የኮምፒውተር ቫይረሶች በርካታ ጊዜ ኮምፒውተራችን ተግባሩን እንዳያከናው

የምንጊዜም አደገኛ የኮምፒውተር ቫይረሶች

 

የኮምፒውተር ቫይረሶች በርካታ ጊዜ ኮምፒውተራችን ተግባሩን እንዳያከናውን እክል ይፈጥሩበታል። የኮምፒውተር ቫይረሶች በሚያጋጥመን ጊዜም ኮምፒተራችንን ከቫይረሱ ነጻ ለማድረግ አንቲ ቫይረሶችን ለመጫን የምንገደድ ሲሆን፥ ኮምፒውተራችን ላይ ያለውን ቫይረስ ለማጽዳት ስንል መረጃዎቻችን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የምንገደድበት ጊዜም አለ። አንዳንዴ በኮምፒውተራችን ላይ የጫነው አንቲ ቫይረስ በኮምፒውተራችን ላይ ያሉትን ቫይረሶች መቆጣጠር ያቅተውና ቫይረሶቹ ኮምፒውተሩን ስራ እንዲያቆም ሊያደርጉ ይችላሉ።

1. ማይ ዱም /My Doom/

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 መፈጠሩ የሚነገረው ማይ ዱም የኮምፒውተር ቫይረስ እንደሌሎች ቫይረሶች ሁሉ በኢሜይል አማካኝነት ነው የሚሰራጨው። ማይ ዱም የኮምፒውተር ቫይረስ ከ2 ሚሊየን በላይ ኮምፒውተሮችን ማጥቃቱም ይነገራል። ማይ ዶም በኢሜይላችን ላይ “Mail Transaction Failed.” የሚል መልእክት የሚያስቀምጥልን ሲሆን፥ ይህንን ለመክፈት በምንጫነው ጊዜ እራሱን በኮምፒውተራችን ውስጥ በማሰራጨት ኮምፒውተራችን ላይ ጥቃት ይፈጽማል።በዚህ ቫይረስ እስካሁን ከ380 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኪሳራ መድረሱ ነው የሚነገረው።

2.አይ ላቭ ዩ /I LOVE YOU/

አይ ላቭ ዩ /I LOVE YOU/ በመባል የሚታወቀው ቫይረስ ኮምፒተሮችን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ለማድረግ ታስቦ ነው የተሰራው። እስካሁንም በዓለማችን ላይ ካሉት ኮምፒውተሮች ማለትም ከኢንተርኔታ ጋር ግንኙነት ካላቸው ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት በቫይረሱ ምክንያት ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ይነገራል። ይህ ውድመት በገንዘብ ሲሰላም ወደ 10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚጠጋ ጥናቱ ያመለክታል። ቫይረሱ በኢሜይል አማካኝነት የሚሰራጭ ነው። በኢሜይላችን ላይም Love-Letter-For-You.TXT.vbs. የሚል መልዕክት የሚመጣልን ሲሆን፥ መልእክቱን በምንከፍትብት ጊዜም ወዲያውኑ ወደ ኮምፒውተራችን ራሱን በማሰራጨት ነው ጉዳቱን የሚያደርሰው። በተጨማሪም ኢሜይሉን ለመክፈት ክሊክ በምናደርግበት ጊዜ ከዚህ ቀደም ኢሜይል ወደምንላላካቸው ወደ 50 ለሚጠጉ ሰዎች ወዲያውኑ ራሱን ሊያሰራጭ ይችላል። ስለዚህም እንዲህ አይነት መልዕክት በማናውቀው አድራሻ ሲመጣልን ከመክፈት ብንቆጠብ መልካም ነው።

3. ሜሊሳ /Melissa/

ሜሊሳ የኮምፒውተር ቫይረስ እንደ አውሮፓውያኑ በ1999 ላይ ነበር ዴቪድ ኤል ሜሊሳ በሚል ግለሰብ የተፈጠረው። ሜሊሳ ቫይረስም ልክ እንደ “አይ ላቭ ዩ” ቫይረስ በኢሜይል አማካኝነት የሚሰራጭ ሲሆን፥ በኢሜይል አድራሻችን የሚላከውን “list.doc.” የሚል መልእክት ስንከፍት በቀላሉ ወደ ኮምፒውተራችን በመሰራጨት እክል ሊፈጥርብን ይችላል። የቫይረሱ ፈጣሪ ዴቪድ ኤል ሜሊሳ በኤፍ ቢ አይ ቁጥጥር ስር ውሎም ለዚህ ስራው 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተቀጥቶ ነበር።

4.ኮድ ሬድ /Code Red/

ኮድ ሬድ ከሌሎች ቫይረሶች ለየት የሚያደርገው እንደ ሌሎቹ በኢሜይል ሳይሆን ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ኮምፒውተሮች በኢንተርኔት መስመሩ አማካኝት በማጥቃቱ ነው። ይህ ቫይረስ ወደ ኮምፒውተራችን ሲመጣም “Hacked by Chinese!” የሚል ጽሁፍ በኮምፒውተራችን ስክሪን ላይ የሚያመጣልን ሲሆን፥ ይህንን ለማጣራት በምንከፍትበት ጊዜም ኮምፒውተራችንን ሙሉ በሙሉ ያጠቃል። ኮድ ሬድ በዓለም ዙሪያ ካሉ ኮምፒውተሮች 1 ሚሊየን ያክሉን ያጠቃ ሲሆን፥ በዚህም 2 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ አስከትሏል። በዚህ ቫይረስ ምክንያትም የአሜሪካውን ኋይት ሃውስ ጨምሮ ከ400 ሺህ በላይ የኢንተርኔት ሰርቨሮች ለመዘጋት ተገደው ነበር።

5. ሳሰር /Sasser/

ሳሰር እንደ አውሮፓውያኑ በ2004 ላይ የተገኘ የኮምፒውተር ቫይረስ ሲሆን፥ የኮምፒውተራችን ፍጥነት እንዲቀንስ እና እየሰራ በመሃል ስራ እንዲያቆም / ክራሽ/ የሚያደርግ ቫይረስ ነው፡ በዚህ ቫይረስ የተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኮምፒውተሮች ሲጠቁ ይስተዋላል።

ምንጭ፡-alifradio

 

  

Related Topics