የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለ400 አመት የሚያገለግል ባትሪ መስ

ለ400 አመት የሚያገለግል የስልክ ባትሪ ተሰራ

 

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለ400 አመት የሚያገለግል ባትሪ መስራታቸውን አስታወቁ።

ተመራማሪዎቹ በመደበኛ ሀይል የሚሞሉ ባትሪዎችን ለመስራት የሚውሉ ናኖዋየሮችን ዲዛይን ሲሰሩ ነው ለአራት ምዕተ አመት ጥቅም ላይ የሚውለውን ባትሪ በአጋጣሚ የፈጠሩት።

“ናኖዋየርስ” ኤሌክትሮኖችን አምቆ መያዝ የሚያስችል ሰፊ ቦታ ስላላቸው ተመራጭ ሀይል አስታለላፊ ናቸው።

ነገር ግን ከተወሰነ ሀይል መሞላት (ቻርጅ መደረግ) በኋላ ስራ የማቆም ባህሪ አላቸው።

ለዚህም ነው በፒኤችዲ ተማሪዋ ያ ሊ ታይ የተመራው የተመራማሪዎች ቡድን ከወርቅ ገመድ የተሰሩ እና በኤሌክትሮላይት ጀል የተሸፈኑ “ናኖዋየርስ” ባህሪን ማጥናት እና መሞከር የጀመረው።

በሙከራ ሂደቱም ቡድኑ አስገራሚ ውጤት ማግኘቱን ነው የገለፀው።

ባትሪው በሶስት ወራት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ ምንም አይነት የአቅም መቀነስ አልታየበትም።

በዚህም ይህ ባትሪ ማንኛውንም ጤናማ ስማርት ስልክም ሆነ ላብቶፕ ኮምፒውተር ለ400 አመት ማንቀሳቀስ ይችላል ተብሏል።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፋኩሊቲ መሪ ሬግናልድ ፔነር፥ የተመራማሪዎቹን በአጋጣሚ የተፈጠረ ግኝት “የሚታመን የማይመስል” ብለውታል።

“ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ባትሪዎች ከ5 ወይንም 6 ሺህ ጊዜ በላይ ቻርጅ ከተደረጉ አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ ይወርዳል” ነው ያሉት ፔነር።

ተመራማሪዎቹ እስካሁን የወርቅ ገመዶቹ እና ኤሌክሮላይት ጀሉ ጥምረት ይህን “ምርጥ ባትሪ” እንዴት ሊሰራ እንደቻለ እርግጠኛ አይደሉም።

ወርቅም ውድ ቁስ በመሆኑ ይህን ባትሪ ወደ ገበያ ከማስገባታቸው በፊት አጥኝዎቹ ሌሎች አማራጮችን እንደሚመለከቱ ተነግሯል።

በዚህም ምክንያት ቻርጅ እየተደረገ ለ400 አመት ያገለግላል የተባለው ባትሪ መቼ ወደ ገበያ ይገባል የሚለውን ለማወቅ አልተቻለም።

ይሁን እንጂ የመጀመሪያውና በአጋጣሚ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑ ነው የተነገረው።

 

 

ምንጭ፦ www.businessinsider.de/

 

  

Related Topics