በተራራማ አካባቢዎች ተጠብቆ የኖረ ዕውቀት

በተራራማ አካባቢዎች ተጠብቆ የኖረ ዕውቀት

 

 

ባለፉት መቶ ዘመናት በተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የመኖሪያ አካባቢያቸው አመቺ ባይሆንም እንዴት ኑሯቸውን አሸንፈው እንደሚኖሩ ተምረዋል። የተራራ ነዋሪዎች መሬታቸው ከሁለት ሺህ ዓመት ግብርና በኋላ እንኳን ለምነቱን እንዳያጣ ያስቻለ እርከን ሠርተዋል። የደጋ አካባቢዎችን ተቋቁመው ሊኖሩ የሚችሉ እንደ ላማና ያክ ያሉትን የዱር እንስሳት አላምደው የቤት እንስሳት አድርገዋል። የተራራ ነዋሪዎች ያካበቱት ባህላዊ ዕውቀት ለሁላችንም ኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ተራሮች  ጠብቆ ለማቆየት እጅግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

 

የወርልድ ዋች ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት አለን ቴን ደርኒንግ “በሁሉም ክፍለ ዓለማት ሥልጣኔ ያልደረሰባቸው ሰፊ አካባቢዎች የሚጠበቁት በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች የዘመናዊ ሳይንስ ቤተ መጻሕፍት እንኳን ሊተካከሉ የማይችሉት የእውቀት ክምችት አላቸው” ብለዋል። ይህ የዕውቀት ክምችትም ቢሆን እንደ ሌሎቹ የተራራማ አካባቢ ሀብቶች ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል።

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም 2002ን ‹‹ዓለም አቀፍ የተራሮች ዓመት›› ሲል ሰይሞታል። የዚህ ፕሮግራም አደራጆች የሰው ልጅ ሕልውና ምን ያህል በተራሮች ላይ የተመካ መሆኑን ለማስገንዘብ “ሁላችንም የተራራ ሰዎች ነን” የሚል መፈክር አውጥተዋል። የዓለም ተራሮች እንዴት ያለ ችግር እንደተደቀነባቸውና እነርሱንም ለመጠበቅ የሚያስችል መፍትሔ መፈለግ አስፈላጊ እንደሆነ ለማስገንዘብ ጥረዋል።

 

ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ተደርጎ መታየቱ በእርግጥም ተገቢ ነው። በኪርጊስታን በተደረገው የቢሽኬክ 2002 የዓለም ተራሮች የመሪዎች ስብሰባ ላይ ዋነኛው ተናጋሪ “ተራሮች የበርካታ የተፈጥሮ ሀብት ምንጮች እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም ለእነዚህ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ለሥነ ምሕዳራቸው ዘላቂነት በቂ ትኩረት አይሰጥም” ብለዋል።

ምንጭ፡-የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍ