የዝነኛዋ ጄኒፈር ሎፔዝ ስም ሲነሳ ከዝናዋ ጋር ብዙ ወንዶችን እያገባች እ

ጄኒፈር ሎፔዝና የትዳር ሕይወቷ

 

 Image result for jennifer lopez

 

የዝነኛዋ ጄኒፈር ሎፔዝ ስም ሲነሳ ከዝናዋ ጋር ብዙ ወንዶችን እያገባች እንደፈታች ይነገራል። ስድስት ጊዜ አግብታ ስድስት ጊዜ ፈታለች። የዓለም የመገናኛ ብዙኃንም ባገባችና በፈታች ቁጥር ሰፊ ሽፋን ይሰጧታል። ባለፈው ነሐሴ ወር እንኳን ካስፔር ስማርት ከተባለው ባሏ ጋር ስትፋታ ሰፊ መነጋገሪያ ሆና ነበር። አንዴ ሲፋቱ አንዴ ሲጋቡ የቆዩት ሁለቱ ዝነኞች ተመልሰው ይጋባሉ የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ታስቦ ነበር። ዳሩ ግን ከሰሞኑ ደግሞ ኢሜሬት 24/7 እንዳስነበበው ጄኒፈር ሎፔዝ ዳግመኛ እንደማታገባው ተናግራለች። አሁንስ ማንን ታገባ ይሆን? የሚለው የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ሎፔዝ የ47 ዓመት ሴት ስትሆን ይህ አንዴ ፈታሁህ ሌላ ጊዜ አገባሁህ የምትለው ባሏ ግን ገና የ29 ዓመት ወጣት ነው።

በፈረንጆቹ ሐምሌ 24 ቀን 1969 የተወለደችው አሜሪካዊት ጄኒፈር ሎፔዝ በዘፋኝነት፣ በተዋናይነት፣ በዳንስ፣ በፋሽን ዲዛይነርና በፕሮዲውሰርነት የዓለም ዝነኛ ሰው ሆናለች።በተለይም ትንሿ ልጄ(My Little Girl) የተሰኘውን ፊልም ላይ ከተወነች በኋላ በፊልም ዓለም ዝነኛ ለመሆን በቅታለች።

ሎፔዝ ገና የአምስት ዓመት ሕጻን እያለች ዘፈንና ዳንስ ጀመረች። ቤተሰቦቿም እሷንና ሁለት እህቶቿን ጨምሮ ቤት ውስጥ እርስበርስ እየተያዩ እንዲዘፍኑና እንዲደንሱ ያደርጉ ነበር። ሎፔዝ በትምህርት ቤት እያለች ከዳንስና ከዘፈን በተጨማሪም የጂምናስቲክና አትሌቲክስ ስፖርተኛ ነበረች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከአካዳሚ ትምህርቱ ይልቅ የሙዚቃና የዳንስ ነገር አመዘነባት።

ገና የ15 ዓመት ልጅ እያለች ዴቪድ ክሩዝ ከተባለ ወጣት ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመረች። እዚያው ትምህርት ቤት እያለችም ፍላጎቷ ፊልም ላይ መተወን እንደሆነ ለቤተሰቦቿ ተናገረች። ቤተሰቦቿ ግን በፍፁም ይህ ሊሆን አይችልም አሏት። ሀሳባቸው ያልተስማማት ሎፔዝ የቤተሰቦቿን ቤት ለቃ ሕይወቷን በውጭ አደረገች። ታዋቂነቷ እየጨመረ ስለመጣ በብዙ ፊልሞች እንድትተውን ተመረጠች።

ጄኒፈር ሎፔዝ የዓለምን ቀልብ እንድትስብ የሚያደርጋት ሌላው የትዳሯ ነገር ነው። በየካቲት 1998 ኦጃን ኗ የተባለ አንድ የኩባ አስተናጋጅ አገባች። ከዚህ ሰው ጋር ብዙም ልትዘልቅ አልቻለችም። በመጨረሻ ግን ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ አስገባት። በጫጉላ ሽርሽር ጊዜ ያደረጉትን ነገር ሁሉ በመጽሐፍ ሊያሳትም ተነሳ። የሚያደርጉትን የወሲብ ግንኙነት በድብቅ ካሜራ ቀርፆ ስለነበር በቪዲዮ እንደሚለቀው አስፈራራት። በኋላም በፍርድ ቤት ከሳ አስከለከለችው።

ኦጃን ኗን ከፈታች በኋላ ደግሞ ወዲያውኑ ክሩስ ጁድ የተባለውን ዳንሰኛ አገባች። ከክሩስ ጁድ ጋር የነበራት የባልና ሚስትነት ጊዜ ስምንት ወር ብቻ ነበር። ክሩስ ጁድን እንደፈታች ቤን አፍሌክ የተባለውን የፊልም ዳይሬክተርና ተዋናይ አገባች። ጄኒፈር የሚለውንና ቤን የሚለውን ስም በማጣመርም ቤኒፈር የሚል ስም ተሰጣቸው። ከዚህም ጋር ሳትዘልቅ እንደልማዷ ፈታችው። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ማርክ አንቶኒን አገባች። ከማርክ አንቶኒ ጋር በነበራት ግንኙነት ወቅት የተቀረፁ ቪዲዮዎች እየተሰረቁ መሸጥ ጀመሩ። ጄኒፈር ሎፔዝ ከነበሯት ባሎች ሁሉ ረዘም ላለ ጊዜ የቆየችው ከማርክ አንቶኒ ጋር እንደነበርም ይነገራል። ገና በጋብቻቸው መጀመሪያም ከአንተ ልጅ እወልዳለሁ እንዳለችው በመሰማቱ የሎፔዝ ሆድ ማርገዝ አለማርገዙን ለማየት አድናቂዎቿ ሁሉ በጉጉት ይከታተሉ ጀመር።

እንደተጠበቀውም የጄኒፈር ሎፔዝ ሆድ እርግዝናን ማሳየት ጀመረ። ማርገዟን ሲሰሙ አባቷ መንታ መውለድ የዘሯ ስለሆነ መንታ ትወልዳለች አለ። እንደተባለውም አንዲት ሴት ልጅና አንድ ወንድ ልጅ መንታ ወለደች። በዚያን ሰሞንም የዓለም ጋዜጦችና መጽሔቶች የፎቶ ሽፋናቸው ይህ ሆነ። ከማርክ አንቶኒ ጋር ባላት የአራት ዓመት ቆይታ አሁን ፀንታ መኖር ጀመረች ሲባል እንደፈታችው አሳወቀች። እነሆ አሁን ደግሞ ካስፔር ስማርትን አንዴ አገባሁት አንዴ ፈታሁት እያለች ትገኛለች።

 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ 2009

 

  

Related Topics