ዝንጅብል በርካታ የጤና በረከቶች እንዳሉት ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው፡

ዝንጅብል እንዳይጠቀሙ የሚመከሩ ሰዎች

 

ዝንጅብል እንዳይጠቀሙ የሚመከሩ ሰዎች

 

ዝንጅብል በርካታ የጤና በረከቶች እንዳሉት ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው፡፡

ከጡንቻ እና አጥንት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ህመሞችን ለማስታገስ እና በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ዝንጅብል፥ የማስመለስ፣ የልብ ህመም፣ ራስ ምታት፣ ጉንፋን፣ ተቅማጥ እና የወር አበባ ይዟቸው የሚመጡ የህመም ስሜቶችን ለማስታገስም አይነተኛ መፍትሄ ነው።

በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠንን እና ኮሊስትሮልን ለመቀነስ እንዲሁም የካንሰር ህዋሳት እድገትን ለመግታትም ያግዛል፤ ዝንጅብል። 

በርካታ የጤና እክሎችን ለመከላከል የሚውለው ዝንጅብል አለማቀፍ መድሃኒት የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል።

በያዘው ፀረ ባክቴሪያ ንጥረ ነገርም በረጅም አመታት ለህክምና አገልግሎት ውሏል።

ይሁን እንጂ ዝንጅብል ለሁሉም አይነት የጤና ችግር መፍትሄ ይሆናል ማለት አይደለም።

ዝንጅብል ቢወስዱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝንባቸው የሚችሉ ሰዎችም እንዳሉ መረዳት ተገቢ ነው።

እናም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አራት ነጥቦችን በአንክሮ ብንመለከት መልካም ነው፡፡

 

ነፍሰ ጡር ሴት

ዝንጅብል በውስጡ የያዘው ሀይለኛ አነቃቂ ንጥረ ነገር ከመደበኛው ጊዜ አስቀድሞ መውለድን ሊያስከትል ይችላል።

በተለይም መውለጃዋ የተቃረበ እንስት ዝንጅብል ባትወስድ ይመከራል።

 

ክብደት መጨመር የሚፈልጉ ሰዎች

ዝንጅብል ክብደት መቀነስ ለሚፈልጉ ሰዎች ተመራጭ ነው።

በአንፃሩ ክብደት መጨመር ለሚፈልጉ ሰዎች ምኞታቸውን ገደል የሚከት ነው ተብሏል።

ዝንጅብል ከሻይ ጋር ቀላቅለንም ሆነ በሌላ መንገድ ስንወስድ የጥጋብ ስሜት እንዲሰማን ከማድረጉም ባለፈ በሰውነታችን ውስጥ የተከማቸ ስብን ለማቅለጥ ያግዛል።

በመሆኑም ክብደትዎን ለመጨመር ከፈለጉ ከዝንጅብል ራቁ ተብላችኋል።

 

ከደም ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ሰዎች

ዝንጅብል የደም ዝውውርን ያፋጥናል።

የደም ማነስ፣ የደም መፍሰስ ችግር (ሄሞፊሊያ)፣ የደም መርጋት፣ የተለያዩ የደም ካንሰሮች (ሊኩሚያ፣ ሊምፎማ እና ሚይሎማ) ያሉባቸው ሰዎች ዝንጅብል ቢጠቀሙ የተለየ ተፅዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል፡፡

 

 

የደም ግፊት እና ስኳር ህመምተኞች

የደም ግፊት አልያም የስኳር ህመምን ለመቆጣጠር መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎችም ዝንጅብል በጭራሽ መውሰድ የለባቸውም ተብሏል።

ይህም ዝንጅብል የህክምና ክትትሉን ሊያዛባባቸው ስለሚችል ነው።

በተለይ ከፍተኛ የደም ግፊትን እና ደም መርጋትን ለመቀነስ ከሚወሰዱ መድሃኒቶች ጋር ዝንጅብል አብሮ መውሰድ አደገኛ መሆኑን ባለሙዎች ይናገራሉ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ከጤናቸው እና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ዝንጅብል ባይወስዱ የሚመከሩ ሰዎች ስለሚኖሩ የህክምና ባለሙዎችን ማማከሩ የተሻለ ነው እንላለን፡፡

 

 

ምንጭ፦ www.fitbodycenter.com/

 

 

 

  

Related Topics