የሳይበር ጥቃት ዲጂታል ምስጢራዊ የመረጃ ቋቶችን መፈልቀቅ ነው፡

የሳይበር ጥቃት ምንድን ነው?

 

 

የሳይበር ጥቃት ዲጂታል ምስጢራዊ የመረጃ ቋቶችን መፈልቀቅ ነው፡፡ የመረጃ ቋቶቹ ከተከፈቱ በኋላ የሚደርሱት/የሚሆኑት ነገሮች የጥቃቱን ደረጃና ዓይነት ልዩ ልዩ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የመረጃ ቋቶቹ መፈልቀቃቸው አንድም በውስጡ ያሉ መረጃዎችን፣ ለመስረቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ሌላ መረጃዎቹን የማጥፋት ተግባርም ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ መረጃውን ማዛባት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፕሮግራም ተደርገው አንድን ተግባር ለመፈጸም በተዘጋጁ ኮምፒዩተሮች ላይ የሚደርስ ከሆነ ተግባሩን ከማስተጓጎል ጀምሮ በንብረቶች ቁሶች ላይ ጉዳት እስከማስከተል ይደርሳል፡፡

 

የሳይበር ጥቃት በግለሰቦች ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉት ሁሉ በመንግሥታዊና ግለሰባዊ ድርጅቶችም ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ አንድን አካባቢ ወይም የአንድን ተቋም አጠቃላይ ኮምፒዩተሮች ወይም የመረጃና ግንኙነት አውታሮች ሊጎዳ ይችላል፡፡

 

የሳይበር ጥቃት በተለያዩ መንግሥታዊና ግለሰባዊ ተግባራት ላይ ባሉ ተቋማት ላይ ይደርሳሉ፡፡ አንዱ ከደኅንነት ስጋት በመነጨ በተገዳዳሪ ሀገራት፣ ወገኖች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶች አሉ፡፡ ለዚህ ተጠቃሽ የሚሆኑ የጥቃት ጥርጣሬዎችን ማንሣት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ እ.አ.አ. በ2007 ዓ.ም እሥራኤልና አሜሪካ የኢራንን የኒኩሊየር ማብላያ መሣሪያዎችን ተግባር ለማስተጓጎል እጅግ በተራቀቀ ዲጂታል ጦር መሣሪያ ለማጥቃት ሞክረው እንደነበር የኢራን መረጃ ምንጮች ያመለክቱ ነበር፡፡ ይህ የታወቀው ግን በ2010 ቢሆንም ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ይሰጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጥቃቱ በዋናነት ያተኮረውም የሥራ መሣሪያዎች እንዳይሠሩ የቁጥጥር ሥርዓቱን ማዛባት ላይ ነው፡፡

 

እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ነገር በአንድ የጀርመን የብረታብረት ኢንዱስትሪ ላይም ድርሷል፡፡ የድርጅቱ ወሳኝ ማሽን የቁጥጥር ሥርዓቱ ተዛብቶ ለፍንዳታ እንዲዳረግ ለማድረግ ባደረጉት ጥረትም ጉዳት ደርሷል፡፡ በሳይበር ጥቃት ጉዳት እንዲደርስባቸው ዒላማ የሚደረጉት የሥራ መሣሪያዎች ወይም የኢንዱስትሪ አካላት ወሳኝ የሥርዓት ቁጥጥር ያላቸው ክፍሎች ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በጥቃቱ የሚደርሰው ጉዳት የከፋና ትርጉም ያለው እንዲሆን ነው፡፡

 

ከዚህ አልፎም የኤሌክትሪክ ሥርጭት ጣቢያዎች፣ የውኃ ማጣሪያ ወይም ማከሚያ መሣሪዎች፣ ማዕከላት፣ ሆስፒታሎችና የፋይናንስ ተቋማት ወሳኝ የአሠራር ሥርዓቶችና መሣሪያዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ስጋት ነው፡፡

 

በአብዛኛው ዒላማ ወደተደረጉ የኢሜይል አድራሻዎች ከታመኑ ምንጮች የመጡ የሚመስሉ፣ ተንኮል ያለባቸው አባሪዎች (attachment) ያሉባቸውን መልዕክቶች በመላክ ወይም አደገኛ የሆኑ ወደ ኮምፒዩተር ለመሰብሰብ የተዘጋጁ (Downloedable) ዳውንሎድ ሊሆኑ የሚችሉ ሴረኛ ፋይሎች ያለባቸውን ጎጂ ድረገጾች እንዲጎበኙ በሚጋብዝ ሁኔታ ሲደርሱ እና ተቀባዩ ሲታለል ወይም ሲሳሳት፣ ሲጋለጥ የሥራ ሥርዓቱ ሁሉ በጥቃት አድራሹ እንዲበረበር፣እንዲጠፋ ወይም እንዲዛባ ይሆናል፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ጥቃት ከሚያደርስበት ተቋም፣ ድርጅት ወይም ኢንዱስትሪ ማሽን የየመረጃ ቴክኖሎጂ ደኅንነት ዕውቀትና ዝርዝር አተገባበር በላይ የረቀቀ እና ዘርዘር ያለ ዕውቀት ባለቤት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ከአሠራር ሂደቱ፣ ከቁጥጥር ሥርዓቱ በላይ የላቀ ዝርዝር የመረጃ ቴክኖሎጂ ዕውቀት ባለቤት መሆን አለበት፡፡

 

የሳይበር ጥቃት ከወታደራዊ ጉዳዮች አንጸር ሲታይ በወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያዎች ላይ የደኅንነት ቁጥጥር ማዕከላዊ ኮምፒዩተሮችና የመረጃ መረቦች ላይ የሚደርስ ጉዳት ሊኖር መቻሉ አንዱ ስጋት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዓየር ጥቃት መከላከያ መረጃ መረቦችን እንዲሁም ጥቅም ላይ ለማዋል የኮምፒዩተር ድጋፍ የሚፈልጉ የጦር መሣሪያዎች ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶች ይኖራሉ፡፡ ሀገራት ወይም ቡድኖች ዓለም አቀፉን የመረጃ መረብ በመጠቀም በጠላቶቻቸው የሚደርሱባቸው ጉዳቶች እንዳይኖሩ ቀድሞ ለመከላከል ወይም ደግሞ ይሄንኑ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ጥቃት የማድረስ ብቃትን ለማስተጓጎል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 

ከወታደራዊ ጉዳዮች አንጻር ሌላው የጥቃት መልክ ደግሞ በወታደራዊ ማዘዣዎች አካባቢ ጥርጣሬ፣ሽብር እና ሌሎች አድካሚ የመልሶ ማደራጀት ሥራዎችን የመሥራት ግዴታ ውስጥ የማስገባት ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ በማዘዣው ያሉ መረጃዎችን የወረሱ ለማስመሰል፣ ጥቃት ለማድረስም ብቃት ላይ እንደሆኑ ለማስመሰል የሚያስችሉ ዲጂታል ፍልቀቃዎችን (hacking) መፈጸም ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ባለፈው ሰሞን በኢራቅና በሶሪያ በአይሲስ ላይ የሚደረገውን የአየር ጥቃት የሚመራው የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣ ማዕከል የትዊተርና ዩቲዩብ ናቸው በተባሉ አካውንቶች ላይ የሳይበር ጥቃት ደርሷል መባሉን የአሜሪካ ፌዴራል የመረጃ ደህንነት ቢሮ ሲመረመር እንደነበር መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡

 

የአይሲስ ደጋፊዎች ነን የሚሉ የኢንተርኔት መረብ ጠላፊና ፈልቃቂዎች ባለፈው ሰሞን የአሜሪካንን የአየር ጥቃት ማዘዣ አካባቢ ማስፈራሪያ መልዕክቶች በማድረስ ያውኩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አልነበረም፡፡ በጊዜውም ከሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡት አስተያየቶች የሆኑት ነገሮች ተራ የሳይበር ውንብድና(cyber vandalism) ናቸው የሚል ነበር፡፡ በእነዚህ ወንበዴ በተባሉ አካላት ግን ደረሱ የተባሉት መልዕክቶች ‹‹እየመጣንባችሁ ነው ዞራችሁ እዩን፤ አይሲስ›› የሚል ነበር፡፡ በተጨማሪም የአሜሪካ የተወሰኑ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የስልክና የኢሜይል አድራሻዎች የያዙ ስለነበሩ በዋዛ መታየት የለባቸውም የሚሉ የሚመለከታቸው አካላት ነበሩ፡፡ የፔንታጎኑ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ስቴቭ ዋረን በበኩላቸው አንዳችም የመከላከያ ክፍሉ ኮምፒዩተር፣ የአሠራር ሥርዓት ወይም የግንኙነት መረብ ስለመሰበሩ ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል፡፡

 

የመንግሥታት ስጋት

 

የሳይበር ጦርነት በየጊዜው በየዓመቱ በዓለማችን ቁጥሩ እየጨመረ የመጣ የውጊያ ግንባር ሆኗል፡፡ እ.አ.አ. በ2006 የራሺያ ማፊያ ቡድን የሆነው አር ቢ ኤን የታወቀ ስርቆት ለመፈጸም ረቂቅ የውንብድና የመረጃ ቴክኖሎጂ መጠቀሙ ከተመዘገበ በኋላ ነገሩ በመንግሥታት ዘንድ በዋዛ የሚታይ አልነበረም፡፡ ይሄ ቡድን ዓላማውን ለማሳካት በዚህ ማዕበልም ለማጥለቅለቅ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተበከሉ ኢሜሎችን ይልኩ ነበር፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩም ኮምፒዩተሮች ሰለባ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ግን ዒላማ የሚያደርጉት ግለሰቦችን እንጂ መንግሥታዊ ተቋማትን አልነበረም፡፡

 

በ2008 ላይ ግን የአሜሪካው ዓለም አቀፉ የስፔስ ጣቢያ ናሳ ባለ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ላይ የሳይበር ዎርም (Cyber Worm) መገኘቱን አረጋግጧል፡፡ ይህ በሆነ ከሦስት ወራት በኋላ የፔንታጎን ኮምፒዩተሮች መነሻቸው ራሺያ እንደሆኑ በተገመቱ የዲጂታል ጥቃት አድራሾች እንደተጎዱ ተነገረ፡፡ ይህ ለአሜሪካ መንግሥት አንዱ ማንቂያ ደወል ነበር፡፡

 

እንዲሁ በ2008 ላይ የሕንድ ብሔራዊ ባንክ መነሻው ፓኪስታን የሆነ የሳበር ጥቃት የተሰነዘረበት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የባንኩን ድረገጽ ሥራ ቢያስተጓጉልም (ለጊዜው ተዘግቶ የነበረና ችግሩን ለመፍታት ጥረት የተደረገ ቢሆንም) የጠፋ መረጃ አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡ ይህ መንግሥታት የፋይናንስ ተቋሞቻቸው የጥቃት ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፍተኛ ግምት የተወሰደበት ነበር፡፡

 

በሌላ በኩል በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ማለትም በሀገራቱ ውስጥ በተተከሉ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ፣ ዜጎች በሌሎች ሀገራት በገነቧቸው ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንደሚኖሩ ስጋት አለ፡፡ ስለዚህም አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የሕግ ረቂቆችን ያዘጋጁ ሲሆን፤ ለሀገራቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ስጋት ተፈጥሯል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በኮሪያ በሚገኘው ሶኒ የአሜሪካውያን ኩባንያ ላይ ከደረሰው የዲጂታል ጥቃት ጋር በተያያዘ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኦባማ ‹‹እንደሀገር፣ እንደ ኢኮኖሚ፣ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ትልቅ ስጋት ተፈጥሯል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ስለዚህ ሀገራት አንደ ሀገር በደህንነት ተቋማት ላይ ተገዳዳሪዎቻቸው በግል ወይም በቡድን ከዚያም ሲያልፍ በጠላትነት ከተፈረጁ ሀገራት ሊቃጣ የሚችልባቸው ዲጅታል ጥቃት እንደሚኖር ግንዛቤ አለ፡፡

 

መንግሥታት ጉዳዩን አሳሳቢና አስቸጋሪ ያደረገባቸው ምክንያት የሳይበር ጥቃት ውስብስብ ባህርይ ነው፡፡ የሳይበር ጥቃት ውስብስብነት ዋነኛ ምክንያቶች ከዓለም አቀፉ የመረጃ መረብ ውስብስብነትና የተበታተነ መሆን ጋር ተያይዞ ኃላፊነት የሚወስድ እኔ ነኝ ባይ አካል ከሌለ በቀር ጥቃት አድራሹን ኃይል በውል ለመለየት አድካሚ መሆኑና ጥቃቱን ለመሰንዘር ምክንያት የሆኑ ምክንያቶችን በትክክል ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡ አንድን ውስን ጥቃትም የታወጀ ጦርነት ነው ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ አይሆንም፡፡

 

በእርግጥ ፖለቲካዊ ምክንያት ያላቸው እንደሆኑ የታሰቡ ሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለምሳሌ በ2008 ጆርጂያ በደቡባዊ ኦሴሺያ (South Ossetia) በነበራት ወታደራዊ መስፋፋት ምክንያት ራሺያ በጆርጂያ መንግሥት ድረገጽ ላይ ሳይበር ጥቃት ፈጽማለች የሚለው በብዙዎች ተቀባይነት ያገኘ ነበር፡፡ እንዲሁም በዚሁ ዓመት ቻይና በቲቤታውያን ላይ በፈጸመችው ጫና ምክንያት ሪፖርት የሠራው ሲ.ኤን.ኤን የቻይና ሀገር ወዳድ(Nationalist) በተባሉ ቡድኖች ሳይበር ጥቃት ተፈጽሞበታል፡፡ ይሄንን የሚመሳስሉ ፖለቲካዊ ምክንያት ያላቸው ጥቃቶች መኖራቸው አይካድም፡፡

 

አንዳንዶች ጥቃቶቹን የሳይበር ጦርነት(cyberwar) ቢሏቸውም በዚህ ዘመን ያለውን የሳይበር ጥቃት እንደ ጦርነት መቁጠር አግባብ አይሆንም የሚሉ አሉ፤ ይልቁንም የሳይበር ሽብር(cyberterrorism) በሚለው ይስማማሉ፡፡ ምክንያቱም የሳይበር ጥቃቶች ዓላሚና ታላሚ ሁልጊዜም ወታደራዊ ኃይል ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም የኢንተርኔት ገጽታዎች ተጋላጮች ናቸው፡፡ በኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች፣ በሲቪል ድርጅቶችና ተቋማት፣ በመረጃ መለዋወጫ በሆኑ መሣሪያዎችና ግንኙነት መረቦች፣ የግለሰቦችም ላፕቶፕና ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ የኤሌክትሪክና ቴሌኮሚዩኒኬሽን አውታሮችም ከሲቪል ዒላማዎች አንጻርም የሚታዩ ናቸው፡፡ የግሉ ሴክተርም ቢሆን በኢንዱስትሪው ዓለም ለሚደረገው ስምሪት ከፍተኛ ስጋት አለው፡፡ በዓለማችን በየጊዜው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ቫይረስን በመላክ የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች በኮርፖሬሽኖች ላይ እንደሚፈጸም እየተጠቀሰ ነው፡፡ እነዚህም ገንዘብ ከማግኘት ጋር በተያያዙ የሚሰነዘሩ ሲሆን፤ ሰለባዎቹ ፖለቲካዊ ትርጉም ወደ መስጠት ጉዳዩን እንዳይመሩት በመስጋት ይመስላል ሚዲያዎች ብዙም ትኩረት አይሰጡትም፡፡

 

የሀገራት የሳይበር ደህንነት ዋስትና

 

የሳይበር ደህንነት ስንል ሀገራት የሳይበር ጥቃት የመፈጸምና ጥቃቱን የመከላከል አቅም ማለታችን ነው፡፡ እስከ 120 የሚደርሱ ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ዓለም አቀፉን የመረጃ መረብ በመጠቀም የመንግሥታትን የኮምፒዩተር ሥርዐትና በፋይናንስ ገበያው ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ኢንተርኔትን እንደ ጦር መሣሪያ ሊጠቀሙ አዘጋጅተው እንደነበር የማካፌ የሳይበር ደህንነት ተቋም በ2007 እ.አ.አ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለምሳሌም ቻይና ከሀገሯ ውጪ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ያለውን የግሉን ሴክተር በመጠቀም እጅግ በርካታ የመከላከልና የማጥቃት አቅሟን እንደገነባች ይታመናል፡፡

 

የቻይና መንግሥት እ.አ.አ. ከ1995 ጀምሮ እስከ 2008 ድረስ ያለው ሲታይ ብቻ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የመረጃ ስርቆቶች (espionage) መፈጸሙን የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡ ይህም የሚደረገው በተበታተነ ሁኔታ በውጭ ያሉትን የተማሪዎቻቸውን፣ የቢዝነስ ሰዎቻቸውን፣ በውጭ ያሉ የዲያስፖራ የአይቲ መሐንዲሶቻቸውን፣ ዲፕሎማቶቻቸውን፣ ሳይንቲስቶቻቸውን በመጠቀም የሚፈጽሙት ነው፡፡ በአውሮፓ የኢንዱስትሪው ዓለምም ለዚሁ ዓላማ የሠለጠኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላዮች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ለምሳሌ እ.አ.አ. በ2007 አንድ የራሺያ ባለሥልጣን የራሺያን የሮኬትና የስፔስ ቴክኖሎጂ አደረጃጀትን በዚሁ መንገድ ለቻይና ሰጥቷል በመባሉ 11 ዓመት እንደተፈረደበት ይታወቃል፡፡

 

በተመሳሳይ የአሜሪካ የኤሮ እስፔስ ምህንድስና፣ ከፍተኛ ስልታዊ ተግባር ያላቸው ኮምፒዩተሮች፣ የኒኩሊየር ጦር መሣሪያ ዲዛይኖች፣ ለታይዋን የሚሸጡ ጦር መሣሪያዎች ዓይነትና መጠን ዝርዝሮች፣ የክሩዝ ሚሳኤሎች መሠረታዊ መረጃ ወዘተ የዚህ የቻይና ስውር የሳይበር ጥቃት ዒላማዎች መሆናቸው ይታመናል፡፡ ቻይና በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በካናዳ፣ በፈረንሳይ፣ በራሺያ እና በሕንድ የመንግሥትና የግል ተቋማት ለደረሱ የሳይበር ጥቃቶች ኃላፊነት እንድትወስድ ብዙ ጊዜ ተጎትጉታለች፡፡ ይሁን እንጂ ቻይና በዚህ መሰል የሳይበር የስለላ ዘመቻ እጇ እንደሌለበት ደጋግማ ትገልጻለች፡፡ እንደውም የቻይና መንግሥት ለተደጋጋሚ የሳይበር ጥቃት እየተጋለጠ መሆኑን በመግለጽ የሚዳኙ ሕጎች መዘጋጀት እንዳለባቸው እየወተወተ ቆይቷል፡፡

 

በዚህ ጉዳይ የተንታኞች እይታ እንደውም ቻይና እያስመዘበች ያለውን የሳይበር እና ወታደራዊ ምህንድስና ያሳደገችው ከውጭ በምታገኘው ዕውቀትና መረጃ ነው ይላሉ፡፡ አሁን ያለውንም ስፔስን መሠረት ያደረገ የደህንነት ቁጥጥር፣ የስለላ መረጃ ስብሰባ፣ ፀረ ራዳርና ሳተላይት ሥርዓቶችን ያዳበረችው በዚሁ መንገድ ነው የሚለውን ብዙዎች በትንታኔያቸው ያካትታሉ፡፡ ወታደራዊ ኃይሏንም ይሄንን የሳይበር አቅም ተንተርሶ የሚመጣን ተገዳዳሪ ማንበርከክ በሚያስችል ደረጃ በሳይበር ቴክኖሎጂ ላይ የምትሰጠው ሠፊ ሥልጠና ወደፊት የሳይበር ቀዝቃዛ ጦርነትን በዓለም ለማምጣት ምክንያት እንዳትሆን ብለውም የሚሰጉ አሉ፡፡

 

ይህ አካሄድ ግን በቻይና የሚገደብ አይደለም፡፡ አሁን ደግሞ ለዓለማችን ልዕለ ኃያል ሀገር አሜሪካ በዚህ መስክም ያላትን አቅም ማሳደግ ካልቻለች ፈታኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥማት እየተረዳች ነው፡፡ ስለዚህ ሳይበር ጥቃትን ለሌላ የጦር ጥቃት እንደ መንደርደሪያ ማማ አድርጎ የማደራጀት ስልት እየተከተለች መሆኑ ታውቋል፡፡ ከ2013 በኋላም የሳይበር ጥቃት ከአልቃይዳ ወይም ሽብር በላይ ለአሜሪካ ስጋት መሆኑ በአሜሪካ የመረጃ ባለሥልጣናት ከግንዛቤ ገብቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢራን በዓለማችን በሳይበር ወታደራዊ ጥቃት የመፈጸምና የመከላከል አቅም በደረጃ ሁለተኛ ሆና መገኘቷ ለአሜሪካ ራስ ምታት ነበር፡፡

 

በአሜሪካ እስከ 2010 የኮምፒዩተር ደህንነት ስፔሻሊስቶች ቁጥር ከ1000 አይበልጥም ነበር፡፡ አሜሪካ ግን በዚህ መስክ ያሏትን ስፔሻሊስቶች ቁጥር ከ20,000 እስከ 30,000 እንዲደርስ እየሠራች ነው፡፡ በኅዳር 2014 ላይ በኮሪያ በሚገኘው ሶኒ የአሜሪካውያን ኩባንያ የደረሰው ሳይበር ጥቃት አሁን ደግሞ ሌላው ማንቂያ ደወል ሆኗል፡፡

 

ጀርመንም በበኩሏ ኤድዋርድ ስኖውደን ስለአሜሪካ የሳይበር ደህንነት ቁጥጥር በተመለከተ መረጃዎችን ከሰጠ በኋላ በሳይበር ደህንነት ጉዳይ አዲስ ፖሊሲ እየተከተለች መሆኗ ታውቋል፡፡ ለዚሁ ዓላማ ያዘጋጀቻቸውም አዲስ የሳይበር መከላከያ ተቋም (ጣቢያ) አሉ፡፡ የሚባሉ የሰሉ የሳይበር ጥቃት አድራሽ ባለሙያዎችን ለመቅጠር እንደምትፈልግ በስለላ ተቋሟ አማካኝነት እ.አ.አ. በ2013 ይፋ አድርጋ ነበር፡፡ በጊዜው የጀርመን መንግሥት መነሻቸው ቻይና የሆኑ አምስት ያህል ጥቃቶች በየቀኑ ይሰነዘሩ እንደነበር መታዘቡን ገልጿል፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ይመድብ የነበረውን በጀት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩም ተሰምቷል፡፡

 

ሕንድም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ተግባራዊ ባታደርግም ወደዚያ የሚያደርሱ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ዘግይታም ቢሆን መውሰድ ጀምራለች፡፡ በተለይ በ2012 ሐምሌ ወር ላይ በ12,000 ያህል የመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናትን ጨምሮ የግለሰቦች የኢሜይል አካውንቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህም ሕንድ ‹‹የአይቲና የሶፍትዌር ማህደር›› የተባለችበትን አቅሟን የፈተነና አስደንጋጭም ጥቃት በመሆኑ ከወዲሁ ጠንካራ ፖሊሲና የሳይበር ደኅንነት ተቋማትን እየገነባች እንድትሄድ እያነቃት ነው፡፡ ሕንድ በተለይም ከባላንጣዋ ከፓኪስታን ሊሰነዘሩ የሚችሉ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ከመከላከል አንጻር መበለጥ አትፈልግም፡፡

 

ሌላዋ የሳይበር ጥቃት የሚያሳስባት ሀገር ኢራን ነች፡፡ በተለይም ባለፉት ጊዜያት በአሜሪካና በእሥራኤል ጣምራ የሳይበር ጥቃት ሳይፈጸም አይቀርም የተባለ የሳይበር ዎርም በመልቀቅ በኒኩሊየር ማብላያ ጣቢያዎቿ አካባቢ ባሉ 60ሺ የሚደርሱ ኮምፒዩተሮች ለጥቃት መጋለጣቸው በኢራን መንግሥት የተረጋገጠ ሲሆን፤ የደረሰው ጉዳት ግን ትርጉም ያለው አለመሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ አሁን ግን ኢራን የሳይበር ደህንነትና የማጥቃት አቅም በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆኗ ይነገራል፡፡ እንደውም በ2012 ላይ ኢራን የሳይበር ጥቃቶችን በአሜሪካ፣ በእሥራኤልና በአረብ ገልፍ ሀገሮች ላይ መፈጸሟ ቢነገርም ኢራን ግን ኃላፊነት አልወሰደችም፡፡

 

በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለው ፍጥጫ ደግሞ ሁለቱን ባላንጣ ኮሪያዎች የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ላይ በእጅጉ የመጠቀ ፖሊሲና አደረጃጀት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ሰሜን ኮሪያ በዚህ በኩል ቀደም ያለ እርምጃ ላይ የደረሰች ሲሆን፤ ራስን በመከላከል ረገድ አሉ የሚባሉ ባለሙያዎቿን አሰማርታ ትገኛለች፡፡ የሠለጠኑ 3000 የሚደርሱ የዲጂታል ምስጢሮችን ፈልቃቂ ኃይሎች እንዳላት ይገለጻል፡፡ እንደውም በመጋቢት ወር 2013 ላይ ሠላሳ ሺሕ የሚደርሱ ኮምፒዩተሮችን ያወከ ጥቃት በደቡብ ኮሪያ ላይ ሲደርስ KBS, YTN and MBC የተባሉት የመገናኛ ብዙኃን ጣቢያዎች ሰለባ ሲሆኑ ሰሜን ኮሪያ በዚህ ረገድ የደረሰችበትን አቅም ጠቋሚ ሆኗል ይባላል፡፡ ስለዚህ ደቡብ ኮሪያም በዚያ አንጻር የሳይበር ደህንነት ላይ እየሠራች መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን በየዲጂታል መረጃዎችና ምስጢሮችን ፈልቃቂና ጥቃት አድራሽ የሠለጠነ የሰው ኃይሏ ከ400 እንደማይበልጥ ይነገራል፡፡ ስለዚህም ለጊዜው ከአሜሪካ ጋር የሚደረጉ ወታደራዊ የጋራ ልምምዶች ለሰሜን ኮሪያ ማስፈራሪያ እና ማስጠንቀቂያ ሆነው እየተወሰዱ ነው፡፡

 

ማጠቃለያ

 

የሳይበር ጥቃት ጉዳይ አሁን የዓለማችን ወሳኝ የደህንነት ጉዳይ ሆኗል፡፡ በመሆኑም መንግሥታትም ሆኑ ግለሰቦች እንዲሁም ከመረጃ ቴክኖሎጂ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት እየሰጡ ነው፡፡ ዘመናችን ደግሞ ተግባራትን ከዚህ ቴክኖሎጂ ውጪ ለመፈጸም የሚሻ አይደለም፤ አይሆንምም፡፡ ነገር ግን የግለሰቦችንም ሆነ የሀገራትን ድካም፣ ጥረት፣ ምስጢር ሁሉ መና የሚያስቀር የሳይበር ጥቃት ስጋት ሆኖ መገኘቱ ደግሞ የዓለማችን ወቅታዊ ጉዳይ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ ዓለም እንዲህ ያለውን ስጋት ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ፣ የቴክኖሎጂ ልህቀት ምላሽ ፖለቲካዊ መፍትሔን እየጠበቀ ነው፡፡

 

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

 

  

Related Topics