ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎች በጤናችን ላይ ምን አይነት ጉዳት ያስከትላሉ

 ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎች በጤናችን ላይ ምን አይነት ጉዳት ያስከትላሉ

 

Image result for ተረከዛቸው ከፍ ያሉ

 

ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎችን መጫማት አሁን አሁን ወጣቶች በተለይም በቁመት አጠር የምንል ሴቶች ምርጫ እየሆኑ መጥተዋል።

 

በሌላ በኩል በተለያያ የዓለማችን ስፍራዎች ላይ ረዥም የተባሉ ሴቶች ሳይቀሩ እነዚህን ጫማዎች ሲያዘወትሩ መመልከትም ብርቅ አይደለም። የጤና ባለሙያዎች ግን ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎችን መጫማት ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች እንደሚዳርግ ነው የሚናገሩት።

እነዚህን ጫማዎችን ማዘውተር በዋናነት የሚከተሉትን የጤና ጉዳቶች ሊያስከትልብን ይችላል።

 

1.የጀርባ ህመምን ያስከትላሉ፣

ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎች ብዙ ጊዜ የሚሰሩት ፋሽንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንጂ ምቾትን በማስቀደም እንዳልሆነ ይነገራል። በመሆኑም እንደነዚህ ያሉት ጫማዎች እንደመሮጫ ጫማዎች እና አንስተኛ ተረከዝ እንዳላቸው ጫማዎች ለተረከዛችን ምቾትን የሚሰጡ አይደሉም። እነዚህን ጫማዎች ስንጫማ አጠቃላይ የሰውነታችን ክብደት በአብዛኛው በተረከዛችን ላይ ለማረፍ ስለሚገደድ እና ይህ ያልተመጣጠነ ክብደት መኖሩም የጀርባችንን የታችኛውን ክፍል በእጅጉ ስለሚጎዳው ፣ የጀርባ ህመምንም ያስከትልብናል።

 

2.የእግር ህመም፣

ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎች ከምቾት ይልቅ ለገፅታዎ ብቻ ትኩረት በመስጠት፥ እግርዎ በጫማዎቹ ቅርፅ ልክ ብቻ እንዲተጣጠፍ ስለሚያደርጉ ብዙ ጊዜ የእግር ህመም እንዲከሰትብን ያደርጋሉ ፤ በተለይም ችግሩ ለረዥም ሰዓታት ጫማዎቹን በምንጫማ ሰዎች ላይ ይጎላል። ከዚህም ባላፈ ተረከዛችን ቢጫ መልክ እንዲኖረው በማድረግ ውበቱን ያደበዝዙታል።

 

3.የባት ህመምን ያስከትላሉ፣

እነዚህን ጫማዎችን ማዘውተር የባት ህመምን ከማስከተል ባለፈ የጡንቻ ዝለት(ስትራፖ) እንዲሁም በእግራችን ውስጥ የሚካሄደው የደም ዝውውር እንዲዛባ እና ደም በአንድ አቅጣጫ እንዲከማች በማድረግ ለመራመድ እስከመቸገር ሊያደርሰን ይችላል።

 

4.ወለምታ፣

የእግር ወለምታ በበዛት ከሚከሰትባቸው ሁኔታዎች መካከል ተረከዛቸው ከፍ ያሉ ጫማዎችን መጫማት ቀዳሚ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የቱን ያህል ጥንቃቄ ቢታከልበት እንኳን በተለይም ኮረኮንች በበዛባቸው ፣ በኮብል ስቶን መንገዶች ላይ የምንጓዝ ሰዎች ለወለምታ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ነን ማለት ይቻላል። ጫማዎቹ ከሚታሰበው በላይ ከተዘወተሩም ወለምታን በማስከተል ብቻ የሚያበቁ ሳይሆን የስር መዞር ፣ የቁርጭምጭሚት ጉዳትን ሁሉ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 

5. የአከርካሪያችንን ተፈጥሯዊ ቅርፅ ያዛባሉ፣

የጫማዎቹ የተረከዝ ርዝመት በጨመረ ቁጥር በታችኛው የጀርባችን ክፍል ላይ የሚያስከትሉት ህመምም ባዛው ልክ ይጨምራል። ተረከዛቸው አንስተኛ የሆኑ ጫማዎችን ስንጫማ እና ባለተረከዝ ጫማዎችን ስንጫማ የሚኖረን አቋቋም ሙሉ በሙሉ የተለያየ ሲሆን፥ ተረከዛማ ጫማዎች ጎበጥ እንድንል በማስገደድ አከርካሪያችን ተፈጥሯዊ ቅርፁን እንዲያጣ እና የእኛም ቁመና እንዲበላሽ ያደርጋሉ።

 

6. የእግር ጣት ጉዳት

እነዚህን ጫማዎች በየእለቱ በመጫማታችን (በማዘውተራችን) የተነሳ የእግር ጣቶቻችን እንዲበልዙ እና አንደኛው ጣታችን በሌላኛው ላይ ላይ በመደረብ የጣቶቻችን ውበት በከፋ ሁኔታ እንዲበላሽ ያደርጋል። በመሆኑም ጫማዎቹ በጤናችን ላይ እክል በማያስከትሉበት ሁኔታ መጠቀሙ ይመከራል። ለአብነት ያህልም ለምን ያህል ሰዓት፣ በየትኛው አካባቢ ልንጫማቸው እንደምንችል ማየቱ እጅግ ጠቃሚ ነው ፤ ከጤናችን የሚበልጥ ምን ነገር አለ?

 

ምንጭ፡- በዶከተር አለ

 

  

Related Topics