ሆንም ግን በወሲብ ህይወት ውስጥ መታቀብ ምርጫ መሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀ

መታቀብ እንዴትና ለምን?

 

Image result for መታቀብ

 

ሳይንስ እንደሚነግረን የወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ በንጥረ ነገሮች የዳበረ ስለሆነ ከሰውነት በሚወጣበት ጊዜ የራሱ የሆነ ጉዳት አለው፡፡ እነዚህ በወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች በዋናነት ሌሲቲንና ፎስፈረስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከወንዴ ዘር ፈሳሽ ውጭ ሌሲቲንና ፎስፈረስ በአዕምሮአችን ውስጥ በከፍተኛ መጠን ይገኛሉ፡፡ በጾታዊ ግንኙነት አሊያም በተለያዩ ሁኔታዎች ሌሲቲንና ፎስፈረስ  ከሰውነት ካልወጡ ደግሞ ወደ ደም ዝውውር በመግባት በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣሉ፡፡

በመንፈሳዊ ህይወታቸው መበርታት ለሚፈልጉ ደግሞ ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬደሪክ ኒቼ እንደሚነግረን እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሰውነት ውስጥ በብዛት መኖር መንፈሳዊ ኃይል ለማግኘት ይረዳል፡፡

ሆንም ግን በወሲብ ህይወት ውስጥ መታቀብ ምርጫ መሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀረ የመጣ ይመስላል፡፡ ወጣቱም ትኩረት እየሰጠው አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ወጣት ልጅአገረዶችንም ያጠቃልላል፡፡ በቀደመው ጊዜ ውግዝ የነበሩ ነገሮች አሁን እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ ጾታ የሚደረግ ግንኙነት፣ አፈንጋጭ የሆኑ የወሲብ ተግባራት፣ የራስን ስሜት በራስ ማርካት ( ማስተርቤሽን) ላይ ጽሁፎች ማሳተም ለአብዛኛው ሰው አዋጪ ገበያ ሆኖአል፡፡ ማስታወቂያዎችም ይህንኑ አጉልተው ያሳያሉ፡፡ አልባሳት፣ ሠራተኞች፣ ቁሳቁስና የመሳሰሉት ሁሉ ጾታዊ መስህብ እንዲኖራቸው እየተደረጉ ነው፡፡

ወሲብ ቀስቃሽ ጩኸቶች አለማችን እያወካት ነው፡፡ ከዚህ ‹ቅጥ አልባ ወሲባዊነት› በስተጀርባ ግን ‹መታቀብን› የሚመርጡ ሆኖም እንዴት ምርጫቸውን እውን ማድረግ እንዳለባቸው ያልተረዱ ሰዎች አሉ፡፡ ከነዚህም አብዛኞቹም እንደሚቻል ይስማሙበታል፡፡ ደናግላዊያን ልምምዱ ስለሌላቸው ጉዳዩ አይከብዳቸው ይሆናል፡፡ አናሳ ፍላጎትም ነው ያላቸው፡፡ ትንሽ ማጠናከርና ማበረታታት ለእነሱ በቂ ነው፡፡ ነገር ግን ጥልቅ የወሲብ ልምድ ላላቸው ከወሲብ ታቅቦ ለመኖር የመታቀብ ጸጋ ያስፈልጋቸዋል ወይም ደግሞ ለየት ያለ ልምምድ ይፈልጋሉ፡፡ ከጅምሩ ግን በ ‹ይቻላል› መርህ መሆኑ ግን የግድ ነው፡፡

ለምን መታቀብ አስፈለገ?

ለምን እንደምንታቀብ ከጅምሩ ምክንያታችንን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በመታቀብ ግንባታ ሂደታችን የመሰረት ድንጋይ መሆን ያለበት አስቀድሞ አስፈላጊነቱን መረዳቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ጥያቄ  ምላሽ የምንፈልገውን የመታቀብ ውጤት እንድናገኝ ትልቅ ሚና ስላለው ነው፡፡ ከወሲብ ለመታቀብ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ኃይማኖትም ዋንኛው ሊሆን ይችላል፡፡

በፈጣሪ መኖር እና በእርሱ ህግ ለሚያምን አማኝ ፋጣሪ የማይወደውን ስራ መስራት ወደ ገሀነመ እሳት እንደሚጥል ማወቁ በእራሱ ከጋብቻ ውጭ ከሚደረግ ወሲብ ለመታቀብ ይረዳል፡፡

እራስን በጋብቻ ውስጥ ለሚደረግ ግንኙነት በማዘጋጀት ጥቂቱን ጊዜ ታቅቦ የእድሜን ረዥሙን ጉዞ ከትዳር አጋር ጋር በመሆን በንጹህ መኝታ በሚገኝ ንጹህ እርካታ መደሰት ይቻላል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ከተለመደው የተለየ የሕይወት መንገድ የሚመርጡት ወሲብን ተከትለው የሚመጡትን ችግሮች በመፍራ ወይም ለወሲብ ዝቅተኛ የሆነ ስሜት ስላላቸው ይሆናል፡፡ መረጃዎች የሚያመለክቱት ወሲብ የማይፈጽሙ ልጅአገረዶች ከአባለዘር በሽታ፣ ካልተፈለገ እርግዝናም ሆነ ከልዩ ልዩ የማህጸን ካንሰሮች የተጠበቁ መሆናቸውን ነው፡፡ በተጨማሪም እስከ 50 በመቶ የሚሆኑ ከልዩ ልዩ ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች የመራቢያ አካላትን በሚያጠቁ በሽታዎች ይያዛሉ፡፡ እነዚህም የማይድኑና ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉም ወደ መራቢያ አካል ካንሰርነት የሚቀየሩ ናቸው፡፡

ከወሲብ መታቀብ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ከወሲብ መታቀብ በጥበብ፣ በማስተዋልና በአሳማኝ ምክንያት ሊደረግ ይገባል። የምክንያቱ ጥንካሬ ውሳኔውን ላለመቀልበስ ስለሚረዳን ነው፡፡

ውሳኔውን መወሰን ተገቢ ነው!!!

ለመታቀብ በቂ ምክንያት ከተገኘ በኃላ ምንም አይነት ወሲብ ባለመፈጸምና ‹መታቀብ ይቻላል› በሚል የእራስ ውሳኔ መጽናት ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ደናግላዊያንና መነኮሳትም የሚያደርጉት ይሄንኑ ነው፡፡ ነገር ግን እነሱም ሰውች እንደሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለመታቀብ ከወሰንን በኃላ ውሳኔውን እውን ለማድረግ የሚረዱ የሕይወት ልምምዶች መደረግ አለባቸው፡፡ እነዚህ ልምምዶች ቤት እስከመቀየር ሊያደርሱን ይችላሉ፡፡ ጓደኛና አካባቢንም ጭምር ያስቀይሩን ይሆናል፡፡ እነዚህ ልምምዶችም ከእድሜና ለጋብቻ ካለን ዝግጅትና ቅርበት ጋር ይገናኛሉ፡፡

ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ያልደረስን ከሆነ የተቃራኒ ጾታ ግንኙነቶች በጭራሽ ባይኖር ይመረጣል፡፡ ከወሲብ ውጭ የፍቅር  ግንኙነት ከተቃራኒ ጾታ ጋር መጀመር በተራበ ሰው ፊት ደስ የሚል ምግብ አስቀምጦ እንደማቁለጭለጭ ይቆጠራል፡፡

እራስህ አስተምር

ከማህበረሰቡ ብዙ እውቀት ይገኛል፡፡ ምን ማሰብና ማድረግ እንደሚገባንና እንደማይገባን እንማራለን፡፡ ማህበረሰቡ ሰው ስለሆንክ ብቻ ከወሲብ መታቀብ እንደማትችል ሊነግርህ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ከወዳጅህ (ከፍቅር ጓደኛህ) የምታንስ፣ የመወሰን አቅሙና ጉልበቱ የሌለህ ነህ ማለት ነው። መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን እንደዚህ የምናስብ ከሆነ አዕምሮን ዝቅ እያደረግነውና በብልታችን እየተመራን እንደሆነ ነው፡፡ ብልቶቻችን ምንግዜም የሚመሩት በአዕምሮዋችን ነው፡፡ እናም ስሜቶቻችንን እንቆጣጠራቸዋለህ፤ የሚጠይቀው ውሳኔና ስርአት ብቻ ነው፡፡

ልብ አድርግ! አስተውል!

አተኩሮትህን ሁሉ ወደስራህና ወደ ኃይማኖትህ አድርግ፡፡ በኃይማኖታዊ ምክንያቶች የምትታቀብ ከሆነ ይህን የሚያጠናክሩ ተግባትን ለምሳሌ በጸሎት፣ ቤተክስቲያን በማዘውተር አዕምሮን መያዝ ይገባል፡፡ አሊያም በሥራና በጥናት መጠመድ ተገቢ ነው፡፡ በዚህም ብዙ ጊዜና ጥረትን ካሳለፍክበት እጅግ ውጤታማ ትሆናህ፡፡ ሌላው በአንድ ክፍል ውስጥ ስራ ፈተህ ብቻህን መሆን የለብህም፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ስራ ፈት አዕምሮ የሰይጣን ሙከራ ቤት ነው፡፡

የሚጠቅምህን ተመልከት

አመለካከትህ ተስተካክሎ የልብህ እንዲሞላ የምታየው ነገር ወሳኝ ሚና ስላለው የምትመለከታቸው ፊልሞች፣ የምታዳምጣቸው ሙዚቃዎች፣ የምታነባቸው መጽሀፍት ወሲብን የሚዘክሩ ከሆኑ በእርግጠኝነት ወደነሱ ትወሰዳለህና ጥንቃቄ በማድረግ ከመታቀብ አላማህ እንዳያግዱህ ልታስብበት ይገባል፡፡ በአንጻሩ ለዓላማህ በሚጠቅሙ መገልገያዎች በቅዱሳን መጽሀፍት መታቀብን በሚደግፉ የሥነ ልቦናና የፍልስፍና መጽሀፍት መለወጡ ተገቢ ነው፡፡

ለሰይጣን እድል አትስጠው

 

ለጋብቻ ዝግጁ ካልሆንክ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ለብቻ መቀጣጠር አያስፈልግም፡፡ መሳሳምና መተቃቀፍ ወዳልተፈለገው ተግባር ያመራሀልና ተጠንቀቅ፡፡ ከጾታዊ እንቅስቃሴዎች ተቆጠብ፡፡ ምናልባት ከባድ መስሎ ይታይህ ይሆናል ግን ይቻላል፡፡

በወደቅህ ጊዜ ለእራስህ ዳግም እድል ስጥ

እርግጥ ነው መታቀብን አስመልክቶ ፍጹማዊ መሆን ከባድ ነው፡፡ እንደዛ አይነት ሰዎች ከስንት አንድ ቢገኙ ነው፡፡ እናም አንተ በመታቀብ አላማህ ውስጥ አንዳንዴ ልትፎርሽና ወሲብ ልትፈጽም ትችላለህ፡፡ ይህ ማለት ግን አንድ ጊዜ ተሳስተህ ወሲብ ስለፈጸምክ ከነጭራሹ የመታቀብ እቅድህን ሰርዘሀል ማለት አይደለም፡፡ ተሳስተህ ከወደቅበት የወሲብ ጉድጋድ በመውጣት የመታቀብ ጉዞህን ልትቀጥል ይገባሀል፡፡ በሌላ መልክ ካየኸው ደግሞ ስህተትህ አንድ ነገር ሊያስተምርህ ስለሚችል እሱን በጥንቃቄ ተገንዝበህ ዳግመኛ እንደዚህ ዓይነት ስዕተት ውስጥ እንዳትገባ መጠንቀቅ አለብህ፡፡

ትኩረትህን መታቀብህ  በሚሰጥህ ሽልማት ላይ አድርገው

አሁንም ሊሰመርበት የሚገባው የመታቀብህ ምክንያት በአላማህ ስኬት ላይ ያለው አስፈላጊነት ነው፡፡ የወሲብ ፍላጎትህ ሲንር እና መላ ሰውነትህ የወሲብ አምሮት ሲያቃጥለው ከዚህ ሁሉ ልቆ ሊሰማህ የሚገባው የመታቀብ ምክንያት ሊሆን ይገባል፡፡ ወሲብ ፈጽመህ ከምታገኘው ጊዜያዊ እፍይታና ደስታ ይልቅ መታቀብ የሚሰጥህን ዘለቄታዊ ጥቅም ሁሌ አይንህ ላይ ድቅን ሊል ይገባዋል፡፡

የብዙ ሃይማኖት ተከታዮች የሃይማኖታቸው አስተምህሮት ከጋብቻ በፊት ወሲብ እየከለከለም ቢሆን እስከጋብቻ ድረስ መታቀብ አይቻልም ብለው ለም ያስባሉ? የዚህ ጥያቄ አንዱ ምላሽ ከመታቀብ የሚገኘውን ትልቅ ሽማት ስላልተረዱት ወይም ስለሌላቸው ነው፡፡ እናም አንተ አንድ ከመታቀብ የሚገኝ ሽልማት ለእራስህ አዘጋጅ፡፡

ህይወትህን በእቅድ ምራ!

መታቀብ ለመተግበር በተወሰነ መልኩ የህይወት ዕቅድ ልታሻሽል ይገባሀል፡፡ ለምሳሌ በጊዜ ማግባት እንዳለብህ አድርገህ ብታቅድ ከጋብቻ በፊት መታቀብን ለመፈጸም እጅጉን ይረዳሀል፡፡ እንበልና በሀያዎቹ መጀመሪያ ላይ የማግባት ዕቅድ ቢኖርህ ለትዳርህ እና ለሚወለዱት ልጆችህ ስትል ገንዘብ መሰብሰብ ትጀምራለህ፡፡ እናም ለጊዜያዊ የወሲብ ጓደኝነት፣ በመጠጥና በአልጋ ኪራይ የምታጠፋውን ገንዘብ ለቁምነገር የማዋያ እድልህ ሰፊ ይሆናል፡፡

የመተጫጫ መመሪያዎች

ለትዳር የምትሆነኝህ ሴት ማጨት አለብኝ ብለህ ካሰብክ ወደወሲብ በማያመራ ሁኔታ ይህን ልታደርግ ይገባል፡፡ ለወሲብ በሚገፋፉ ቦታዎች ላይ እየተገናኛጭሁ ባታወሩ ይመረጣል፡፡ በስልክ ስታወሩም ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችን ማድረግ የለባችሁም፡፡ እርቃኗን ሆና የተነሳችውን ፎቶ እንድትልክልህ ባትጨቀጭቃት መልካም ነው፡፡

በስርዓቱ ቁጭ ብላችሁ ስለወደፊቱ የኑሮ ሁኔታችሁ የምትወያዩ ከሆነ ወደወሲብ የመገፋፋት ዕድላችሁ በጣም የጠበበ ነው፡፡ ሌላው ልታውቀው የሚገባህ ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንደማትፈልግ በግልጽ ለሴት ጓደኛህ መንገር ምንም የሚያሳፍር ነገር እንደሌለው ነው፡፡ ከተስማማችሁ በዕቅድህ መሰረት ትቀጥላላችሁ ካልሆነ ግን የአንተን ሀሳብ የምትጋራ ሌላ ሴት ፈልገህ ትይዛለህ። አሊያም ሀሳብህን እንድትቀበት ታሳምናታለህ፡፡

 

በአጠቃላይ ከማግባትህ በፊት እራስህን ከወሲብ መታቀብ ካላስተማርከው ትዳር ስትመሰርት የሚመጣብህን ፈተና ማለፍ አትችልም ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በጋብቻ ውስጥም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜ ከወሲብ እንድትታቀብ የሚያስገድድህ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ በዚህ ጊዜ አስቀድመህ ያልተለማመድከውን መታቀብ ልታመጣው አትችልም፡፡

በዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ያላችሁን ሀሳብ አስተያየት አኑሩልን። ለጓደኞቻችሁ ይህንን ጽሁፍ ሼር በማድረግ አካፍሉአቸው።

ይህን መሰል ማህበረሰባዊ ይዘት ያላቸውን ጥናታዊ ጽሁፎችን ይዘንላችሁ መቅረብ እንቀጥላለን። አብራችሁን ሁኑ። ሰላም!!!

source : selamall.com