማመድ ስለሚችሉ ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተጨባጭ የሆነ ውጤትም ለማስገኘት ታታሪ ሆነው እንድሚሰሩ ማሳወቅም ይገባል፡፡ በመስሪያ ቤቱ ላይ ለውጥ አመጣለሁ እንዳይሉ ግን ይጠንቀቁ፡፡ በኋላ እንደሁኔታው ይደርሱበታል፡፡ በኋላም ቢሆን በተግባር እንጂ ለውጥ አመጣለሁ እያሉ አይደለም።

 

ከአምስት አመታት በኋላ ምን እንደሚመስሉ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኛ ስራ ቀጣሪዎች ግን ሊፈታተኑዎት ይፈልጋሉ። ቢሆንም ግን የተለያዩ አላማዎች ሊኖርዎት ይገባል፡፡ ለምሳሌ ስለቤተሰብ፣ ስለስራ፣ የተለያዩ ነገሮችን ስለማድረግ እና ስለ ስኬታቸው ወዘተ፡፡ ህይዎት እራሷ ትምህርት ቤት እንደመሆኗ መጠን በሚቀጥሉት አመታት ውስጥ በተለያዩ ነገሮች ላይ የበለጠ በእውቀት እንደሚዳብሩ መግለፁም አይከፋም፡፡ ካሁኑ የተሻልኩ ሆኜ እገኛለሁ ማለትም ይቻላል፡፡ ብዙዎቻችን ከደካማ ጎን ይልቅ ጠንካራ ጎናችንን መናገር ይቀለናል፡፡ ጠንካራ ጎንዎን ሲናገሩ ጉራ እንዳይመስልብዎት ጓዴኞቼ እንዲህና እንዲህ ይሉኛል ማለቱ ይሻላል፡፡ ለምሳሌ ማዳመጥን፣ ፍላጎትዎን፣ የትርፍ ጊዜ እንቅስቃሴዎን፣ አቀራረብዎን፣ የተለያዩ አስተያየትዎን ወዘተ በተመለከተ ሊሆን ይችላል፡፡

 

ደካማ ጎንን ለመናገር ሲሆን ግን ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ግን ሰው ፍፁም አይደለምና ደካማ ጎንም ሊኖርዎት ይገባል፡፡ ይህንን ሲናገሩ ግን ድፍን ያለ ደካማ ጎንዎን መናገር የለብዎትም፡፡ ለምሳሌ ወደ ትልቅ ከተማ ስሄድ ፎቆችን መቁጠር ስለለመደብኝ መንገደኞች ጋር መጋጨት ያጠቃኛል ማለት ጭልጥ ያለ ሁለት አይነት ሞኝነት ነው፡፡ በምትኩ ግን ጓደኞቼ ግትር አይነት ነህ፤ ምክንያቱም አንድ ጊዜ የተባለውና የታቀደው ነገር ሳያልቅ በቂ እረፍት አታደርግም " ይሉኛል ማለቱ ይሻላል፡፡ ግትር አይነት ቢሆኑም በዕቅድ መመራትዎን ያሳውቅልዎታል፡፡ እራስዎን የሚያረክስ ነገር ቢጠየቁም ስራ ለማግኘት እስከመጡ ድረስ እራስዎን ሙሉ በሙሉ ማርከስ የለብዎትም፡፡ በአርካሹ መልስዎ ይዘት ውስጥ ለስራ ሰጪው ክፍል የሚጥቅም ነገር ማዘል አለበት፡፡ በምሳሌው እንደተረዱኝ ተስፋ አለኝ፡፡

 

አብዛኛውን ጊዜ ስራ ቀጣሪወች እርስዎ አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ከተጠየቁ አሁን የሚያደርጉትንና የሚሰሩትን ባጭሩና በዝርዝር ማስረዳት አለብዎት፡፡ ስራ የሚቀይሩም ከሆን አሁን ያሉበት የስራ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ገና ከት/ቤት የወጡ ከሆነም ስለመጨረሻው ትልቁ ፕሮጀክትዎ ዙሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ስራ የሌለወት ግን ስራ ብቻ የሚፈልጉም ከሆነ የከተማ አውደልዳይ እንዳይመስሏቸው በትርፍ ጊዜዎ የተለያዩ ነገሮችን እንደሚያደርጉ መጥቀሱ አይከፋም፡፡ ለምሳሌ የሆነ ዝንባሌ እንዳለወት ወይም በጎ አድራጎት ስራ እንደሚሰሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን አሁን እርስዎ ለራስዎም ሆነ ላካባቢዎ የሚጠቅምና ፍሬማ ነገር የሚያደርጉ መሆንዎን ቀጣሪወቹ ግምት ውስጥ እንዲያስገቡት ነው፡፡

 

ደመወዝስ? ጥያቄው አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ስለመስሪያ ቤቱ አጥንተው ከሆነ የደመወዙን መጠንና አካባቢ በቀላሉ ያውቁታል፡፡ ከት/ቤት በቅርቡ የጨረሱ ከሆነ፣ የስራ ልምድ ካለዎት፣ የመስሪያ ቤቱ አይነት፣ የሰራው አይነትና ሃላፊነት የደመወዙን መጠን ይወስነዋል፡፡ ቁጥር ከመጥራትዎ በፊት ግን ለኔ ለእድገት በር ከፋችና የምወደውን ስራ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ስራ ለማግኘት ያመለከትኩት ለዚሁ ነው ብለው ቢጀምሩ ነገሮች ይለሰልሳሉ፡፡ ግምትም ውስጥ አይገቡም፡፡ ቁጥርም መጥራት ካስፈለገ ምክንያታዊ ሆኖ ጥሩ ደመዎዝ መጠየቅ አለበወት፡፡ እርካሽ ደመወዝ ከጠሩ የስራ ለማኝ ስለሚያስመስል ምክንያታዊ የሆነ ጥሩ ቁጥር መጥራት አለብወት፡፡

 

አቀራረብና ልብስ።

ለቃለ ምልልስ ሲጠሩ ምን ልልበስ? ምን ልጫመት? ምን ልኳኳል? እያሉ ማሰብ አይቀርም፡፡ ልብስ የእርቃን መሸፈኛ ብቻ ነው ብሎ ችላ ማለትም አያስፈልግም፡፡

እንዳገሩ ሁኔታ ቢሆንም ገላን ታጥቦ ንፁህና ለሰውነትዎ የሚስማማ ልብስ ከለበሱና ከተጫመቱ በቂ ነው፡፡ ከረባት የግድ ማድረግ የለብዎትም፡፡ ለጋብቻ እንደተጠራ አሸብርቆ ወይም አጊጦ መሄድም አያስፈልግም፡፡ የቀለሙ ቅንብርና ለሰውነት የሚስማማ ልብስ መምረጥና መጠቀም እራሱ ችሎታ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ስንቱ በየመንገዱ ተንጀርፎ የምናየው፡፡

 

ስለዚህ ለእርስዎ የሚስማማዎትን የልብስና የጫማ አይነት መምረጥ ይኖርብዎታል፡፡ ጥፍር መከርከምና ፀጉር መበጠር አለበት፡፡ ከሩቅ የሚጣራ ሽቶ ያስገምታል፡፡ የከንፈር ቀለምና ኩላኩል ነገርም ማብዛት አያስፈልግም፡፡ ደረትም ባይጋለጥ ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ወንዶች አንገት የሚደርስ ሙሉና ክብ ሹራብ ለብሰው ኮት ቢደርቡበት ያምርባቸዋል፡፡ ሴቶች አመልካቾች ደግሞ ከልብሳቸው ቀለም ጋር የሚስማማ ሻሽ ነገር አንገታቸው ላይ ሸብ አድረገው በደረታቸው ላይ ጠልጠል ቢል የሚያምርባቸው ይመስለኛል፡፡ ያየሩ ንብረት ከፈቀደም ሴቶች ቀሚስ ቢለብሱ ይመረጣል፡፡ የተለያዩ አቀራረቦች ቢኖሩም ማንም ቢሆን የሚመርጠው ቀና የሆነ አቀራረብን ነው። ታዝበው ከሆነ መጥፎ ነገር ቀርቶ ደህና ነገር ላይ እንኳን ሲያስቡ፣ ሲናገሩና ሲመለከቱ ሳያውቁት በተለምዶ ፊታቸው የሚኮሰተር ሰዎች በርካታ ናቸው። እነሱ እራሳቸው ባያውቁትም ተመልካቹ ግን ያውቀዋል፡፡

 

የመጀመሪያ ግምገማ ወሳኝ እስከሆነ ድረስ ስራ ፍለጋ ሄደው ፊትዎን አኮሳትረው እራስዎን እንዳይቀጡ፡፡ አደራ፡፡ ሲናገሩና ሲያስቡ ፊትዎ ምን እንደሚመስል በመስታወት ወይም በጓዴኛዎ በቅድሚያ መለማመድ ይችላሉ፡፡

ለቃለ ምልልስ የሚሄዱበትን ቦታ ቀደም ብለው አድራሻውን ካዎቁ ከሃሳብና ጭንቀት ይድናሉ፡፡ በቀጠሮውም ሳይዘገዩ አምስት ደቂቃ አካባቢ ሲቀረው በስፍራው መገኘት ይጠቅመዎታል፡፡ እጅዎንም ካላበዎት በመሃረም ነገር ያድርቁት፡፡ ቀጣሪው ክፍልም በሚቀበልዎት ጊዜ አንገትዎን ቀና፣ ፊትዎንና ትካሻዎን ዘና አድርገው ፊት ለፊት እያዩ ሞቅና ጠበቅ ያለ ሰላምታ ይስጡ፡፡ ስመወንም ያስተዋውቁ፡፡ ከዚህ በፊት በስልክ ያነጋገሩት ግለሰብ መጥቶ ከተቀበለዎትና በስሙ እርግጠኛ ከሆኑ፤ ከርስዎ ጋር ከዚህ በፊት ስለስራው ተነጋግረናል ብለው መጥቀስ ይችላሉ፡፡ ወደ ውይይት ክፍሉ ሲወሰዱ መተላለፊያው፣ ጓዳውና ኮተቱ የበዛበት ከሆነ፤ በኋላ ሲወጡ መውጫው እንዳይጠፋዎት ያስታውሱ፡፡ በኋላ እንዳይታዘቡዎት፡፡ እኔ ኣንድ ጊዜ ተሸውጃለሁ። ክፍሉም ውስጥ እንደገቡ ሌሎች ሁለት አካባቢ የሚሆኑ በነገር የሚፈታተኑወት ግለሰቦች መኖራቸው ስለማይቀር ለነሱም ሞቅ ያለ ሰላምታ ያቅርቡ፡፡ ስማቸውንም ለማስተዎስ ይሞክሩ፡፡ ክፍሉም ጥሩ ከሆነ ወይም ጠረንጴዛው በቅጡ የተዘጋጀ ከሆነ ወይም ግድግዳው ላይ ጥሩ ስዕል ካዩ ጥሩ መሆኑን ቢገልጹ ጥሩ ታዛቢ መሆንዎን ያሳያል፡፡ ካላማረዎት ግን ማስመሰል ስለሚሆን አፍዎን አያበላሹ፡፡ ሲቀመጡም ሌሎቹን መጀመሪያ ቢያስቀድሙ ጥሩ ነው፡፡

 

ከተቀመጡ በኋላም ተዝናንተው በስርአት ይቀመጡ እንጂ ዝልፍልፍ ወይም ጭብጥ አይበሉ፡፡ የፈሩም አይምሰሉ፡፡ እግርዎን ሳያነባብሩ ቁጭ ብለው እጆችዎ ጭነዎ ላይ አርፈው አገጭዎ ፎቶ እነደሚነሳ ሰው ቀና ብሎ፤ ትካሻዎና ወገብዎ ሲዝናና ከተሰማዎት ግሩም አቀማመጥ ይመስለኛል፡፡ ፊትዎም ዘና ማለቱን ሁልጊዜ ያስታውሱ። ይህ አቀማመጥ እንደተጠበቀ ሆኖ እጅዎንም ሆነ ሰውነትዎን በተገቢው ለማንቀሳቀስ ምቹ ነው፡፡ በሚናገሩ ጊዜ የጠየቀዎትን ግለሰብ በቀጥታ እያዩ ቢሆንም ሌሎቹንም ለአፍታ ገረፍ ማድረግ አለብዎት፡፡ ሌሎች በሚናገሩ ጊዜ እንዳያቋርጧቸው ጠንቀቅ ይበሉ፡፡ አቀርቅረው አያውሩ፡፡ የሚናገሩት ቋንቋም አንድ ሆኖ ግልፅና ሙሉ መሆን አለበት፡፡ አፉን እንደሚፈታ ህጻን ልጅም መንተባተብ አይገባም፡፡ ቀጣሪዎቹ ምን አሉ? እንዲሉዎት እድል አይስጡ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር እጅዎን አያወናጭፉ፡፡ ነገርን ባጭሩ ይመልሱ እንጂ ያለአስፈላጊ ብዙ ትንተና ውስጥ ገብተው ነገር አይበላሽብዎት፡፡ የማያውቁት ነገር ከተጠየቁ ይህንን አላውቅም ማለት ይሻላል፡፡ ሲያዳምጡም ሆነ ሲናገሩ የፊትዎ ገጽታ የዘናና የተዝናና መሆኑን በውስጥዎ ያስታውሱ፡፡

ምንጭ፡-tatariw.