የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና፣ የብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ወልደ ሥላሴ

የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና፣ የብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ወልደ ሥላሴ አጭር የሕይወት ታሪክ

 

Image result for የብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ

 

ብ/ጄ ለገሠ ተፈራ፤ ከአባታቸው ከአቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ተናኜ ተክለ ወልድ፤ ነሐሴ 13 ቀን 1934 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፤ ሾላ ላም በረት በሚባለው አካባቢ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም፤ በአቅራቢያቸው በሚገኘው የደጃዝማች ወንድይራድ ት/ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ፤ በኮከበ ጽብሐ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለው በጥሩ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ጄኔራል ለገሠ፤ አገራቸውን በውትድርና ሙያ ለማገልገል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ፤ ጥቅምት 1 ቀን 1956 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የሐረር ጦር አካዳሚ የ7ኛ ጊዜ ተወዳዳሪ ዕጩ መኮንን በመሆን፤ አንጋፋውን የኢትዮጵያ የምድር ጦር ሠራዊት ተቀላቀሉ፡፡ ከዚያም፤ በሐረር ጦር አካዳሚ የተሰጠውን ወታደራዊ የአዛዥነት ትምሕርት ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ያህል ሲከታተሉ ከቆዩበኋላ፤ ለበራራ ትምሕርት የሚያበቃቸውን ፈተና በአጥጋቢ ውጤት በማለፋቸው፤ ወደ ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዛወሩ፡፡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የበረራ ትምሕርታቸውን እየተከታተሉ፤ ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የሐረር ጦር አካዳሚ የ7ኛ ኮርስ ጓደኞቻቸው ጋር፤ ጥቅምት 5 ቀን 1959 ዓ.ም. በም/መ/እልቅና ማዕረግ በዲኘሎም ተመርቀዋል፡፡ከዚያም ወደ ደብረ ዘይት አየር ኃይል ተመልሰው ቀሪውን የበረራ ትምህርታቸውን ተከታትለው በአጥጋቢ ውጤት ፈጽመዋል፡፡

በጥሩ ስፖርታዊ አቋማቸው የሚታወቁት ጄኔራል ለገሠ ተፈራ፤ የእግረኛ ጦር አዛዥነት ትምሕርትን ከበረራ ትምሕርት ጋር አንድ ላይ አዋህደው ሥልጠና ከወሰዱት በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት የአገራችን ምርጥ መኮንኖች መካከል አንዱ ለመሆንም፤ በቅተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘጠነኛው ስኳድሮን ውስጥ ሥራቸውን“ሀ” ብለው የጀመሩት ጄኔራል ለገሠ፤ ከጦር ግንባር ግዳጃቸው በተጨማሪ በበረራ ትምሕርት ቤት ውስጥ በአስተማሪነት ተመድበው ብዙ ተተኪዎቻቸውን አፍርተዋል፡፡ሙያቸውን የበለጠ እንዲዳብሩም፤ ለከፍተኛ የF-5E ኢንተር ሴፕተር የበረራ ትምሕርት፤ አሪዞና ወደሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ኮሌጅ ተልከው፤ ለአንድ ዓመት የተሰጠውን የበረራ ትምሕርት በጥሩ ውጤት አጠናቀው፤ ወደ እናት አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በ1960ዎቹ ገደማ፤ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና እንግዳቸው ለነበሩት የኬንያው ኘሬዜዳንት ጆሞ ኬኔያታ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ትርዒት በቀረበበት ወቅት፤የበረራ ብቃታቸውን ካስመሰከሩት የአየር ኃይሉ አብራሪዎች መካካል፤በወቅቱ መቶ አለቃ የነበሩት፤ ለገሠ ተፈራ አንዱ ናቸው፡፡ በ1969 ዓ.ም. ዕብሪተኛው የሶማሊያ መንግሥት፤ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ታጥቆ የአገራችንን ድንበር በመጣስ፤ በየነጥብ ጣቢያ ተበታትነውና ተራርቀው የሚገኙትን፣ የጦር ክፍሎችና የፖሊስ ጣቢያዎችን እየደመሰሰ፤ በምሥራቅና በደቡብ የአገራችን ክፍል 700 ኪሜ ያህል ዘልቆ በመግባት ወረራ በፈፀመበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት፤ የዚያን ጊዜው ሻለቃ ለገሠ ተፈራ፤ ከሌሎች የአየር ኃይል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን፤ ጠላትን በማርበርበድ፤ አገርንና ሕዝብን ከጥፋትና ከውርደት ታድገዋል፡፡ በዚሁም መሠረት፤የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምዕራፍ አንድ ዘመቻው፤ጄኔራል ለገሠና ጓዶቻቸውን አሰማርቶ፤ የጠላትን የምድር ይዞታዎች ከማውደም ተልዕኮ በላቀ ሁኔታ፤ ከሐምሌ 17 ቀን 1969 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1969 ዓ.ም. ድረስ ያለማቋረጥ በተናጠልና በቡድን ሆነው ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር ባካሔዱት የአየር ለአየር ውጊያ፤ የጠላትን አየር ኃይል አሥራ ሁለት ሚግ - 21 እና አሥራ ሶስት ሚግ -17 በድምሩ ሃያ አምሥት ተዋጊ አውሮኘላኖችን ከአየር ላይ በማራገፍ፤ የጠላትን ቅስም ሰብረውና አቅሙን አሽመድምደው አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፤ ከኢትዮጵያ አየር ላይ በማባረር፤ ዳግም የአገራችንን የጠፈር ክልል እንዳያያትና ዝር እንዳይልባት አድርገዋል፡፡

ይህንን አኩሪ ገድል ከፈፀሙት ብርቅዬ የአገራችን የቁርጥቀን ልጆች መካከል አንዱና ዋናው፤ በግል የጠላትን ስድስት አውሮኘላኖች ያወደሙትና ሁለት ሚግ- 21 ጄቶችን እርስ በእርስ በማጋጨት፤ በሕዝባችን ላይ ለማዝነብ የታጠቁትን ቦምብ እንደያዟት በአየር ላይ በማጋየት ያወደሙት፤ የአየሩ ላይ ነብር ብ/ ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ነበሩ፡፡ ጄኔራል ለገሠና የአየር ኃይል ጀግኖቻችን፤ ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር ባካሔዱት የአየር ለአየር ውጊያ፤ የጠላትን አውሮኘላኖችን በማውደምና ከኢትዮጵያ የአየር ክልል ላይ በማባረር ብቻ ሳይወሰኑ፤ ሶማሊያ ውስጥ በሚገኙት በሐርጌሣና በበርበራ የአየር ኃይል ጦር ሠፈሮች ላይ ዘምተው፤በማኮብኮቢያ ሜዳ ላይ ቆመው የነበሩትን ሚግ - 21 እና ኢሉዥን - 28 እንዲሁም፤ ሌሎች በርካታ ወታደራዊ ሔሊኮኘተሮችን በማውደምና በማቃጠል፤ የጠላትን የጦር መሣሪያና የፈንጂ ግምጃ ቤቶችን፣ የስንቅና ትጥቅ ማከማቻ ዴፖዎችን፣ወታደራዊ አገልግሎት የሚሠጡ ወደቦቹንና የነዳጅ ማጠራቀሚያ ግዙፍ ታንከሮችን በመደብደብ፤ በተለይም የሶማሊያን አየር ኃይል በአገሩ ምድርና ሰማይ ላይ እንደልቡ እንዳይላወስ፤ ቁም ስቅሉን አሳይተው መድረሻ በማሳጣት፤ አቋሙን አናግተውና አከርካሪውን ሰብረው፤የተረፉ ጥቂት አውሮኘላኖቹን ይዞ ወደ ደቡብ ሶማሊያ የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር የጠረፍ ከተማ ኪስማዩ ወስዶ እንዲደብቅና እንደ መኪና መሬት ላይ እንዲቀሩ አድርገዋል፡፡ ጄኔራል ለገሠና የአየር ኃይል ሠራዊት በሙሉ፤ሌት ተቀንተረባርበው የሶማሊያን አየር ኃይል አሽመድምደው ከውጊያ

ውጭ ካደረጉት በኋላ፤ በምዕራፍ ሁለት ሙሉ ዘመቻቸው፤ ያለምንም ተቀኛቃኝ የሶማሊያን እግረኛ፣ ታንከኛ፣ መድፈኛና አየርመቃወሚያ በአጠቃላይ ሜካናይዝድ ክፍሉን እንዲሁም የፊትናየኋላ ወረዳውን በዋናነት፤በተለይ ደግሞ፤በድሬዳዋ ግንባር፤- በጀልዴሣ፣ በሐረዋ፣ በሁርሶ፣ በሐወሌ፣በሺኒሌ፣ በአልባሕና በአይሻ፤ በሐረር ግንባር፤- በቢሲዲሞ፣በባቢሌ፣ በፈዲስ፣ በኮምቦልቻ፣ በአሪፍ ካሊድ፣ በኦማርኬሎ፣በጂጂጋ ግንባር፤- በካራማራ፣በፋፈም፣ በሐደው፣በቆሬ፣ በጭናክሰን፣ በፊቅ፣ በቀብሪ በያህ፤ በኦጋዴን ግንባር፤በደገሐቡር፣ በቀብሪ ደሐር፣ በዋርደር፣ በወልወል፣ በኤሚ፣በጎዴ፣ በቀላፎ፣ በሙስታሒል እና በዋቢ ሸበሌ ሸለቆዎች፣በደቡብ ጦር ግንባር፤- በዶሎ፣ በባሬ፣ በኤልከሬ፣ በሐርገሌ፣በገናሌ ሸለቆዎችና በፊልቱ፤በሶማሊያ ውስጥም፤ በሐርጌሣ፣በበርበራ፣ በጋልካዮ እና በሎግፈራንዲ ድልድይ እንዲሁም፤ሌሎችንም የጠላት ወታደራዊ ይዞታዎችን ከአየር ላይ ሆነውአናት አናቱን በመደብደብና በመደምሰስ፤ ለኢትዮጵያ እግረኛናሜካናይዝድ ጦር የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ አመቺ ሁኔታ ፈጥረውወራሪው ሠራዊት እንዲፍረከረክና እንዲበታተን፤ በመጨረሻም ከአገራችን ግዛት ተጠራርጎ እንዲወጣ የበኩላቸውን አኩሪ ግዳጅ ተወጥተዋል፡፡.ከጠላቶቻችን በሰተ-ጀርባ ሆነው ውድቀታችንን ይናፍቁ የነበሩትን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ሁሉ በማሳፈርና በማሸማቀቅ፤ አገርና ወገንን ካኮሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጀግኖቻችን መካከል፤የወራሪው ጦር የአየር ላይ መቅሰፍት፤ ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እንደ ሶማሊያ አየር ኃይል ሁሉ በምሥራቁ አውደ ውጊያ በለስ ያልቀናው የሶማሊያ የምድር ጦር ሠራዊት፤ የሞተው ሞቶየአውሬና የአሞራ ሲሳይ ሆኖ ሲቀር፤ የተረፈው እግሬ አውጭኝ ብሎ ወኔና ቀን ከድቶት በሽሽት ወደ መጣበት ሲፈረጥጥ፤ዕብሪተኛው መንግሥት ከዚያ በኋላ የቀረውን ያለ የሌለ እግረኛና ሜካናይዝድ የጦር ክፍሎቹን አሰባስብቦ በደቡብ ግንባር በማሰለፍ፤በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ወስጥ የጥፋት ተልዕኮውን በከፍተኛ ደረጃ መፈፀም ጀመረ፡፡በዚህ ግንባር የወገን እግረኛ ሠራዊት ወረራውን ጦር በመመከት ከጠላቱ ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ በሚያደርግበት ወሳኝ የሞት ሽረት ወቅት፤ የአየር ድጋፍ በማስፈለጉ፤ ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥሪው እንደደረሰው ደቂቃ ሳያባክን፤ በምሥራቅ ጦር ግንባርበሽሽት ላይ የሚገኘውን የሶማሊያ እግረኛና ታንከኛ ጦርን እያሳደዱ በመምታት ግዳጅ ላይ የነበሩትን ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራን ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር በፍጥነት ተመልሰው፤ ለካምቤራ አውሮኘላን ሽፋን እየሠጡ እንዲዋጉ አዘዛቸው፡፡ ሙሉ ቀን ግዳጅ ላይ የዋሉት ጄኔራል ለገሠ፤ ያለምንም ማመንታት ራበኝ ጠማኝ ሳይሉና ዕረፍት ሳያምራቸው፤ ከሌሎች አብራሪ ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው፤ በፍልሚያ ላይ የነበረውን የወገንን እግረኛ ጦር ለመታደግ፤ ወድያውኑ F-5E ጄታቸው ውስጥ ተመልሰው በመግባት፤ ወደ ፊልቱ ጦር ግንባር እንደ ቀስት ተወረወሩ፡፡ ወራሪው የሶማሊያ ሠራዊት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምሥራቅ ጦር ግንባር ያደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ በስለነበር፤ ይህንን የአየር የበላይነት የነበረውን የወገን ሠራዊት ለመቋቋም የሚያስችል ዝግጅት አድርጎ በደቡብ በኩል ብቅ ቢልም፤ የሶማሊያ ጦር ሳያሰበው በድንገት አናቱ ላይ ደርሰው፤ እንደ ብራቅ አንባርቀው ሰማይ መሬቱን በአስፈሪ ድምፅ ደበላልቀው በነቀነቁት በጄኔራል ለገሠ ተፈራና በ F-5E ጄት አውሮኘላናቸው ድንገተኝነት ተርበተበተ፡፡ ምድር ቀውጢ ሆነች፡፡

የጠላት አየር መቃወሚያ መሣሪያዎች የሞት ሞታቸውን ላንቃቸውን በመክፈት፤ በፊልቱ ሰማይ ላይ ጥይቶቻቸውን እንደርችት በመተኮስ ሞሉት፡፡ ጄኔራል ለገሠ ምንም ሳይደናገጡ፤ የጠላትን አሰላለፍና ይዞታ ለመቃኘትጭራሽኑ ዝቅ ብለው በረሩ፡፡ከፈጣኑ ቅኝታቸው ያዩትንና የተገነዘቡትን ዋናውን ግዳጅ ለሚፈጽሙትለካምቤራው አብራሪ ጠቁመው፤ ወደ ላይ ከፍ ብለው ለመብረር ሲሞክሩ፤ራስንለመከላከል በድንጋጤና በደመ-ነፍስ የተተኮሰውና የፊልቱን ሰማይ የሞላውየሶማሊያ ጦር ጥይት፤ ለወራት ያህል የጠራራ ፀሐይ መብረቅ ሆነውያሸበሩትን የጄኔራል ለገሠ ተፈራን F-5E ጄት አውሮኘላናቸውን አገኛት፡፡የጠላት ጥይት አውሮኘላኗ ውስጥ 75 በመቶ ተሰገሰገ ፡፡ የጄታቸው የኋለኛውአካል መጨስ ጀመረ፡፡ የአየሩ ላይ ነብር ከጓዶቻቸው ጋር የነበራቸው የሬድዮግንኙነት፤በአውሮኘላኗ ራዳር መመታት የተነሣ፤ተቋረጠ፡፡መስከረም 11 ቀን 1970 ዓ.ም. ጄታቸው በገጠማት በዚህ ከፍተኛ ጉዳትየተነሣ፤ ለመከስከስ ወደ መሬት ተንደርድራ ጥቂት ሜትሮች ያህል ሲቀራት፤ለገሠ፤ ጠላት በስፋት በሚርመሰመስበት ወረዳ ውስጥ ከነበሩበት ከፍታ ላይሆነው በፓራሽት ወደ መሬት ዘለሉ፡፡ካምቤራ የዕለቱን ውጊያ በአጥጋቢ ውጤት ፈፅሞ የጠላትን ጦር በመደምሰስ ለወገን እግረኛ ጦር አመቺ ሁኔታ ፈጥሮ ወደ ሠፈሩ በሰላም ቢመለስም፤ሽፋን ሰጥተውትና ቅኝት አድርገው ለውጤት ያበቁት የአየሩ ላይ ነብርናየኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ግን፤ እዚያው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር፤ ፊልቱ ጦር ግንባር ላይ ቀሩ፡፡ አልተመለሱም፡፡የጠላት ግስጋሴ በካምቤራ ከፍተኛ ጥቃት በመገታቱና ጄኔራል ለገሠም ዝቅብለው በመዝላላቸው፤ እንደ ዕድል ሆኖ የጠላት ጦር ሳያያቸው ጫካ ውስጥውለው አደሩ፡፡

የአየሩ ጀግና ከአውሮኘላኗ ዘለው ሲወርዱ ባጋጠማቸው የእግር ወለምታየተነሣ፤ብዙ ተጉዘው ከወገን እግረኛ ጦር ጋር ለመቀላቀል ተሳናቸው፡፡በደቡብ ጦር ግንባር የተሠማራው የኢትዮጵያ ጀግና እግረኛ ሠራዊትም፤በሰፊው የውጊያ ቀጠና ውስጥ በአንድ በኩል ከጠላቱ ጋር እየተፋለመ፤ በሌላበኩል ደግሞ፤ የአየሩን ጀግና በብዙ አቅጣጫዎች ያለማቋረጥ ሲፈልጋቸውዋለ፣ አደረ፡፡ ሆኖም ግን፤ ሊያገኛቸው አልቻለም፡፡በፊልቱ ጫካ ውስጥ በከፍተኛ ድካም ላይ የነበሩት ለገሠ ግን፤ ውኃሊሰጧቸው በቀረቧቸውና በሶማሊያ መንግሥት ካድሬዎች በተወናበዱየአገራችን ዜጎች ጥቆማ፤ መስከረም 12 ቀን 1970 ዓ.ም. ሳያስቡትበድንገት፤ ጎናቸውን ለማሳረፍ ጋደም ብለው በእንቅልፍ ሰመመን ውስጥእንዳሉ፤ በጠላት ወታደሮች ተያዙ፡፡ጄኔራል ለገሠ፤ ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰባቸውናይህንኑ ሠራዊት እጅግ በጣም በሚፈሩትና አምርረውም በሚጠሉት፤ሶማሊያውያን እጅ ወደቁ፡፡ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በወቅቱ የአየሩ ላይ ነብር በጠላትእጅ ስለመውደቃቸውም ሆነ፤በግዳጅ ላይ ስለመሰዋታቸው ምንም ዓይነትማረጋገጫ ባለማግኘቱ፤ ለጊዜው፤ በግዳጅ ላይ መጥፋታቸውን ብቻ አምኖ ተቀበለ፡፡በመሆኑም፤ የኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት፤ የዘወትር ወታደራዊግዳጅ ከሚጠይቀው በላይ ወደር የሌለው ጀግንነት ለፈፀሙ የሠራዊቱ አባላት የሚሰጠውንና በአገሪቱ የመጨረሻና ከፍተኛ የሆነውን፤ የኅብረተሰብአዊትኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይ፤ መስከረም 3 ቀን 1972 ዓ.ም. በአብዮት አደባባይ በተከናወነ ደማቅ ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ፤ ለአየሩ ላይ ነብር ለሻለቃ ለገሠ ተፈራ፤ ከሌ/ኮሎኔልነት የተፋጠነ የማዕረግ ዕድገት ጋር፤ በሌሉበት ሰጥቷቸዋል፡፡

በወቅቱ አብዮት አደባባይ በመገኘት፤ ሽልማቱን ከአገሪቱ መሪ ከሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ የተቀበሉት፤ዛሬ በሕይወት የሌሉት፤ቆፍጣናው የአየሩ ጀግና ወላጅ አባት፤ አቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴ ነበሩ፡፡ ጄኔራል ለገሠ፤ በፊልቱ ጦር ግንባር የጠላት ጦር አዛዥ የነበሩትና ከዚያድ ባሬ መንግሥት መውደቅ በኋላ፤ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ኘሬዜዳንትበመሆን ያገለገሉት ኮሎኔል አብዱላሂ ዩሱፍ ፊት ተይዘው በቀረቡበት ወቅት፤ ኮሎኔሉ ለበላይ አለቃቸው ሪፖርት ሲያስተላልፉ፤ በወገን የሬድዮ ሠራተኞች የተጠለፈው መልዕክታቸው እንደሚያስረዳው፤ ‹‹ ሰውየው ከነብር የበለጠ ቁጡ ነው፡፡ ጠላት እጅ የገባም አልመሰለው፡፡ ተለሳላሽ አይደለም፡፡ ሰው ሲማረክ አንገቱን ይሰብራል፡፡ የማረከው እንዲራራለት አንገቱን ይደፋል፡፡ ይህ ሰው ግን ለየት ያለ ነው፡፡ ግድ ያለውም አይመስልም ፡፡ መረጋጋቱና ኩራቱ ያናድዳል፡፡ ወደ እናንተ ስልከው ይህንን ትዕቢቱን፣ ቁጣውንና ኩራቱን ከውስጡ ጨምቃችሁ ማውጣት አለባችሁ፡፡ … ስለዚህ ሶማሊያ ማን እንደሆነች እንዲያውቅ መማር ይኖርበታል! ›› በማለት በሬድዮ ወደ ሞቋዲሾ መልዕክት ሲያስተላልፉ ተደምጠዋል፡ ፡ በዚህም፤ ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ጀግንነታቸውንና ቁርጠኝነት የተላበሰው ወኔያቸውን፤ ወገን ብቻ ሳይሆን፤ ጠላቶቻችን ሳይቀሩ መስክረውላቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሶማሊያ ተልከው ከመሥመራዊ መርማሪ መኮንኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣኖች ድረስ ተራ በተራ እየተፈራረቁ ምርመራና ቃለ መጠይቅ አድርገውላቸዋል፡፡ በመጨረሻም፤ በጣልያን ቅን ገዢዎች እንደተሠራ በሚነገርለት ወደ ሼሎ ሞርቴ፤ ልዩ ስሙ ላንታቡር ወደ ተባለ የሞት ዋሻ እስር ቤት ተላኩ፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ እንደገቡ፤ ያለአንዳች የመኝታ ልብስ በጭካኔ በደረቅ ሲሚንቶ ላይ፤ ለ11 ዓመታት ያህል በእርዛት እንዲተኙ ተደረገ፡፡ የነቀዘና የተበላሸ ምግብ እየተሰጣቸው የመቃብር ሕይወትን አሳልፈዋል፡፡በአገሪቱ የፀጥታ መኮንኖች፤በየጊዜው ድብደባና ግርፋት የታከለበት ምርመራ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ አንዳች ሕክምና ሳያገኙ በሞት ጥላ ውስጥ፤ለዘመናት የፀሐይ ብርሃንን ሳያዩ፤ በጨለማ ቤት ኖረዋል፡፡ በዓለም ላይ ከሞት በላይ አሉ የተባሉ ሥቃይና መከራዎችን ሁሉ፤ በሶማሊያ እሥር ቤቶች ውስጥ ተቀብለዋል፡፡ በዚያ ክፉ ዘመን፤ ሞትን እንደ አንድ ጥሩ ነገር ተመኝተውትም፤ አጥተውታል፡፡ በመጨረሻም በኃያሉ አምላክ በልዑል እግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት፤ ሁለቱ አገሮች የጦር ምርከኞችን ለመለዋወጥ በአደረጉት ስምምነት መሠረት፤ የአየር ኃይሉን ጀግና ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ ከዚያ የሞት መንደር ተርፈውና ተፈተው፤ ነሐሴ 17 ቀን 1980 ዓ.ም. ወደ ውዲቷ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የጽልመት ዘመናቸው በእግዚአብሔር እርዳታ ተገፎ ወደ ብርሃን ከተለወጠ በኋላ፤መስከረም 1 ቀን 1981 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊት ዲሞክራሲዊት ሪፑብሊክ መንግሥት፤ ለኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ ለአየሩ ላይ ነብር፤ለሌተና ኮሎኔል ለገሠ ተፈራ የብ/ጄኔራልነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡በዚሁ ዕለትም የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የየካቲት 66 አንደኛ ደረጃ ኒሻን ሸልሟቸዋል፡፡

በተመሣሣይ የአብዮታዊት ኩባ መንግሥትም፤ የአየሩን ጀግና ወደ አገሩ ጋብዞ፤ የአገሪቱን ከፍተኛ የጀግና ሜዳይ ሸልሟቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ፤አንዱ ዘመን አልፎ፤ ሌላው ተተካ፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ጄኔራል ለገሠ፤ በሥራ ምክንያት ከቤተሰባቸው ጋር፤በመጀመሪያ ወደ ጣልያን አገር፤ ቀጥሎም ወደ ጄኔቭ ሰዊዘርላልድ፤ በመጨረሻም ወደ አሜሪካ በመሄድ፤ ዳግም የስደት ኑሯቸውን ጀመሩ፡፡ አሜሪካን አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የጀግኖች ምሽት በማዘጋጀት፤ለብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ፤ ለውድ እናት አገራችን ኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በመዋደቅ ለአበረከቱት ወደር ለሌለው ለማይረሳው አኩሪ የተጋድሎ ውለታቸው፤ ከፍተኛውን ሽልማት ሰጥተዋቸዋል፡፡ የአየሩ ላይ ነብር፤ አሜሪካ ደርሰው ሥራ ከጀመሩ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን፤ ለአሥራ አንድ ዓመታት በሶማሊያ እሥር ቤት፤ በአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለብቻቸው ታሥረው በከፍተኛ ጉስቁልናና በጭካኔ ደረቅ ሲሚንቶ ላይ ተኝተው ያሳለፉት የመከራ ሕይወት በአስከተለባቸው የጤና ችግር የተነሣ፤ ቀስ በቀስ፤ድካምና ሕመም እየተሰማቸው መጣ፡፡ ጊዜ እያለፈ ሲሄድም፤ የአየሩ ጀግና እቤት መዋል ጀመሩ፡፡ እያደርም፤ … እንደዋዛ … አልጋ ላይ ቀሩ፡፡ ለዘመናት በአካል ጥንካሬ ዳብሮ፤ እንደ አለንጋ እጥፍ ዘርጋ ይል የነበረው ያ… ዘንካታ ገላ፤ አልላወስ አለ፡፡ እምቢ አለ፡፡ ወደ ማታ፤ነብሩ ተሸነፈ፡፡ ለገሠ፤ተያዘ፡፡

ጄኔራል ለገሠ ከሕመማቸው እንዲያገግሙ በርካታ ተከታታይ ሕክምና ተደረገላቸው፡፡ ይሁን እንጂ፤ የሐኪሞች ርብርቦሽና ጥረት የሶማሊያ እሥር ቤት ካወረሳቸው ሕመም፤ በቀላሉ ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ በመጨረሻም፤ የቤተሰብ፣ የወዳጅ ዘመድና የኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ፍቅርና አክብሮት ያልተለያቸው፤ ተግባቢውና ትሁቱ፣ ትልቅ ትንሹ የሚወዳቸው፣ የሰው መውደድና ፍቅር ሃብታቸው የነበረው፤ አስተዋዩና ታዛዡ የአየሩ ጀግና፤ ለዘመናት ሲፋለሙት ከኖሩትና ፈፅሞ ከማይፈሩት ሞት ጋር ተፋጠጡ፡፡ እንዲህ ሆኖ፤ዘመኑ ተፈፀመ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ፤ለአዳም ዘር የሰጠውን ሕግ መተላለፍ አይቻልምና የኢትዮጵያን ጠላቶች በአየር ላይ እያርበደበዱ ተዋግተው ዶግ አመድ ያደረጉት፣የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊትን ተዋጊ ሚግ አውሮኘላኖችን ከአገራችን አየር ላይ እንደቅጠል ያረገፉትና እንደ ጉም ያበነኑት፣ ጠላቶቻችን ሳይቀሩ ጀግንነታቸውን የመሰከሩላቸው፣የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታና ፈርጥ፣የአየር ኃይሉ ነጎድጓድ፣ የአገራችን የቁርጥ ቀን ልጅ፣ የአየሩ ላይ ነብር፣የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና፣ የጠራራው ፀሐይ መብረቅ፣ ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ወልደ ሥላሴ፤ በተወለዱ በ75 ዓመታቸው መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቨርጂኒያ አሜሪካ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ጀኔራል ለገሠ፤ የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና የብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ስም፣ አኩሪ ገድልና ታሪክ፤ከመቃብር በላይ ውሎ፤ በትውልዱ ውስጥ ምንጊዜም ሲታወስና ሲዘከር ይኖራል፡፡ በመጨረሻም የጄኔራል ለገሠ ተፈራ የቀብር ሥነ-ሥርዓት፤ ለአንድነቷና ለነፃነቷ በተፋለሙላት፣ የአየር ክልሏንና ዳር ድንበሯን ባስከበሩላትና መከራዋን በተቀበሉላት በሚወዷት እናት አገራቸው በኢትዮጵያ እንዲፈፀም ለአደረጋችሁ እህት ወንድሞቻቸው እንዲሁም፣በሰሜን አሜሪካና በአገር ውስጥ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ፤ የቀድሞ የቀ.ኃ.ሥ. ሐረር ጦር አካዳሚና የዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሥራ ባልደረቦቻቸውና ጓደኞቻቸው በሙሉ፤ከልብ የመነጨ ምሥጋናቸውን በትህትና ያቀርባሉ፡፡ ኃያሉ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር፤ የሟቹን ነፍስ በገነት እንዲያሳርፍልንና ለቤተሰቦቻቸው፣ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ፤ብርታቱንና መጽናናትን እንዲሰጣቸው፣ሐዘኑንም የሐዘን ዳርቻ ያደርግላቸው ዘንድ እንፀልያለን፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ 2009ዓ.ም

 

 

 

 

  

Related Topics