ተመራቂ ተማሪዎች የተሳካ የስራ ዘመን እንዲኖራቸው የሚያግዙ 10 ጠቃሚ ነጥ

ተመራቂ ተማሪዎች የተሳካ የስራ ዘመን እንዲኖራቸው የሚያግዙ 10 ጠቃሚ ነጥቦች

 

Image result for ተመራቂ ተማሪዎች

 

ከከፍተኛ ት/ት በኃላ፤ የተማሪነት ሕይወትን ካጠናቀቁ በኋላ የሚከተለው የስራ ጊዜ / ዘመን/ ለአብዛኛው ወጣቶች አስቸጋሪ እና ፈታኝ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ይህ የቀጣይ ሕይወት ፈተና ከበቂ ልምድ እና ዝግጅት እጦት፣ ከት/ት ሕይወት ውጪ ያሉ የስራ እና የስራ ልምዶች እጦት /ማነስ/ እና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ግን ጥቂት ልምዶችንና ክህሎቶችን በማዳበር ይህንን የስራ ጀማሪነት ጊዜ እና ተያይዘው የሚመጡ ፈተናዎችን በብቃት ማለፍ ይቻላል። ለዚህም ይረዳሉ ያልናቸውን 10 ነጥቦች ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

1. ጥያቄ በድፍረት መጠየቅ

ብዙዎች ስለማያውቁት ነገር ጥያቄ በመጠየቅ በቂ ማብራርያ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ባለመጠየቅ አላዋቂ ሆኖ መዝለቅን ይመርጣሉ ይህ ደግሞ ለሁለት ጉዳቶች አሉት፡፡

 

1ኛ. አላዋቂ ሆኖ የሚያስቀር ሲሆን

2ኛ. በሌላ ጊዜ መጋፈጥ ስለማይቀር ሃፍረትን ያስከትላል

በመሆኑም ያልገቡን ነገሮች ካሉ በሚገባ መጠየቅ እና አሰራሮችን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

2. ለመማር ዝግጁ መሆን

አብዛኛውን ጊዜ አዳዲስ ምሩቃን በስራ አለም ላይ ካሉ አሰራሮች ጋር የመተዋወቅ እድላቸው በጣም የጠበበ ነው። በዚህ ምክኒያት በስራ አለም ላይ ልዩ ልዩ (በቀለም ትምህርት ሊገኙ የማይችሉ) ክህሎቶችን የሚጠይቁ ፈተናዎች ይገጥማቸዋል ። እነዚህን ክህሎቶች በቂ እውቀት እና ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ለመማር ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

 

3. ከተለያዩ ሰዎች ጋር የስራ ግንኙነት መፍጠር

ከተለያዩ  /በተለያየ የሙያ መስክ ላይ ከተሰማሩ/ ግለሰቦች ጋር ትስስር እና ትውውቅ መፍጠር እጅግ ጠቃሚ ነው። ምክኒያቱም ሰዎች ሁል ጊዜ ከሚያውቁት ሰው ጋር መስራት ይመርጣሉ። በመሆኑም ይህ ክህሎት ያለው ሰው ሁል ጊዜ ተመራጭ ይሆናል።

 

ይህንን  ለማዳበር ከሚያስችሉ ባህሪያት መሃከል፦

ከተለያዩ የሙያ ማህበራት ጋር መተዋወቅ

የተለያዩ የስራ እና የትውውቅ ቦታዎች(ሲምፖዚየሞች እና ኤግዚቢሽኖች) ላይ በመገኘት ሰዎችን መተዋወቅ

ኢንተርኔት እና ለስራ ትስስር የተፈጠሩ ድህረ ገጾች (እንደ LinkedIn ያሉ) ላይ በመሳተፍ እራስን ማስተዋወቅ።

 

4. የመሪነት ክህሎትን ማዳበር

በርካታ ድርጅቶች ሰራተኞች በቂ የመምራት ችሎታ እንዲኖራቸው ይሻሉ። ስለሆነም የሚቀጥሯቸው ሰራተኞች የመሪነት ችሎታ ላላቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ። የመሪነት ክህሎት በትምህርት ቤት በክለባት፣ በክፍል ውስጥ ስራዎች  / የቤት ስራዎች እና ፕሮጀክቶች/ ላይ ማዳበር የሚቻል ሲሆን በጣም ወሳኝ እና መሰረታዊ የሆነ ክህሎት ነው።

 

5. በቡድን መስራት

በአለማችን ላይ ተጽእኖ እና ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ክቻሉ የተለያዩ የፈጠራ ሃሳብ እና ግኝቶች የቡድን ስራ ውጤቶች ናቸው። ሰዎች አቅም፣ ብቃት እና ችሎታቸውን በማቀናጀት የተሻለ ለውጥ ማምጣት እና ከፍተኛ አተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት በቡድን ስራ ነው። ስለሆነም በቡድን መስራት  መልመድ እና የሌሎችን ሃሳብ የማስተናገድ ልምድ ማዳበር ይገባል።

 

6. የመግባባት ክህሎትን ማሳደግ

የስራ ተግባቦት /business communication / ከመደበኛ ንግግር እና ገለጻ ፍጹም የተለየ እውቀት እና የተለየ ልምድ የሚጠይቅ ነው። ይህንን ክህሎት የተለያዩ  ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፤በዘርፉ የተጻፉ መጽሀፍትን በማንበብ እና የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ማዳበር እና ማሻሻል ይቻላል። መልካም የመግባባት ክህሎት ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር በአንድ አላማ በተቀናጀ ሁኔታ በመስራት ድርጅትን ትርፋማ ያደርጋል።

 

7. ትርፍ ጊዜን ስራ ላይ ማዋል

ይህንን ማድረግ የስራውን ባህሪ  እና የ አሰራር ስልቶች በአጭር ጊዜ ለመረዳት የሚረዳ ቢሆንም ብዙዎች ግን ይህንን ማድረግ አይፈልጉም። ነገር ግን ብቁ ባለሙያ ለመሆን ትርፍ ጊዚያትን መስዋት በማድረግ በቂ ልምድ ማካበት ያስፈልጋል።

 

8. ገበያ ተኮር መሆን

የአንድ ድርጅት እድገት እና ትርፋማነት የመላው ሰራተኞች ማደግ መሆኑን በመገንዘብ  ድርጅቱ ትርፋማ የሚሆንባቸውን ዘዴዎች እና ለዚህም የሚረዱ ምርምሮችን  ማድረግ ተገቢ ነው። ይህም ለወደፊት የስራ ዘመን ትርፋማ ድርጅት የመመስረት ብቃት ያላብሳል።

 

9. በኮሌጅ ያካበቷቸውን ስራዎች ማደራጀት

ተማሪዎች በኮሌጅ ቆይታቸው የሰሩትን ጥናት፣ ፕሮጀክት እና ምርምር በማደራጀት እና በግል እና በማህበራዊ ድህረገጾች ላይ በማኖር ራሣቸውን ማስተዋወቅ ይገባቸዋል። ይህንን የማድረግ ጠቀሜታው በዋነኝነት በአሁኑ ሰዐት በርካታ የስራ እድሎች እና መረጃዎች የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢንተርኔት የሚለቀቁ በመሆኑ በቀላሉ ተፈላጊ እና ተመራጭ ያደርጋል።

 

10. ለሙያ ስነምግባር ተገዥ መሆን

ሁሉም የሙያ መስኮች የራሳቸው የሆነ የሙያ ስነ ምግባራት ያሏቸው ሲሆን በእያንዳንዱ የሙያ ዘርፍ የሚሰማራ ግለሰብ እነዚህን ደንቦች መጠበቅ እና ለእነርሱም ተገዢ መሆን መቻል አለበት። ይህም ግለሰቡን ከተጠያቂነት እና ተወቃሽነት ነጻ ከማድረጉም በላይ ግለሰቡን ብቁ እና ተመራጭ ያደርገዋል።

ምንጭ፡-studentethiopia.