ደም ማጠብ ማለት ምን ማለት ነው? የኩላሊት በሽታስ ደምን ያቆሽሻል እንዴ?

ደም ማጠብ ማለት ምን ማለት ነው? የኩላሊት በሽታስ ደምን ያቆሽሻል እንዴ?

 

 

ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁልኝ? የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ስሆን የአባቴ ጤና በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለሆነ ነው ዛሬ እናንተን ለማማከር ብዕሬን ያነሳሁት፡፡ አባዬ የስኳር በሽተኛ ሲሆን ላለፉት 14 ዓመታት ተገቢውን ህክምናና ክትትል እያደረገ በአንፃራዊ ሁኔታ ደህና ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የሚከታተሉት ሐኪሞች ደም ግፊትና ኩላሊት በሽታዎችም አሉብህ አሉት፡፡ ተጨማሪ ምክርና መድሃኒትም ሰጡት፡፡ ይሁን እንጂ ከመዳን ይልቅ እየባሰበት ሄደ፡፡ በተለይም የኩላሊት በሽታው አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ሐኪሞቹም ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጭ እየሆኑ ስለሆነ ኩላሊቱ መቀየር አሊያም ደሙ መታጠብ አለበት ተባልን፡፡

 

እኔ የምለው የአባቴን ህይወት ለመታደግ ሌላ አማራጭ የለም ማለት ነው? ደም ማጠብ ማለትስ ምን ማለት ነው? የኩላሊት በሽታ ደምን ያቆሽሻል ማለት ነው? እባካችሁ አፋጣኝ መልስ ስጡኝ፡፡

 

የተቸገርኩ አንባቢያችሁ ነኝ

የአባትህ ሁኔታ በእውነትም አሳሳቢ ነው፡፡ አንዴ ከያዘ በማይለቀው ስኳር በሽታ ተይዘው ተገቢውን ህክምናና ክትትል ሳይሰለቹ ሲያደርጉ መቆየታቸው በእውነቱ ያስመሰግናቸዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጤና የመቆየታቸው ምስጢርም ጥንቁቅነታቸው ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ምንም ቢጠነቀቁ እንዲህ አይነት በሽታዎች በመጨረሻ እየተባባሱ ሄደው ለሌሎች በሽታዎችና ለተለያዩ የአካል ክፍሎች ብልሽት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም አባትህ በአሁኑ ወቅት ‹‹የጣምራዎቹ ደዌዎች›› ታማሚ መሆናቸውን ከገለፃህ ተረድተናል፡፡

 

ኩላሊትን ለብልሽትና ለውድቀት ከሚዳርጉት በሽታዎች ደግሞ ስኳርና ደም ግፊት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በእኛም ሆነ በምዕራባውያን ዘንድ ሶስቱም በሽታዎች ደግሞ አንዱ ለአንዱ መንስኤና ውጤት በመሆን ይተጋገዛሉ፡፡

 

ውድ የተቸገርከው አንባቢያችን ይህ ችግር ያንተ አባት ብቻ አይደለም፡፡ የአብዛኛው የህብረተሰባችን ችግር በመሆኑ እኛም ቅድሚያ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ መሰረት ኩላሊት በአግባቡ ስራውን መወጣት አልቻለም የሚባለው መቼ ነው? በምንስ ይታወቃል? እንዴት መከላከልና ማከም ይቻላል? በሚሉትና በህክምናው አማራጮች ዙሪያ አጠር ያለ ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

 

እንደሚታወቀው ኩላሊት ብዙ ተግባራት ቢኖሩትም አንዱና ዋነኛው ተግባሩ ግን በደም ውስጥ የሚዘዋወሩ ተረፈ ምርቶችና መርዛማ ኬሚካሎችን እያጣራ በሽንት መልክ ማስወገድ ነው፡፡ የተጣራ የደም ዝውውርና ያልተዛባ የንጥረ ነገሮች ሚዛን እንዲኖር ማለት ነው፡፡ በዚህ ተግባሩ ላይ እክል የሚፈጥሩ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡

 

እነዚህ ችግሮች በኩላሊት ተግባር ላይ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ እንደየችግሮቹ ክብደትና ቅለት እንዲሁም እንደየተከሰቱበት ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአጭር ጊዜ ተከስተው በአጣዳፊ ሁኔታ ኩላሊት ተግባሩን መወጣት እንዳይችል የሚያደርጉ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በከፍተኛ የደም መፍሰስ ወይም በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ሳቢያ የሚከሰት የደም ዝውውር ማነስ እንዲሁም በተወሳሰቡ አደገኛ ኢንፌክሽኖች የሚከሰት ‹‹ሴፕሲስ›› ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህን በአብዛኛው መከላከል እና ከተከሰቱም በተገቢው አፋጣኝ ህክምና የኩላሊትን ተግባር መታደግ ይቻላል፡፡

 

በአንጻሩ ደግሞ ቀስ በቀስ ስር እየሰደዱ የኩላሊትን ተግባር በማዳከም በመጨረሻ ለኩላሊት ውድቀት የሚዳርጉ በሽታዎችም ሞልተዋል፡፡ ለዚህም አባትህን ያጠቁት ‹‹ጣምራ ደዌዎች›› የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ እነዚህንም ስር የሰደዱ በሽታዎች መከላከል እና በኩላሊት ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ መቀነስ ይቻላል፡፡ ሆኖም ጊዜው ይርዘም እንጂ ኩላሊት እየተዳከመ ሄዶ ከነጭራሹ ተግባሩን የማያከናውንበት ደረጃ መድረሱ አይቀሬ ነው፡፡ በአባትህም ላይ የተከሰተው ይኸው ይመስላል፡፡

 

ውድ ጠያቂያችን በዚህ የመጨረሻ ደረጃም ቢሆን መፍትሄ አለው፡- (Renal replacement therapy) የሚባል መፍትሄ፡፡ ይህ ማለት የተበላሸውን ኩላሊት ተግባር ተክቶ የሚሰራ ተተኪ ኩላሊት ወይም ተክቶ የሚሰራ ማሽን ነው፡፡ ስለሁለቱም በአጭሩ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

 

ሁለቱም ኩላሊቶች አክትሞላቸው ተግባራቸው በእነዚህ ህክምናዎች መተካት አለበት የሚባለው ተግባራቸውን የማከናወን አቅማቸው በ90 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ሲቀንስ ነው (ERD)፡፡ እስከዚያ ግን በሌሎች አጋዥ ህክምናዎች (Supportive measures) ማቆየት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ጤነኛ ኩላሊት ካለ በቂ ነው፡፡ የኩላሊትን ተግባር ከሚተኩ ሁለት አማራጮች ተመራጩ የተበላሹትን ኩላሊቶች በህክምና አስወግዶ በሌላ ጤነኛ ኩላሊት መተካት (Renal transplantation) ነው፡፡ ይሄኛው አማራጭ የራሱ የሆኑ አንፃራዊ ጉዳቶች ያሉትና ውድ ቢሆንም ፈዋሽነቱ የተሻለ ነው፡፡ ለታካሚው የሚስማማ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ህክምና በሀገራችን መሰጠት አለመጀመሩ ሑኔታውን ይበልጥ አስቸጋሪና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በቅርቡ ለመጀመር አንዳንድ የግል ሆስፒታሎች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ የሚበረታታ ጥረት ነው፡፡ እስከዚያው ግን ኪሳቸው ወይም የዘመዳቸው ኪስ ዳጎስ ያለ አሊያም የሚረዳ ‹‹ስፖንሰር›› ማግኘት የቻሉ (ብሩን ብቻ ሳይሆን ኩላሊቱም ጭምር) ታካሚዎች ህክምናው ወደ ሚሰጥባቸው ሀገሮች ‹‹ሪፈር›› የመደረግ መብት አላቸው፡፡ ከምዕራብ ሀገሮች በተጨማሪም ህክምናው በደቡብ አፍሪካ፣ በህንድና ታይላንድ በመሳሰሉት ሀገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ይሰጣል፡፡ ታክመው ተመልሰው በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉም ወገኖች አሉ፡፡

 

ሁለተኛው የህክምና አማራጭና ጠያቂያችንም ይበልጥ ያተኮርክበት የህክምና አይነት በማሽን አማካይነት ደምን በማጣራት አብዛኛውን የኩላሊት ተግባር የሚተካው የህክምና አይነት ነው፡፡ ‹‹Dialysis›› በመባል ይታወቃል፡፡ ሁለት አይነት ነው፡፡ አንደኛው ደምን የሚያጣራው (Hem dialysis) የሚባለው ሲሆን ሌላው ሆድ ውስጥ የሚገኘውን ፈሳሽ የሚያጣራው (Peritoneal Dialysis) ነው፡፡ በአብዛኛው ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ምርጫው በሐኪሙና በታካሚው/በቤተሰቦቹ ይወሰናል፡፡

 

ይኸኛው የደም ማጣራት ህክምና ለብዙ ጊዜ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ያውም ለአጣዳፊና ተቀልባሽ ለሆኑ የኩላሊት ብልሽቶች (Acute renal failure) ብቻ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ለሁለቱም አይነት የኩላሊት ብልሽቶች እየተሰጠ ነው፡፡ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢም ህክምናውንና ማሽን በተመለከተ በዚሁ ሆስፒታል የአጭር ጊዜ ስልጠናና የልምድ ልውውጥ የማድረግ ዕድል ነበረው፡፡

 

የህክምናው ውድነት ግን አያጠያይቅም፡፡ ለብዙዎች የሚሞከር አይደለም፡፡ ጠያቂያችንም እንደጠቀስከው ኑሯችሁ ከእጅ ወደ አፍ ይመስላል፡፡ ስለዚህም ዘመድ አዝማድ ማስቸገር አሊያም ‹‹ስፖንሰር›› ማፈላለግ ሳይኖርባችሁ አይቀርም፡፡ ፈጣሪ ይርዳችሁ፡፡ ውድነቱ ማሽኑን ጨምሮ የሚያስፈልጉ መድሃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች በአብዛኛው በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ከመሆናቸው የመነጨ ነው፡፡ በዚያ ላይ በተደጋጋሚ ለብዙ ጊዜ ነው የሚከሰተው፡፡ ስር ለሰደደው የኩላሊት ውድቀት እጥበቱ በሳምንት ቢያንስ ለአራት ቀናት፣ በቀን ከሶስት እስከ አራት ሰዓታት ይሰጣል፡፡ ለታካሚው፣ ለቤተሰቡ፣ ለበሽተኛውና ለባለሙያዎቹ አድካሚ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ሆኖም ህይወትን የመታደግ ነገር ስለሆነ መሰላቸት አያስፈልግም፡፡

 

የዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ህክምናው ከመጀመሩ በፊት መደረግ የሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶችም አሉ፡፡ ደም ከሰውነት ወደ ማሽኑ ብሎም በማሽኑ ከተጣራ በኋላ ተመልሶ ወደ ሰውነት የሚመለስበት ለዚሁ ተብሎ ቀድሞ በሚዘጋጅ የደም ስር አማካይነት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ እጅ ላይ በሚገኙ የደም ስሮ በቀላል ቀዶ ህክምና ከ2-4 ወራት ቀደም ብሎ መሰራት አለበት የደም ማዘዋወሪያ መንገዱ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የታካሚው የአመጋገብ ሁኔታ እንዲሁም በአጋዥ ህክምናዎች ሊስተካከሉ የሚችሉ ተያያዥ የጤና ችግሮች ‹‹ዲያሊሲሱ›› ከመጀመሩ በፊት መታከምና መስተካከል አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የደም ማነስ ችገር፣ የደም ግፊት መጨመር፣ ወይም መቀነስ፣ ኢንፌክሽኖች፣ የንጥረ ኬሚካሎች መዛባት ወዘተ… ቅድሚያ መስተካከል አለባቸው፡፡

 

ውድ አንባቢያችን ከላይ እንደተጠቀሰው የዚህ ህክምና ዋነኛ ተግባር በኩላሊት መወገድ የነበረባቸው ተረፈ ኬሚካሎች፣ መርዛማ ንጥረ ነገሮችና ለሰውነት ጎጂ የሆኑ ‹‹የሜታቦሊዝም›› ውጤቶች ኩላሊትን ተመስሎ በተሰራ ማሽን አማካይነት እንዲወገዱ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ሰውነት ውስጥ የሚገኙ ፈሳሾችና ንጥረ ኬሚካሎች በሚለጉበት መጠን ሚዛናቸው ተጠብቆ (Fluid and Electrolyte Balance) ታካሚው ጤናማ ህይወት እንዲመራ ማስቻል ነው የህክምናው ዋና አላማ፡፡ በተለምዶ ‹‹ደም ማጠብ››

 

በነገራችን ላይ የታደሉት ምዕራባዊያን ባለሀብቶች ማሽን እቤታቸው አስተክለው በሰለጠኑ ባለሙያዎችና በቤተሰብ ክትትል የቤት ውስጥ ህክምና ይደረግላቸዋል፡፡ ህክምናው በሚሰጥበት ረጅም ሰዓታትም ታካሚው መተኛት፣ ማንበብ ወይም ቲቪ መመልከት ይችላል፡፡ አለዚያማ ይሰለቻል፡፡

 

በዚሁ በያዝነው ዓመት የኩላሊት ስፔሻሊስት ሐኪሞቻችን ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጋር በመተባበር ‹‹የኢትዮጵያ የኩላሊት ህክምና ማህበር›› መመስረታቸው ይታወሳል፡፡ ጥሩ እርምጃ ነው፡፡ ማህበሩ ከኩላሊት በሽታና ህክምናው ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በርትቶ እንደሚሰራ እምነታችን ነው፡፡ ጥረታቸው ሰምሮ ጤናማ ኩላሊቶች ያሉት ማህበረሰብ እንድንሆን ያስችሉን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳቸው፡፡ እኛ በሀገር ደረጃ አንድ ለእናቱ የሆነ ማህበር ለመመስረት ይህን ያህል ጊዜ ወስዶብናል፡፡ በበለፀጉት ሀገራት በኩላሊት ችግሮች ዙሪያ ብቻ የሚሰሩ የአንድ ሀገር ማህበራት በአስሮች ይቆጠራሉ፡፡ የዚያ ሰው ይበለን፡፡

 

ውድ ጠያቂያችን ለእኛ ከሁሉ በላይ አዋጪው ነገር ቀድሞ መጠንቀቅ ነውና ያባትህ ክፉ ዕጣ በቤተሰባችሁ ላይ እንዳይደገም ቅድመ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ምናልባትም ለስኳር በሽታና ለደም ግፊት ተጋላጭ ልትሆኑ ስለምትችሉ የቅርብ ቤተሰብ አባላት ተመርመሩ፡፡ ሰላም ሁን፡፡

 

source=zehabesha

 

  

Related Topics