የሰው ልጅ አካል የተሰራው በዋነኝነት ከፕሮቲን ነው፡፡

የእርጅና መድሃኒቶችን ያውቋቸዋል? ካላወቋቸው እነሆ እንንገራችሁ

 

 Image result for የእርጅና መድሃኒቶችን

 

የሰው ልጅ አካል የተሰራው በዋነኝነት ከፕሮቲን ነው፡፡ ፕሮቲን ደግሞ የተገነባው ቢያንስ ከአምስት መሰረታዊ ንጥረ ነገሮች ነው፡፡ ይኸውም ካርቦን (C)፣ ሃይድሮጅን (H)፣ ኦክሲጂን (O)፣ ናይትሮጂን (N) እና ሰልፈር (S) ናቸው፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ በአየር፣ በውሃ፣ በአፈር፣ በእፀዋትና፣ በእንስሳት ውስጥ በተለያየ መጠን ይገኛሉ፡፡ ሕይወት እንዴት እንደተሳሰረ ተመለከታችሁ? ይሄ ማለት ወደ ተፈጥሮ ስር መሰረት ስሪት ስንመለስ ህይወት ያለውም ሕይወት የሌለውም አንድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው እና መሰል ንጥረ ነገሮች (የካርቦን፣ ኦክስጂን፣ ሃይድሮጂን ወዘተ…) በቀላል ቋንቋ አተም እንላቸዋለን፡፡ አተሞች የተሰሩት ደግሞ ከሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ኤሌክትሮን ይባላል፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች እርስ በእርስ እየተሳሳቡና እየተጣመዱ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ይፈጥራሉ፡፡ ለምሳሌ ፕሮቲን፣ ስብ፣ ውሃ፣ አልኮል፣ ነዳጅ ወዘተ…፡፡

 

በአተሞች የላይኛው ምህዋራቸው ላይ የሚሽከረከሩት ኤሌክትሮኖች በባህሪያቸው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ቁጥራቸው 8 ከሆነ የተረጋጉ (Stable) ይሆናሉ፡፡ ሰባትና ከዚያ በታች ሲሆኑ ደግሞ ያልተረጋጉ (Unstable) ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ያልተረጋጉ አተሞች ሁልጊዜ የህይወት ትግላቸው ለመረጋጋት የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ኤሌክትሮን መፈለግ ነው፡፡ ይሄንን ተጨማሪ ኤሌክትሮን አንድ በመበደር ወይም በመጋራት አለዚያ አለመረጋጋቱን የፈጠረውን ትርፍ ኤሌክትሮን በማበደር ከሌሎች አተሞች ጋር ጥምረት በመፍጠር ለመረጋጋት ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የህይወት ቅምር ሰንሰለት ሒደቱን ይቀጥላል፡፡ ይሄ ግንዛቤ ቀጥሎ ለማስረዳው ጉዳይ መሰረት ነው፡፡

 

የአካላችን ግንባታ የሚጀምረው ከሴሎች ነው (ሴሎች የተሰሩት ከላይ ከጠቀስናቸው ንጥረ ነገሮች መሆኑን አስታውሱ)፡፡ ልክ ቤት ሲሰራ ከብሎኬት ወይም ከጡብ እንደሆነ ሁሉ ማለት ነው፡፡ (ጡብና ብሎኬቱ የተሰሩት ደግሞ ከተለያዩ ግብዓቶች ነው)፡፡ ሴሎች በዓይን የማይታዩ ህዋሶች ናቸው፡፡ እነርሱ ተገጣጥመው ግን ቲሹ (Tissue) ይሰራሉ፡፡ ቲሹን እንደ የቤቱ የአንድ ጎን ግድግዳ እንመልከተው፡፡ ገና ቤት አልሆነም፡፡ ቲሹዎች ተገጣጥመው ደግሞ የአካላችንን የተለያዩ ክፍሎችን ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ዓይን፣ አፍንጫ፣ ሣንባ፣ ጉበት፣ ልብ ወዘተ…፡፡ እነዚህ ክፍሎች ደግሞ በተለያዩ ስርዓቶች (Systems) ተያይዘው የሰውን አካል ሙሉውን ይሰራሉ ማለት ነው፡፡

 

ይሄ አካል እንግዲህ በብዙ ትሪሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሴሎች ነው የተገነባው፡፡ እነዚህ ሴሎች እያንዳንዳቸው ለራሳቸው የሚሆን ኃይል (Energy) ማመንጨት ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው ከምግብ የሚገኘውን የኃይል ምንጭ የሆነውን ግሉኮስ እንደማገዶ ሰባብሮ ወደ ኤቲፒ (ATP) የሚባል የኃይል ቅምር ወይም በቀላል አማርኛ የባትሪ ድንጋይ በመቀየር ነው፡፡ ይሄ ሂደት እያንዳንዷን ሴል በህይወት እንድትቆይ ያደርጋል፡፡

 

ሴሎች ከላይ የተብራራውን እጅግ በጣም አስፈላጊ ስራ ሲሰሩ በጎንዮሽ በጣም አጥፊ የሆኑ ኬሚካሎች ይፈጠራሉ፡፡ ስማቸውም ፍሪ ራዲካልስ (Free Radicals) ይባላል፡፡ ፍሪ ራዲካሎች በተፈጥሮ የሚኖሩያልተረጋጉ የኦክሲጅን አተሞች ናቸው፡፡ ይህ አለመረጋጋታቸው ደግሞ ሁልጊዜ የጎደላቸውን ኤሌክትሮን ለማሟላትና ለመረጋጋት ሲሉ አንድ እጅግ አደገኛ የሆነ ስራ ይሰራሉ፡፡ ይህም ራሳቸውን እየወረወሩ ተረጋግተው ስራቸውን ከሚሰሩት ሴሎቻችን ጋር እያጋጩ ኤሌክትሮን ለመስረቅ ትግል ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳቢያ ይሄንን ውርጅብኝ የሚቀበሉ ሴሎቻችን ላይ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ጉዳቱ ሴሎች ዳግመኛ በትክክል እንዳይሰሩ ከማድረግ በተጨማሪ በትክክል እንዳይራቡ የዘር ስሌትን እስከ መጉዳት (Genetic Matrial Damage) ሁሉ ሊያደርስ ይችላል፡፡

 

ይሄ የፍሪ ራዲካሎች ጦርነት እወጃ ሴሎቻችንን በጎዳ ቁጥር የእኛም ቆዳና አካል እያረጀ ይሄዳል፡፡ ማርጀት ብቻ ሳይሆን የፍሪ ራዲካሎች ጥቃት ከዚህም የከፋና ቁጥራቸው በርካታ ለሆኑ የጤና ችግሮች አካላችንን ያጋልጣል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የፍሪ ራዲካሎች ቁጥር በአካላችን ውስጥ መብዛትና የካንሰር በሽታ መፈጠር በከፍተኛ ደረጃ ተዛማጅነት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለሌሎች በሽታዎች ማለትም ለልብ በሽታ፣ ለደም ስሮች መቆርፈድ፣ የደም መርጋት፣ ኢንፍላሜሽኖች (ለካንሰር መንሰራራት መንስኤ ነው)፣ ለቆዳ ጉዳት ወዘተ… መንስኤ ይሆናል፡፡

 

ከላይ እንደተገለፀው እንግዲህ ይነስም ይብዛም ይሄ በተፈጥሮ ፍሪ ራዲካሎችን እንደ የጎንዮሽ ውጤት የማምረቱ ሂደት በሁላችንም አካል ውስጥ አለ፡፡ ጥቁር ይሁን ነጭ፣ ቀይ ይሁን ቢጫ የተባለ የሰው ዘር ውስጥ ሁሉ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ይሄን የፍሪ ራዲካሎችን ምርት የሚያባብሱ ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም ሲጃራ ማጤስ፣ መጠጥ መጠጣት፣ የአየር ብክለት (በተለያዩ ኬሚካሎች)፣ የተጠበሱ ስብና ቅባት የበዛባቸው ምግቦች፣ በጣም ጣፋጭ ምግቦች፣ አርቴፊሻል ማጣፈጫዎች፣ እና ቀለሞች ወዘተ… ያሉባቸው ምግቦች እና የመሳሰሉት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አካላችንን የሚጎዱ ነገሮች ወደ ሰውነታችን ሲገቡ ሰውነት እነርሱ የያዙትን መርዝ (Toxin) ለማስወገድ በሚታገልበት ጊዜ በርካታ ፍሪ ራዲካሎች ይመረታሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚፈጠሩት ፍሪ ራዲካሎች ደግሞ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ ከመሆኑ በተጨማሪ ጉዳታቸውም በተፈጥሮ ከሚመረቱት ፍሪ ራዲካሎች የከፋ ነው፡፡ ለዚህ ነው የአልኮል ጠጪዎች፣ ሲጃራ አጫሾች፣ የጫትና የሺሻ ወዘተ… ሱሰኞች ከእኩዮቻቸው ቶሎ የፊት ቆዳቸው ሲያረጅና አካላቸው ሲላሽቅ የምናየው፡፡ የልጅ መልክ የነበራቸው ሰዎች በእነዚህ ሱሶች ሲጠመዱ ወዲያውኑ በተለይ የፊት ቆዳቸው በዓይናቸው ዙሪያ ያለው ስስ ቆዳ የመጥቆርና የመሸብሸብ ምልክት ያሳያል፡፡ ይህ እንግዲህ ከውስጥ የሚፈጠረውን ጉዳት የማይጨምር ነው፡፡

 

እንግዲህ ወገኖቼ እዚህ ላይ ቆም ተብሎ ሊታሰብ ይገባል፡፡ በሰውነታችን ውስጥ በተፈጥሮ የሚፈጠሩት ፍሪ ራዲካሎች ሳያንሱ ከውጭ እያመጣን በምንሞጅራቸው መርዞች አማካኝነት ለምን ለተጨማሪ ጉዳት ራሳችንን እናጋልጣለን? ስለዚህ ቢያንስ የፍሪ ራዲካሎችን ምርት ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ባይቻል እንኳ በከፍተኛ መጠን ግን መቀነስ እንችላለን፡፡ በተፈጥሮ የሚፈጠሩትን ከስር ከስር ማስወገድ ራሱ በቂ የቤት ስራ ነው፡፡

 

ፍሪ ራዲካሎች ከሰውነታችን እንዴት እናስወግድ?

 

‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንዲሉ ለፍሪ ራዲካሎች የሚሆኑ አስገራሚ መድሃኒቶች አሉ፡፡ ፍሪ ራዲካሎች ሴሎቻችንን እንዳይጎዱ እንደ ጋሻ እየተከላከሉ እና እንዲረጋጉ ደግሞ የሚፈልጉትን ኤሌክትሮኖች የሚለግሱ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነፃ አውጪዎች ደግሞ ምንድን ናቸው? አትሉም፡፡ እነዚህ ነፃ አውጪዎች ስማቸው ‹ሚ‹አንታይ ኦክሲዳት›› ይባላል፡፡ የኬሚካል ስሞች እንደበዛባችሁ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ይሄንን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ብንሞክር ሌላ የአማርኛ ፍቺ የሚጠይቅ የአማርኛ ቃል እንዳይሆንብን እሰጋለሁ፡፡ ስለዚህ ልክ የውጭ ሀገር የእግርኳስ ተጨዋቾችን ስም እንደምንሸመድደው እነዚህንም በቃላችን እንያዛቸው፡፡ ደጋግመን አንብበንም እናጥናቸው፡፡ ይሄ ጉዳይ የእያንዳንዳችን አካል ጉዳይ ነውና፡፡

 

አንታይ ኦክሲዳንቶች ከላይ እንደገለፅኩት በተፈጥረአቸው ትርፍ ኤሌክትሮን ለጋሾች ናቸው፡፡ ትርፍ ኤሌክትሮኖችን ለእነዚያ ኤሌክትሮን ተርበው ሴሎቻችንን ለሚወግሩት ፍሪ ራዲካሎች በመስጠት ያረጋጓቸዋል፡፡

 

ታዲያ አንታይ ኦክሲዳንቶችን ከየት ነው የምናገኛቸው? የሚል ጥያቄ ካነሳን በአንድ በኩል በመጠኑ ሰውነታችን ራሱ የሚያመርታቸው ሲሆን በሌላ በኩል ግን በበቂ መጠን በምግባችን አማካኝነት ለሰውነታችን መቅረብ አለበት፡፡

 

አንታይ ኦክሲዳንቶች እስከ ዛሬ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው በብዛት የሚገኙት በአትክልትና ፍራፍሬ ውስጥ ሲሆን በተጨማሪ ከተለያዩ እርጥብና ደረቅ ቅመሞችና እንደ የወይራ ዘይት አይነት ጤናማ ቅባቶች ውስጥም ይገኛሉ፡፡

 

የሚገርማችሁ አንታይ ኦክሲዳንቶች ያለባቸውን ምግቦች ለይቶ መሸመት እጅግ በጣም ቀላል ከመሆኑ የተነሳ ምንም ያልተማረ ሰው እንኳን እየለቀመ ሊያወጣቸው ይችላል፡፡ ይኸውም ቀለማቸውን በማየት ነው፡፡

 

አንታይ ኦክሲዳንት ያለባቸው ምግቦች በአብዛኛው በቀለም ኮዳቸው ይመደባሉ፡፡ እነርሱም ቀያዮቹ፣ ቢጫና ብርቱካናማዎቹ፣ አረንጓዴዎቹ፣ ወይን ጠጅና ሰማያዎቹ፣ ነጭና ቡናማዎቹ ወዘተ… በመባል ነው፡፡

 

ቀያዮቹ

ቀያዮቹ አትክልትና ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ላይኮፔን (Lycopen) የሚባል አንታይ ኦክሲዳንት የያዙ ሲሆን ለቀለማቸው ቀይ መሆን ምክንያትም ነው፡፡ ቀያዮቹን ለመጥቀስ ያህል ቲማቲም፣ ሐብሐብ፣ እንጀራ፣ የሮማን ፍሬ፣ ቀይ አፕል፣ ራድሽ (የቀይ ስር ዘሮች ሆነው ትንንሽ ናቸው)፣ ፕሪም፣ የፈረንጅ ቀዩ ቃሪያ፣ ቀይ ቦለቄ ወዘተ…፡፡

 

ቢጫና ብርቱካናማዎቹ

እነዚህ ደግሞ በውስጣቸው ቤታ ካሮቲንና አስኮርቢክ አሲድን (Beta Carotene and Ascotic Acid) የመሳሰሉት የአንታይ ኦክሲዳንት አይነቶችን የያዙ ሲሆን በተለምዶ ቫይታሚን ኤ እና ቫይታሚን ሲ በምሳሌነት ይነሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ ብርቱካን፣ አናናስ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ካሮት፣ ዱባ፣ ቢጫውና ብርቱካናማው የፈረጅን ቃሪያ ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 

ወይን ጠጅና ሰማያዊዎቹ

እነዚህኞቹ ደግሞ አንቶሳይኒን (Anthocyanin) እና ፍላቫኖይድ (Flavanoids) የሚባሉትን የአንታይ ኦክሲዳንት ዓይነት የያዙ ሲሆን እንደ ብሎቤሪ፣ ብላክቤሪ፣ ወይን ጠጅ ካሮት፣ ወይን ጠጅ አበባ፣ ወይን ጠጅ ጎመን፣ ወይን ጠጅ ድንች ያሉ እኛ ሀገር የማይገኙ ይሄንን አይነት አንታይ ኦክሲዳንቶች በብዛት የያዙ ፍራፍሬ እና አትክልት ናቸው፡፡ እኛ ሀገር ከሚገኙት መካከል ብርንጃል፣ ወይን ጠጅ ጥቅል ጎመን፣ ወይን ጠጅ የፈረጅን ቃሪያ፣ ወይን ጠጅ ወይን፣ ቀይ ስር፣ ወይን ጠጅ ቀይ ሽንኩርት (በተለምዶ ቀይ ሽንኩርት የሚባለው) ይጠቀሳሉ፡፡

 

አረንጓዴዎቹ

አረንጓዴዎቹ ደግሞ በዋናነት ሎቲን እና ዚያክሳንቲን (Lutein and Zeaxanthin) የተባሉትን የአንታይ ኦክሲዳንት አይነቶችን የያዙ ሲሆን ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ብሮክሊ፣ ስፒናች፣ አስፓርገስ፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቃሪያ፣ ፎሶሊያ፣ አረንጓዴ የፈረንጅ ቃሪያ፣ አረንጓዴ አፕል፣ የድንብላል ቅጠል፣ የስጎ ቅጠል፣ የጥብስ ቅጠል፣ ኮሰረት፣ ጦስኝ፣ በሶብላ፣ ወዘተ… ይጠቀሳሉ፡፡

 

ነጫጮቹና ቡናማዎቹ

እነዚህኞቹ ደግሞ አሊሲን (Allicin) እና ኪውርሲቲን (Quercetin) የተባሉትን አንታይ ኦክሲዳንቶች ይይዛሉ፡፡ እነዚህ አንታይ ኦክሲዳንት ነጭ ሽንኩርት፣ አበባ ጎመን፣ እንጉዳይ፣ ነጭ ቦለቄ፣ ነጭ ራዲሽ (ነጭ ካሮት የሚመስል)፣ የተፈጥሮ ካካዎ፣ ተልባ፣ አጃ ወዘተ… ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ከተረዳነው በቀላሉ ሸምተን በገበታችን ላይ እንዲገኙ ማድረግ እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ ላስገነዝብ የምፈልገው ከላይ የቀረበው አይነት አከፋፈል እንዲህ በቀላሉ አንታይ ኦክሲዳንቶቹን ለመረዳት እና ለመለየት እንዲያስችል ሆኖ የተዘጋጀና የአንታይ ኦክሲዳንቱ አይነት በጣም ጎልቶ በብዛት በሚገኘው ተመድቦ እንጂ በአንድ ቡድን ውስጥ ሌላው አይነት አንታይ ኦክሲዳንት ፈፅሞ አይገኝም ማለት አይደለም፡፡ ያው እንደምታውቁት ተፈጥሮ በቸርነት የተገነባች ነች፡፡ ተፈጥሮ ላይ አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ብቻ ነው የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን እንዳያችሁት እንደዚህ በቀለም ከፋፍለን ስናየው ብዙ ስራ ያቃልልልናል፡፡ በቀላሉ ያግባባናልም፡፡

 

ማስታወሻ

አንታይ ኦክሲዳንቶችን በተጨማሪ ምግብነት (Food Supplements) ተዘጋጅተው ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ሲ፣ ቫይታሚን ኢ ወዘተ… በመባል የሚቀረቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን አንድን አይነት ንጥረ ነገር ለብቻው ነጥሎ አውጥቶ መጠቀምን የስነ ምግብ ሳይንቲስቶች አይመክሩም፡፡ የተሻለ የሚሆነው እነዚህን አንታይ ኦክሲዳንቶችን ከላይ ከተዘረዘሩት የተፈጥሮ ምግቦች ብናገኛቸው ነው፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት፣ አንታይ ኦክሲዳንቶች ለፍሪ ራዲካሎች ኤሌክትሮን ከለገሱ በኋላ ራሳቸውን እንዲያረጋጉ የሚያደርጉ ሌሎች አንታይ ኦክሲዳንቶች በምግቡ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ይህም የኤሌክትሮን እጦት የሚፈጥረውን ሠንሠለታዊ ሂደቶችን (Chain Reactions) እንዳይኖር ይረዳሉ፡፡ በአርቴፊሻል መንገድ አንድ አይነት አንታይ ኦክሲዳንትን ነጥለን ብንወስድ ግን ይሄን አይነት ድጋፍ አናገኘም፡፡

 

በመጨረሻም ‹‹በቂ አንታይ ኦክሲዳንት ያለበትን ምግብ እየበላሁ እንደሆነ በምን አውቃለሁ?›› ብሎ ለሚጠይቅ፣ የማዕዳችሁን ቀለም ተመልከቱ እላለሁ፡፡ በተለይ በተለይ ምግባችን በእሳት ያልተጎዳ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በየዕለቱ የምንመገበው ከሆነ ጥሩ የአንታይ ኦክሲዳንት ማዕድ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡

 

ስለዚህ ምግባችንን በእነዚህ ደማቅ ቀለሞች በታጀቡ ምግቦች በማስዋብ ወጣት እንደመሰልን እንድናረጅ እየመከርኩ ለዛሬ በዚሁ ልሰናበት፡፡

 

source -zehabesha

 

  

Related Topics