ረጅም የቀን እንቅልፍ (ሸለብታ) ለስኳር በሽታ መጋለጥን ሊያመላክት ይችላ

ረጅም የቀን እንቅልፍ (ሸለብታ) ለስኳር በሽታ መጋለጥን ሊያመላክት ይችላል ተባለ

 

 

 

ከአንድ ስአት በላይ የሚወሰድ የቀን ሸለብታ (ናፕ) የታይፕ 2 የስኳር በሽታ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊሆን እንደሚችል የጃፓን ተመራማሪዎች ተናግረዋል።

አጥኚዎቹ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት ነው የረጅም ሸለብታ (ናፕ) እና የስኳር በሽታ ዝምድናን ለማረጋገጥ የሞከሩት።

የብሪታንያ ተመራማሪዎችም ለረጅም ጊዜ የቆየ የጤና እክል ያለባቸውና የስኳር ህመምተኞች ቀን ላይ የድካም ስሜት እንደሚሰማቸው ከዚህ ቀደም ባደረጉት ጥናት አረጋግጠዋል።

ነገር ግን ሸለብታ ለስኳር በሽታ ተጋላጭነት መንስኤ መሆኑን ማረጋገጥ አልቻልንም ብለው እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።

በቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተደረገውና በሙኒክ በተካሄደው የአውሮፓ የስኳር በሽታ ጥናት ማህበር ስብሰባ ይፋ የሆነው ጥናት ግን ረጅም የቀን ሸለብታ እና የስኳር በሽታ ግንኙነትን አብራርቷል።

በጥናቱ ቀን ላይ ከ60 ደቂቃ በላይ የሚተኙ ሰዎች ከማይተኙት ይልቅ ለታይፕ 2 የስኳር ህመም የመጋለጥ እድላቸው በ45 በመቶ መጨመሩ ተረጋግጧል።

ይሁን እንጂ ከ40 ደቂቃ በታች የሚተኙት ከህመሙ ጋር ግንኙነት የላቸውም ይላል ጥናቱ።

 

የአተኛኘት ሁኔታ

ተመራማሪዎቹ ረጅም ሸለብታ የሌሊት እንቅልፍ መዛባት ውጤት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ይህ የእንቅልፍ መዛባትም ለልብ ህመም፣ ስትሮክ፣ ለደም ዝውውር እና የምግብ መፈጨት ችግሮች እንዲሁም ለታይፕ 2 የስኳር በሽታ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።

በስራ አልያም በሌላ ማህበራዊ ህይወት የተነሳ የሚከሰት የእንቅልፍ እጦት የምግብ ፍላጎትን ስለሚጨምርም ለታይፕ 2 የስኳር ህመም የመጋለጥ መጠንን ያሳድጋል።

በአንፃሩ አጭር ሸለብታዎች ንቃትን ከመጨመር ባለፈ ክህሎትን ያሳድጋሉ ነው ያሉት አጥኚዎቹ።

 

“የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክት”

በግላስጎቭ ዩኒቨርሲቲ የሜታቦሊክ ሜዲሲን ፕሮፌሰሩ ናቬድ ሳታር እንደሚሉት፥ የእንቅልፍ መዛባት እና የስኳር ህመም ያላቸውን ዝምድና የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።

“ለስኳር ህመም የሚያጋልጡ ነገሮች ለሸለብታም ምክንያት ይሆናሉ፤ የእንቅልፍ መዛባት ከፍተኛ የሰውነት የስኳር መጠንን ያመለክታል፤ በመሆኑም ረጅም ሸለብታ የስኳር በሽታ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክት ሊሆን ይችላል” ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ።

ይሁን እንጂ ከእንቅልፍ ሁኔታ በተጨማሪ ለስኳር በሽታ መጋለጥን የሚያመላክቱ ሌሎች ምልክቶችም እንዳሉ አስገንዝበዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ኢፒዲሞሎጂ ክፍል የሚሰሩት ዶክተር ቤንጃሚን ካይርንስ በበኩላቸው፥ የቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት የጥናት ውጤት ጥንቃቄ ያሻዋል ባይ ናቸው።

አንዳንድ ጊዜ ረጅም ሸለብታ ከእንቅልፍ መዛባት ጋር ተያይዞ ሊከሰት ስለሚችል ረጅም ሸለብታ የስኳር በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል ብሎ መደመደም ተገቢ አይደለም።

 

ምንጭ፡- ዶክተር ቤንጃሚን

 

  

Related Topics