ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው ምግቦች እድሜያቸው በገፉ ሴቶች ላይ የልብ

ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው ምግቦች እድሜያቸው በገፉ ሴቶች ላይ የልብ ችግር ያስከትላል - ጥናት

 

 

በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦች ለሰውነት እድገትና ለአጠቃላይ ጤና መልካምና አስፈላጊ እንደሆኑ ይነገራል።

ከዚህ በፊት በተደረጉ ምርምሮች ፕሮቲን የበዛበት ምግብ ለተስተካከለ የሰውነት ቁመና እንደሚጠቅምም ባለሙያዎች ገልጸዋል፤ የምግብ ፍላጎትን በመገደብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በመጠቆም።

ይህ ሁኔታ ግን ለሁሉም አይሰራም ባይ ናቸው፥ በቅርብ ጊዜ ጥናታችን ፕሮቲን የበዛባቸውን ምገቦች ማዘውተሩ እድሜያቸው ገፋ ላሉ ሴቶች እንደማይበጅ ይጠቅሳሉ።

እድሜያቸው ከ50 እስከ 79 አመት የሚገኙ ሴቶችን ባሳተፉበት ጥናታቸው፥ በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦች እነርሱ ላይ የልብ ህመም ችግርን ያስከትላል ነው ያሉት።

ይህ ደግሞ ልብ በትክክለኛውና በተፈለገው መንገድ ደም እንዳይረጭና እንዳይሰራ በማድረግ የልብን በትክክል አለመስራት ያስከትላል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ከእንስሳት ተዋጽኦ በተለይም ከስጋ የሚገኝ ፕሮቲን አይነተኛ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ፕሮቲን ከእርድ እንስሳት በሚገኝ ስጋ፣ ከዶሮ፣ ከወተት ተዋጽኦ፣ ከአሳ ዝርያዎች፣ ከባቄላ፣ አተር እና ለውዝ በብዛት ይገኛል።

በተጠቀሰው የእድሜ ክልል ለሚገኙ ሴቶች ሁሉም መልካም ባይሆኑም፥ የስጋ ተዋጽኦ ግን ልብ በትክክል እንዳይሰራ በማድረግ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወስድም ነው የገለጹት።

ተመራማሪዎች እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ከ103 ሺህ በላይ ሴቶችን፥ የአምስት አመት የአመጋገብ ስርዓትን ለመፈተሽ ሞክረዋል።

በዚህም በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን አብዝተው የሚመገቡት ከማይመገቡት ይልቅ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ሆነው መገኘታቸውን ይገልጻሉ።

ከምንም በላይ ደግሞ ከስጋ ተዋጽኦ የሚገኝ ፕሮቲንን የሚያዘወትሩት ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውንም በጥናት ውጤታቸው ይፋ አድርገዋል።

ይህ ተጋላጭነታቸው ግን ከዚህ ቀደም ከነበረባቸው የጤና እክል ጋር የማይያያዝ እና ፕሮቲን የበዛባቸውን ምግቦች ከማዘውተር የመጣ ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ።

እዚህ ላይ ግን ከስጋ የሚገኘው ፕሮቲን አደገኛ ሆኖ የአትክልት ዘሮችን የፕሮቲን ተዋጽኦ መመገብ ስለሚያስከትለው ጉዳት እና ስላለው ጠቀሜታ ተመራማሪዎቹ ያሉት ነገር የለም።

ከዛ ይልቅ የሁለቱን ጠቀሜታና ጉዳት ለመለየት የሚረዳ ሰፋ ያሉ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

እስከዛው ግን እድሜያቸው የገፋ ሴቶች ራሳቸውን ከእነዚህ ምግቦች ቢቆጥቡ መልካም መሆኑን ይመክራሉ።

 

 ምንጭ፦ medicalnewstoday.com/

 

  

Related Topics