ጨረቃን ዩፎዎች ጠልፈዋት ቢሄዱ ምን ይቀርብናል

 

ጨረቃን ዩፎዎች ጠልፈዋት ቢሄዱ ምን ይቀርብናል? ጨረቃ በዩፎች ከተጠለፈች የዓለም መጨረሻ ይሆናል፤ እንዴት?

 

ወደ ፊት የሰው ልጅ የሚጠብቀው አይቀሬ ውጊያ  ከባዕዳን ፍጡራን /ዩፎዎች/ ምድርን ለብቻቸው ለመቆጣጠር እኛን ማጥፋት ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ናሳ ከፍተኛ ክትትል እያደረገባቸው ነው፡፡  ስቴፈን ሐውኪንግም በተቻለ መጠን የሰው ልጅ ከባዕዳን ፍጡራን ጋር ፊት ለፊት ባይገጥም ይመረጣል ሲል  አስጠንቅቋል፡፡ አሁን እየተፈራ ያለው ነገር እነዚህ ባዕድ ፍጡራን ወደ   ፊት ከሰው ልጅ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ  ከሚገቡ ጨረቃን በቀላሉ መገንጠል ቀላሉ  ስልታቸው ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡ ለመሆኑ ላለማስገንጠል እንችል ይሆን? ከባድ ይመስላል ታዲያ የዩፎዎች ጨረቃን ገንጥለው ቢወስዷት ምን እንሆናለን? ጨረቃን ላለማስገንጠል መሰዋዕትነት መክፍል እንዳለብንና እንደሌለብን የምናውቀው ታዲያ ጥቅምና ጉዳቷን ስንረዳ ነውና እነሆ ብለናል፡፡

 

ምድራችንን ከሌሎች ክዋክብት፣ ዐለታማ አካላት፣ በራሪ አካላት፣ ግዙፍ ፕላኔቶች፣ ጨረቃዎችና ሌሎች የግዙፉ ህዋ ፍጡራን ጋር አንድም ሆነ ሌላ የሚያስተሳስር ጉዳይ አይጠፋም፡፡ በተለይ የአንደኛው መኖር ለሌላኛው ወሳኝ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ አንደኛው ባይኖር ደግሞ ሌላኛው ሊጠፋ፣ ሊዛባ አልያም ከባድ ተፅዕኖ ላይ ሊወድቅ ግድ ይል የተፈጥሮ ሕግ አስተሳስሮታል፡፡ ታድያ በምድራችን የጭለማ ወቅት የጊዜ ዑደትን እያሰላች ብቅ የምትለው ጨረቃ፣ ለኛ ምድርና ለሰው ልጅም ሆነ ለሌሎች የምድር ላይ ፍጡራን መኖር ወሳኝ ሚና እንዳላት፣ ምን ያህሎቻችሁ ታውቁ ይሆን? በተለይም ብርሃን ከመስጠት ባሻገር ጨረቃ ለመሬት ብዙ አገልግሎት እንዳላት ሰምተን ይሆን?

 

አንድ እውነታ እናስታውስ፡፡ ሳይንስ እንደሚለን ከሆነ ጨረቃ በከፊል ከምድር በፈረሰ አካል እንደተሰራች ነው፡፡ ገና በ30 ሚልዮን ዕድሜዋ ምድር የእሣሳተ ገሞራ ቅሪት ነበረች፡፡ በዚያ ወቅት ከምድር ጋር ተጋጨ የተባለው አካል፣ ብዙ የሚባሉ የምድር ላይ ዐለቶችንና የሞልተን ዐለቶችን ይዞ ወደ ህዋው ነጎደ፡፡ በመቀጠልም ይህ አካል ወደ ጨረቃ አካልነት እንደተቀየረ፣ ይህም ከቢልዮን ዓመታት ውስጥ እንደተፈጠረ በሉናርና ፕላኔታሪ ኢንስቲትዩት ጆርናል ላይ ሠፍሮ እናገኘዋለን፡፡

 

ከብዙ ቢልዮን ዓመታት በፊት፣ ጨረቃ ከምድር የነበራት ርቀት እጅግ ቅርብ ነበር ይባላል፡፡ በተለይ እንደ ሳይንስ ግምት በአማካኝ 12 ሺህ ኪሎ ሜትር እንደነበረ ነው፡፡ ዛሬ ግን ሳይንስ እንዳረጋገጠውም በጨረቃ እና በምድራችን መካከል ያለው ርቀት፣ 384.400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትታየናለች፡፡ ጨረቃ በዚህ ርቀት መሆኗም ለምድራችን ህልውና ትልቅ አስተዋጽዖ እንዲኖራት የታሰበ ይመስላል፡፡ ተፈጥሮ በዚህ መልኩ ያስተሳሰረቻቸው ሁለቱ ግዙፍ አካላት አንደኛው ለአንደኛው መኖር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡

 

የጨረቃና የምድር ትስስር

 

ከሁሉ ነገር አስቀድሞ የሚጠበቀውና የመጀመሪያ የሚሆነው፣ የጨረቃ አለመኖር የሚያስከትለው ከባድ የሆነ የባህር ወጀብ ለውጥ ነው፡፡ ባህሮች በጨረቃ ስበት ሥር ወጀቦቻቸው ተወጥረው ይገኛሉ፡፡ ጨረቃ ባትኖር የባህር ወጀቦቹ መጠናቸው፣ አሁን ካሉበት መጠን ሦስት እጥፍ ይጨምሩ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጨረቃ የሃይቆችን አልቲትዩድ ላይ ተፅዕኖ አላት፡፡ ጨረቃ በስበት ኃይል ወጥራ መያዝዋም በምድር ወገብ አካባቢ፣ ከፍተኛ የውሃ መጠን እንዲኖርና በምድር ዋልታዎች ዝቅተኛ የውሃ መጠን እንዲኖር መንስዔም ነው፡፡ ጨረቃ ባትኖርም ይህ ውሃ ወደ ሰሜናዊ አልያም ደቡባዊ ዋልታ መፍሰሱና መከማቸቱ የማይቀር ነው፡፡

 

ጨረቃ የምድርን ሽክርክሪት በማዘግየት ትልቅ ሚና አላት፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ ቀናቶች ላይ መዛባት ሊከሰትም ይችላል፡፡ በተለይም ቀደም ሲል እንደነበረው ምድር ከቢልዮን ዓመታት በፊት ጨረቃ ሳትኖር፣ አማካኝ የቀን ሰዓታት ከ8 እስከ 10 ነበር፡፡ ይህ ሁኔታም ዛሬ ላይ ጨረቃ ባትኖረን ሊከሰት ይችላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም አያሌ እንግዳ የሆኑ ክስተቶች ይከሰታሉ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ የንፋስና የአውሎ ንፋስ መጠንና ዐቅም ይጨምራል፡፡ በተያያዥም በምድር ላይ የሚኖረው የሰው ልጅም ሆነ አጠቃላይ ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ፣ በኢቮሊሽን የሚከሰቱ ነገሮች ላይ ተፅእኖ መፍጠሩ የማይቀር ይሆናል፡፡

 

ሌላኛው እና ዋነኛው ጉዳይ፣ ምድር 23 ዲግሪ አጋድላ እንድትቀጥል የጨረቃ የስበት ኃይል ዋነኛ ሥራ ነው፡፡ እናም ይህ የምድር 23 ዲግሪ ማጋደል መዛባቱ የማይቀር ነው፡፡ ምድርም በራሷ ዛቢያ የምትሽከረከርበት ሁኔታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ እንደ አንዳንዶች ሳይንሳዊ ግምት ደግሞ፣ የመሬት ማጋደል ወደ 0 ዲግሪ ሊወርድ ይችላል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ አብዛኞቹ የመሬት ክፍል ፀሐይን በቀን ለተወሰነች ደቂቃ ብቻ እንዲያገኟት ያደርጋል፡፡ ስለዚህም የጨረቃችን አለመኖር ከቀን እስከ ማታ በሚኖረን የዘልማድ ሕይወት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ ይጠበቃል፡፡

 

ጨረቃችን ብትጠፋ ከዚህ የበለጠ ጉዳቶች ሊከሰቱም ይችላሉ፡፡ በተለይም እርስ በእርስ ተያያዥ የሆኑ ነገሮች ብዙ የመሆናቸውን ያህል መጠን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጨረቃ ባትኖር በምድር ላይ ያለው የአየር ንብረት እጅግ ባስገራሚ ፍጥነት ይቀየራል፡፡ የዚህ ምክንያትም ጨረቃ የምድርን አቀማመጥ በስበት ኃይል ደግፋ ስለያዘች ነው፡፡ ምድርም 23 ዲግሪ ጋደል ብላ መሽከርከር የቻለችው፣ በጨረቃ ስበት የመሆኑን ያህል ይህን መሰል አቀማመጥ አይኖራትም፡፡ የተለያየ የአየር ንብረት ያላቸው የምድር ክፍሎችም፣ አዳዲስ የአየር ንብረት ማስተናገድ ይጀምራሉ፡፡ ይህ ለውጥ ምድር ላይ ያሉ ሀገራትን ማመሱ የማይቀር ጉዳይ ይሆናል፡፡ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስም ከፍተኛ በረዷማ አገራት ከፍተኛ ሙቀት ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው ሙቀታማ አገራት ከፍተኛ ብርድና ዝናብ፣ በረዶ ሊያስተናግዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

 

የጨረቃ አለመኖር አልያም ድንገት መጥፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳቱ የሚደርሳቸው አያሌ ፍጡራን አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የጨረቃን ዑደት ተከትለው የሚራቡ የዱር እንሰሳዎች ሲሆኑ፤ በሐይቅ ውስጥና ውጭ የሚበቅሉ ተክሎችም ሌሎች ተጠቂዎች ይሆናሉ፡፡ አንዳንድ የባህር እንስሳቶችም ከፍተኛ ወጀብ በሚኖርበት የምዕራባውያን በጋ ወቅት ዕንቁላሎቻቸውን ይጥላሉ፤ ሌሎች ደግሞ የመራቢያ ወቅታቸው ከጨረቃ እንቅስቃሴ ጋር ይያያዛል፡፡ በተዘዋዋሪም እነዚህ የተፈጥሮ ሒደቶች ማለትም ዕንቁላል መጣሉም ሆነ መዋለዱ ሊዘገይ፣ ሊዛባ አልያም በአንዳንድ ቦታዎች ከመጠን በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

 

ምድር ባትኖር ጨረቃ ካለችበት ቦታ መንቀሳቀሷ አይቀሬ ይሆናል፤ ምክንያቱም ጨረቃ ከምድር ጋር በስበት ኃይል ተወጥራ ያለች መሆኗ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጨረቃ ከምህዋራችን ርቃ መሄዷ አይቀሬ ይሆናል፤ ምናልባትም በቅርብ ርቀት ከሚገኙ ፕላኔቶች መካከል ከአንዷ ጋር በስበት ኃይል ተወጥራ ልትቆም ትችል ይሆናል፡፡ አልያም በራሷ የሽክርክሬት ፍጥነት ከኛ ምህዋር ውጭ ልትሆን ትችላለች፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ትልቁና የሚፈራው ነገር፣ ከፊቷ ተደቅኖ ይጠብቃታል – ብላክ ሆል፡፡ ብላክ ሆል ማንኛውንም ፕላኔታዊ አካል መዋጥ የሚችል ነውና የጨረቃ ዕጣ ፈንታም መበላት ሊሆን ይችላል፡፡

 

ሁላችንም እንደምንገምተው፣ ጨረቃችን ማታ ማታ ለምናየው ውበትና ድምቀት ብቻ የሚሆን ብርሃን ለጋሽ ብቻ አይደለችም፡፡ ከዚህ ባለፈም ለህልውናችን ወሳኝ የሆኑ ግልጋሎቶችን ትሰጣለች፡፡ በዚህም የተነሣ ጨረቃና ምድር አንድ አካል፣ ሁለት አምሳል ናቸው ልንል እንችላለን፡፡

 

 

 ምንጭ፡- ከስኬት ሚስጥሮች መጽኀፍ የተወሰደ 

                                 

 

 

 

  

Related Topics