ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ኮሌጅ በስዕል ትምህርት በ1980 ዓ.ም ተ

ሰዓሊው የአዲስ አድማስ ወዳጅ!

 

ሰዓሊው የአዲስ አድማስ ወዳጅ!

 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ኮሌጅ በስዕል ትምህርት በ1980 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ በአሁን ሰዓት የራሱን ስቱዲዮ አቋቁሞ የተለያዩ የስዕል ሥራዎቹን እየሰራ ሲሆን በአፍሪካ ግብፅን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የስዕል አውደርዕዮችን አቅርቧል፡፡ የአዲስ አድማስ ወዳጅ የሆነው ሠዓሊ ዘርአዳዊት አባተ፤ ጋዜጣችን 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር የማስታወሻ ስዕል በስጦታ ያበረከተ ሲሆን ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ በተከበረው የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በዓል ዝግጅት ላይም ተጨማሪ የስዕል ስጦታ አበርክቷል፡፡ ሰዓሊው ከጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጓል፡፡

 

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር እንዴት ተዋወቅህ?

ከአዲስ አድማስ ጋር የተዋወቅሁት በ1998 ዓ.ም በፀጋዬ ገ/መድህን ግጥሞች ላይ “እሳት ወይ አበባ” በሚል ርዕስ ሂልተን ሆቴል ኤግዚቢሽን ሳቀርብ አዲስ አድማስ እንዲዘግብልኝ ጠይቄ በሙሉ ፈቃደኝነት ጥሩ የሆነ ዘገባ ባወጣልኝ ጊዜ ነበር፡፡  ይህ አንዱ የቅርበታችንና የትውውቃችን መሰረት ቢሆንም እኔ ከድሮም ጋዜጣውን እወደዋለሁ፡፡ የሥነ ፅሁፍ አፍቃሪ  ስለሆንኩ ጋዜጣውን በጣም ነው የማደንቀው፡፡

የስዕል ስራዎችህን ለጋዜጣው በስጦታ ለማበርከት ያነሳሳህ ምንድን ነው?

የስዕል ስራዎቼን ለማበርከት የፈለግሁት ለሌሎች ሰአሊዎች አርአያ ለመሆን ነው፡፡ እንደዚህ ላሉ ሃገሪቷን በጥሩ ስሜት ለሚያገለግሉ የስነ ጥበብ አክባሪ የጋዜጣ ድርጅቶች የስዕል ስራቸውን ቢያበረክቱ መልካም ነው፡፡ እኔም ሁልጊዜ ከመሸጥ ማበርከትም መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የ10ኛ ዓመቱ ላይ ያበረከትኩት አድናቆቴን ለመግለፅ ነው፡፡ አሁን 15ኛ አመት ላይ ደግሞ ከአድናቆትም በላይ ለሰአሊዎች አርአያ ለመሆን ነው፡፡ በአዳራሹ ውስጥ በጣም ብዙ ሰአሊዎች ነበሩ፡፡ ስዕል ላበረክት ነው ስላቸው እየቀለዱብኝ፤ “አንተ ከዚህ ጋዜጣ ጋር የተለየ ግንኙነት ነው ያለህ” እያሉ ነበር፤ ነገር ግን ጥሩ ስሜት እንደጫርኩባቸው ይገባኛል፡፡ በ15ኛ ዓመቱ ላይ ይህን የስዕል ስራዬን በማበርከቴም ደስታ ይሰማኛል፡፡ ለ20ኛ ዓመቱም እድሜና ጤና ከሰጠኝ ማበርከቴ አይቀርም፡፡ አዲስ አድማስ በአሉን ባከበረ ቁጥር የስዕል ስጦታውን አላቋርጥም፤ እቀጥላለሁ፡፡

ከአዲስ አድማስ የትኞቹ አምዶች ይበልጥ ይስቡሃል?

አንዱ ኪነ ጥበብ ላይ አትኩሮ የሚሰራቸው ዘገባዎቹ ሲሆን ቀደም ሲል ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሚል አምድ የሚያቀርባቸው ጥሩ ፅሁፎች ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በየሳምንቱ የሚወጡት ትናንሽ ግጥሞች ናቸው፡፡ ሌላው በጣም የማደንቀው ገጣሚ ነቢይ የሚፅፈውን ርዕሰ አንቀፅ ነው፡፡ በተረት አዋዝቶ ስለሚፅፍ ትላልቅ መልእክት አላቸው፡፡ ከ10ኛው አመት ጀምሮ የተፃፉትን ርዕሰ አንቀፆች በሙሉ ኮምፒውተሬ ውስጥ ፋይል አድርጌ አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ በታሪካዊ እውነቶች ላይ የተፃፉ አንዳንድ የጋዜጣው ፅሁፎች ለስዕሎቼ መነሻ ሆነውኛል፡፡

ምን አይነት የአሳሳል ዘይቤ ነው የምትከተለው?

 ሪያሊስቲክ ላይ ነው የማተኩረው ግን አብስትራክትም መስራት ጀምሬአለሁ፡፡ ሮማንቲዝምም ደስ ይለኛል፤ ላንድ ስኬፕ ደግሞ በጣም እወዳለሁ፡፡

የስዕል ስራዎችህን ከኢትዮጵያ ውጪ ያቀረብክበት አጋጣሚ አለ?

እንግዲህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርት ስኩል በ1981 ዓ.ም በማዕረግ ነው የተመረቅሁት፡፡ የመመረቂያ ስራዬ የሚያዚያ 27 የድል ቀን ማስታወሻ ስዕል ነው፡፡ ይህን ስዕል ብዙ ጊዜ በኤግዚቢሽን አቅርቤዋለሁ፡፡ በጊዜው አድናቆት የተቸረው ነው፤ አሁን አርት ስኩል ነው ያለው፡፡ ኮፒው ደግሞ አርበኞች ማህበርን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ይገኛል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ በስዕል ስራ ላይ የቆየሁ ሲሆን በግብፅ፣ በናይሮቢ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ኤግዚቢሽኖችን አሳይቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ አውሮፓ አቀናለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለጋዜጣው የምትሰጠው አስተያየት ይኖራል?

የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በአል በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ በተረፈ ጋዜጣዋ በየጊዜው መሻሻል አለባት፡፡ መጽሄትም ብትጀምሩ ጥሩ ነው፡፡ ለጋዜጣው አምዶች ቢጨመሩ… በተለይ ያልተነኩና አዳዲስ ጉዳዮችን የሚዳስሱ አምዶች መኖር አለባቸው፡፡

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ