ኢትዮጵያና የቱሪዝም ሃብቶቿ

 

ኢትዮጵያና የቱሪዝም ሃብቶቿ

ዶ/ር ታሌብ የሚመሩት የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በዓለም ቅርስነት ከመዘገባቸው ቅርሶች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር በመያዝ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ናት፡፡

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በ1950ዎቹ መጨረሻ ነበር የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ያቋቋሙት፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ወቅት ዘርፉን ካቋቋሙ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱትሪ መመስረት ማግስት ወደ ሀገራችን የሚገቡት ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህንንም ከግምት በማስገባት የተለያዩ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ መድረክ የማስመዝገብ ስራ ተጀመረ፡፡ ይህም ፍሬ አፍርቶ የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ባህልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርሶቹን በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገብ ጀመረ፡፡ የዩኔስኮ ምዝገባ ቅርሶቹን ለማስተዋወቅ ከመርዳቱም በተጨማሪ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግም የሚያግዝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶችን ይዛለች፡፡ በተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች የበለጸገችም ናት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ካሰባሰባቸው የመረጃ ሃብቶች መካከል 12 የስነ ጽሑፍ ቅርሶች በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ አድርጓል፡፡

ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ በብራና ላይ የተጻፉት መጽሐፈ ሄኖክ፣ መጽሐፈ ፍትሐ ነገሥት፣ መጽሐፈ ታሪከ ነገሥት፣ መጽሐፈግብረ ህማማት ፣ አርባዕቱ ወንጌል ቅዱስና የሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ናቸው፡፡ ሶስቱ ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ የጻፉት ደብዳቤ፤ የሸዋው ንጉስ ሣህለ ስላሴ ለእንግሊዝ ንግስት የጻፉት ደብዳቤና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ 2ኛ ለሞስኮው ንጉስ ኒኮላስ ቄሳር 2ኛ የጻፉት ደብዳቤ ናቸው፡፡ በጆሐንስ ፖትከን የጻፈው መዝሙረ ዳዊት፤ በግዕዝ ቋንቋ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበር የተጻፈው መጽሐፈ ቅዳሴና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ታሪክ ደግሞ ቀሪዎቹ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የስነጽሁፍ ቅርሶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከነዚህ ሌላ በይበልጥ የሚታወቁና የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡

አክሱም

 

የአክሱም ከተማ ከአዲስ አባባ በ1025 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በከተማዋ የሚገኙት የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን፣ የአክሱም ሃውልቶችና የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ግኝቶች የአክሱማይት ስልጣኔ መገለጫ ናቸው፡፡ በጊዜው፤ ከተማዋ የስልጣኔ፣ የእምነትና የአስተዳደር ማዕከል ነበረች፡፡

ከአንድ አለት የተፈለፈሉ ሃውልቶች መገኛ የሆነችው አክሱም በያዘቻቸው ሃውልቶች በይበልጥ ትታወቃለች፡፡ ከነዚህ ውስጥ ቁመቱ 33 ሜትር የሚረዝመውና አሁን ወድቆ የሚገኘው ሃውልት ረዥሙ ነው፡፡

 24 ሜትር የሚረዝመው ሃውልት አሁንም በቦታው ቆሞ ይታያል፡፡ በጎርጎሮሳዊያኑ  በ1937 ወደ ሮም የተወሰደውና 27 ሜትር የሚረዝመው ሌላኛው ሃውልት ሶስት ቦታ ተቆርጦ በጎርጎሮሳዊያኑ 2005 ወደ ነበረበት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

ሃውልቶቹ የአክሱም ስልጣኔ የደረሰበትን የዕድገትና የምህንድስና ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ባላቸው ታሪካው እሴት አክሱምና የአርኪዮሎጂ ቦታዎቹ በዓለም ቅርስነት በጎርጎሮሳዊያኑ  በ1980 ተመዝግበዋል፡፡

ሃውልቶቹ የ1700 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው ይገመታል፡፡ ሃውልቶቹ ላይ ሁለት በር መሳይ ቅርጽ ሲኖሩ በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ መስኮት መሳይ ቅርጾችንም ይዟል፡፡ አናቱ ላይ ደግሞ ግማሽ ክብ ያለው ቅርጽ አለው፡፡

ላሊበላ

ሮሃ ወይንም የአሁኗ ላሊበላ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫ ነበረች፡፡ በከተማዋ የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በንጉስ ላሊበላ ዘመነ መንግስት የተሰሩ ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያኖቹ ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሰሩ ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያኖቹ ቁጥር 11 ሲደርስ በ3 ምድብ ተከፍለዋል፡፡

በመጀመሪያው ምድብ ውስጥ  ስድስት ቤተክርስቲያኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ቤተ መድሃኒዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ድንግል፣ ቤተ ጎልጎታና ቤተ ሚካኤል ናቸው፡፡

ቤተ ገብርኤልና ሩፋኤል፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆሪዮስና ቤተ አባ ሊባኖስ በሁለተኛው ምድብ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምድብ የሚገኙ ሶስት ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ለውስጥ ከቤተ አባ ሊባኖስ ጋር ይገናኛሉ፡፡

በሶስተኛው ምድብ ብቻውን የሚገኘውና ባለው የምህንድስና ጥበብና ውበት ይበልጥ የሚታወቀው ቤተ ጊዮርጊስን የያዘ ነው፡፡

ቤተክርስቲያኖቹ በ12ኛውና በ13ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰሩ ይገመታል፡፡ የቤተክርስቲያኖቹ ግንባታ 24 ዓመት ወስዷል፡፡ አለቶቹን ፈልፍሎ አሁን ያሉትን ውቅር አብያ ቤተ ክርስቲያኖች ለመስራት 40 ሺህ የሰው ሃይል ተካፋይ ሆኖበታል፡፡

በብዙ የቅርስ አጥኚዎች 8ኛው የአለማችን አስደናቂ ቅርስ በመባል የሚታወቁት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት በጎርጎሮሳዊያኑ 1978 ነው፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ስያሜና ቅርጽ እየሩሳሌምን በምሳሌነት በመውሰድ የተሰሩ መሆናቸው ይነገራል፡፡

ጎንደር

በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መቀመጫ የነበረችው ጎንደር በአጼ ፋሲለደስ ዘመን ነበር የተቆረቆረችው፡፡ ንጉሱ በጎርጎሮሳዊያኑ 1962 ነበር ቤተ መንግስታቸውን በከተማዋ ያስገነቡት፡፡ በቀጣይነት የመጡት አስተዳዳሪዎችም የራሳቸውን መቀመጫ መገንባታቸው ይነገርላቸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የሚገኙ ቤተ መንግስቶች 900 ሜትር ርዝመት ባለው ግድግዳ የታጠሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ መገለጫ የሆነው የፋሲለደስ ግቢ በዓለም ቅርስነት በጎርጎሮሳዊያኑ  በ1980 ተመዝግቧል፡፡

ግቢው 76 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን በውስጡም 5 ቤተ መንግስቶችና ብዛት ያላቸው አነስተኛ ህንጻዎችን ይዟል፡፡ በተጨማሪም 12 በሮች አሉት፡፡

 

የሰሜንተራሮችብሔራዊፓርክ

 

 

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ይገኛል፡፡ ፓርኩ ከጎንደር ከተማ በሰሜን አቅጣጫ በ140 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በቀዳሚነት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ተብለው ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ፓርኩ በጎርጎሮሳዊያኑ 1978 ነበር በዩኔስኮ የተመዘገበው፡፡ ረዣዥም የተራራ ጫፎችና አስፈሪ ገደሎችን መያዙ ፓርኩ እጅግ ሳቢ የሆነ የመሬት አቀማመጥ እንዲኖረው አስችሏል፡፡

ረዥሙ ተራራ ራስ ዳሽን ሲሆን 4620 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ ተራራው በኢትዮጵያ በቁመቱ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ በአፍሪካ ደግሞ 4ኛ ነው፡፡ ፓርኩ እስከ 1500 ሜትር ገደላማ የሆኑ ቦታዎችን ይዟል፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ጭላዳ ባቡን፣ የሰሜን ቀበሮና ዋሊያ አይቤክስ ያሉ እንስሳትም መኖሪያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እጽዋትም በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በጎርጎሮሳዊያኑ  በ1996 አደጋ ውስጥ ከሚገኙ የዓለም ቅርሶች መካከል ተመድቧል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዋሊያ አይቤክሶች ቁጥር መቀነስና ሰዎች በፓርኩ ውስጥ መስፈራቸው በምክንያትነት ተጠቀሷል፡፡ ይህ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በመሻሻል ላይ ይገኛል፡፡

በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም አቶ ዳውድ ሙሜ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንገ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት የፓርኩን ስፋት በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ተችሏል፡፡ 250 የነበሩትንም የዋሊያዎች ቁጥር ወደ 900 አድጓል ብለዋል፡፡

የህዝብ ጫናን ለመቀነስ የተካሄደው ስራ ከፍተኛ ውጤት ከማስመዝገቡም በላይ የቱሪዝም ዕድገት ዕቅድ ለማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል፡፡


 

የታችኛው  አዋሽ ስምጥ ሸለቆ

 

 

የታችኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆ በአፋር ክልላዊ መንግስት ነው የሚገኘው፡፡ አካባቢው የአርኪዮሎጂ ጥናት የሚደረግበት የምርምር ስፍራ በመሆን ይታወቃል፡፡ በአካባቢው የተለያዩ ፍለጋዎች ተደርገው ውጤት ተገኝቶባቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የሰው ልጅ መገኛን የሚያሳዩና ያለውንም ለውጥን ለመከታተል የሚረዱ ውጤታማ ግኝቶች በአካባቢው ተገኝተዋል፡፡ 3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላትና በጎርጎሮሳዊያኑ በ1974 የተገኘችው ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በዚህ በኩል ተጠቃሽ ናት፡፡

ከ5.3 እስከ 3.9 ሚሊዮን አመት ዕድሜ ያላቸው ቅሪቶች መገኘታቸው የታችኛውን አዋሽ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአርኪዮሎጂ ጥናት ማዕከል እንዲሆን አድርገዋል፡፡

በቅርቡ ደግሞ ከድንቅነሽ 150 ሺህ ዓመት የምትቀድመው ሠላም መገኘቷ ለዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡

የታችኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆ በጎርጎሮሳዊያኑ 1980 ነው በዓለም ቅርስነት ተመዘገበው፡፡

 

የታችኛው  ኦሞ  ስምጥሸለቆ

የታችኛው ኦሞ ስምጥ ሸለቆ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ነው የሚገኘው፡፡

በአካባቢው የተገኙት የሰው ቅሪተ አካላት፣ መገልገያ መሳሩያዎች ስምጥ ሸለቆውን ለሰው ልጅ ለውጥ ጥናት እገዣቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ኦሞ ከምዕራብ ሸዋ እስከ ቱርካና ሃይቅ ድረስ ያለውን 760 ኪ.ሜ የሚያካልል ወንዝ ነው፡፡ ሁሉም የወንዙ መስመሮች ለጂኦሎጂና አርኪዮሎጂ ጥናት ከፍተኛ እገዛ አላቸው፡፡ ከአካባቢው በአሜሪካዊያንና በፈረንሳዊያን ተመራማሪዎች የሰው ቅሪተ አካሎች ተገኝተዋል፡፡ በአካባቢው የተገኘው የድንጋይ መሳሪያ 2.4 ዓመት በማስቆጠር በዕድሜ ረዥሙ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የሰውን ልጅ ዝግመተ ለውጥ የሚያሳዩ የመገልገያ መሳሪያዎች በአካባቢው በብዛት በመገኘታቸው በጎርጎሮሳዊያኑ 1980 የታችኛው ኦሞ ስምጥ ሸለቆ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ አካባቢው የተለያዩ ባህልና ተፈጥሮአዊ ውበት ያላቸው ብሄር ብሔረሰቦች፤ ድንቅ ብሔራዊ ፓርኮችና አስደናቂ እጽዋትና እንስሳት መኖሪያም ጭምር ነው፡፡

ኮንሶ

የኮንሶ ባህላዊ የመሬት አቀማመጥ 55 ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን በድንጋይ የተሰራ የእርከን ስራ ነው፡፡ ይህ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለሃያ አንድ ትውልዶች ወይም አራት መቶ አመታት የዘለቀ ነው፡፡ ስራው የአካባቢው ህብረተሰብ እሴትን፣ ማህበራዊ ትስስርና ምህንድስናን እንደሚያሳይ ዩኔስኮ አስታውቋል፡፡

የእርከን ስራው በአንዳንድ ቦታዎች እስከ አምስት ሜትር ድረስ ክፍታ ያለው አለው፡፡ አካባቢው የእንጨት ቅርጻ ቅርጾችንም ይዟል፡፡ ቅርጻ ቅርጾቹ አካባቢውን የተከበሩ ሰዎችና ጀግኖች የሚወክል ነው፡፡

ይህንን ከግምት በማስገባትም ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ አድርጎ ኮንሶን በጎርጎሮሳዊያኑ 2011 መዝግቦታል፡፡

 

ጢያ

ጢያ ከአዲስ አበባ በ90 ኪ.ሜ ርቀት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ነው የሚገኘው፡፡ በቦታው 36 ሃውልቶች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 32ቱ በተለያየ ቅርፅ ያጌጡ ናቸው፡፡ ቦታዎቹ መቃብር ቦታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምት አለ፡፡

የጢያ ትክል ድንጋይ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ በጎርጎሮሳዊያኑ 1980 ነበር የተመዘገበው፡፡

ሀረር

ሀረር ከእስልምና ማዕከልነቷ በተጨማሪ የንግድ ማዕከልም በመሆን አገልግላለች፡፡ ከተማዋ በግንብ አጥር ተከበበች በመሆን ትታወቃልች፡፡ እነዚህ ግንቦች የተገነቡት በኤሚር ኑር ኢብን ሙጃሂድ ጊዜ ነበር፡፡

ግንቦቹ የተገነቡት ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል በሚል ነበር፡፡ ግንቡ 3.5 ኪ.ሜ ርዝመትና 4 ሜትር ቁመት አለው፡፡ ግንቡ አምስት መግቢያ በሮች ሲኖሩት የከተማዋ ልዩ ምልክት በመሆንም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

በከተማዋ 99 መስጊዶች ሲኖሩ ከመካ፣ መዲናና እየሩሳሌም በመቀጠል 4ኛዋ የእስልምና ቅድስት ከተማ ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡

ሀረር የመቻቻል፣ የሰላምና የአብሮ መኖር ምልክት ተደረጋ ትወሰዳለች፡፡ ያላትን ባህላዊ ሃብት ከግምት በማስገባት ታሪካዊቷን የሀረር ከተማ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት በጎርጎሮሳዊያኑ 2006 መዝግቧል፡፡

ሐረር በአንድ ወቅት የራሷ መገበያያ ሳንቲም እንደነበራት ይነገራል፡፡

 

የማይዳሰሱባህላዊቅርሶች

የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (Intangible Heritages) ስንል የማይዳሰሱና የማይጨበጡ ወይንም በመንካት ፣በመጨበጥ፣በመዳሰስ ሊለዩ (ሊታወቁ )  የማይችሉ ነገር ግን በዓይን ሊታዩና በጆሮ ሊሰሙ የሚችሉ ቅርሶችን ነው፡፡ ስለ ቅርስ ጥናትና አጠባበቅ በወጣው  አዋጅ 209/92 እንደተጠቀሰው ኢንታንጀብል ቅርስ አንድ ህዝብ እየኖረ ያለውና የማንነቱ መገለጫ  የሆኑ እንደ ሥነ ቃል፣የእምነት፣የጋብቻ፣የሀዘን  ሥነስርዓት፣ሙዚቃ ልዩ ልዩ ትርኢትና ጫወታ እና ሌሎች ተመሳሳይ ባህላዊ እሴት ወግና ልማድን ይጨምራል፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ 2003  በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ  ጥበቃ ኮንቬንሽን ወይንም ስምምነት (Convention for the safeguarding of Intangible Cultural Heritage) የኢንታንጀብል ባህላዊ  ቅርሶች  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸው አድርገው  የተቀበሏቸውን ድርጊቶች፣ እውቀቶች፣ ሥነ ጥበባት፣ ሕግጋት፣ እምነቶች፣  ማኀበራዊ ክንዋኔዎችና ሥነ - ሥርዓቶች፣ ክብረ በዓላት  የሚያካትት ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሀገራት 281 የማይዳሰሱ ቅርሶች እስከ ጎርጎሮሳዊያኑ  2013 ድረስ  በዩኔስኮ አስመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 የሚሆኑት በአፍሪካ ሀገራት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከነዚህ መካከል አንዷናት፡፡

 

የመስቀልበዓል

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በአምስቱ ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሰረት ሁለት የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ Representative List of the Intangible Cultural Heritage of Humanity ማህደር ውስጥ ለማስመዝገብ ይቻል ዘንድ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም መሠረት የመስቀል የማይዳሰስ ቅርስን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ የሚያስችል ጥናት በባለስልጣኑ ባለሙያዎች አማካኝነት ተከናውኖ የዓለም አቀፍ ምዝገባ ኖሚኔሽን ሰነዱ ለዩኔስኮ በ2004 ዓ.ም እንዲላክ ተደርጓል፡፡

ተጠንቶ የተላከው የመስቀል ቅርስ ሰነድ ዩኔስኮ የሚጠይቀውን ሂደት ጠብቆና የተለያዩ የግምገማ መስፈርቶችን አልፎ አዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ከጎርጎሮሳዊያኑ ታህሳስ 02-07, 2013 ድረስ በተካሄደው ስምንተኛው የዩኔስኮ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጉባዔ ላይ ቀርቧል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገቡ ለጉባዔው ከቀረቡት 31 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል አንዱ መስቀል ሲሆን በጉባዔው እንዲመዘገቡ የመጨረሻ ውሳኔ ከተላለፈባቸው 25 ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

ስለሆነም የመስቀል በዓል የማይዳሰስ ቅርስ በዩኔስኮ ደረጃ ህዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም በመመዝገብ እውቅና አግኝቷል፡:

 

በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የታቀዱቅርሶች

በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ቅርሶች በተጨማሪ ሌሎችንም ቅርሶች ለማስመዝገብ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ አቶ ደሣለኝ አበባው በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ አቶ ደሣለኝ ገለጻ ከሆነ አገሪቱ በዩኔስኮ በጊዚያዊነት ያስመዘገበቻቸው አራት ቅርሶች የመልካ ቁንጡሬና የባጭልት የቅሪት አካል አካባቢዎች፣ የጌዲኦ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መልከአ ምድር እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻና የድሬ ሼክ ሁሴን መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱን በዚህ ዓመት በቋሚነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።

ከማይዳሱ ቅርሶች መካከል እስካሁን የተመዘገበው የመስቀል በዓል ቢሆንም ሌሎችንም ለማስመዝገብ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አንድን የማይዳሰስ ቅርስ በዩኔስኮ አስመዝግቦ የዓለም ቅርስ ለማስባል ሁለት አመታትን የሚጠይቅ ሲሆን በዓመትም አንድ ቅርስ ብቻ ነው ማስመዝገብ የሚቻለው፡፡ በዚህም ከሀረሪ ህዝብ ዘመን መለወጫ ጋር የሚያያዘው አሹራ ወይንም ዊርሻቶን ለማስመዝገብ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ በቀጣይነት በዩኔስኮ የዓለም ቀርስ ለመሆን የሚያስችለውን ውጤት ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼና የጨምበላላ በዓል ነው፡፡ በዓሉ የዓለም ቅርስ ይሁን አይሁን የሚለው ውሳኔ የሚያገኘው በጎርጎሮሳዊያኑ በ2016 ነው፡፡

የገዳ ስርአትን የሚመለከት ጥናት ተሰርቶ ለዩኔስኮ ይቀርባል፡፡ በዚህ ውስጥም የኢሬቻ ወይንም የምስጋና ቀን ክብረ በዓልና ያዩ ጉሙን የመሰሉ የግጭት አፈታቶች እንደሚካተቱበትም አቶ ደሣለኝ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በማይዳሱ ቅርሶች ዘርፍ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በማሰመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ የምንሆንበት እድል እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በበኩሉ ካስመዘገባቸው 12 የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች በተጨማሪ ሌሎችንም ለማስመዝገብ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም መጽሐፈ ድጓንና ባህረ ሀሳብ ወይም አቡሻህርን ለማስመዝገብ ለውድድር ያቀረባቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ናቸው፡፡

አዝጋሚ የነበረው የቱሪዝም እንዱስትሪ ባለፉት 22 ዓመታት ተቀይሯል፡፡ የመሠረተ ልማት መስፋፋትና የማስተዋወቅ ስራ በመስራት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩርት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች ቅርሶቹን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ዘርፉ በፈጣን ሁኔታ እያደገ መጥቷል፡፡ "የቱሪዝም ዕድገት ቀድሞ ከነበረበት የኋሊት ጉዞ በመላቀቅ ዕድገት ማስመዝገብ ጀምሯል" ብለዋል የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ለባህልና ቱሪዝም መጽሔት፡፡ የዕድገቱ ፍጥነት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ባለፉት 5 ዓመታት ሀገራችን የቱሪስት ፍሰት በአማካይ በ12.8 በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡

ይህ ዕድገት በአፍሪካ ደረጃ ፈጣን የሚባል ነው፡፡ እንደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ ከዓመታት በፊት አንድ ብቻ ነበረው የአስጎብኚነት ስራ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ አሁን ዕውቅና የተሰጣቸው 310 የግል አስጎብኚ ድርጅቶች አሉ፡፡ የጎብኚዎችን ደረጃ የሚያሟሉ ሆቴሎቸ፣ ሎጆችና ሪዞርቶች በ1999 ዓ.ም ከነበረበት 157 ወደ 800 ማደጉን የዓለም ባንክ ጥናት ያሳያል፡፡ አዳዲስ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶችም እየተገነቡ መሆኑ ይህ ቁጥር በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያድግ ያሳያል፡፡ ከዘርፉ ሰፊ ስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ብዛት ያላቸው ህብረተሰብ አቀፍ የቱሪዝምና የኢኮ-ቱሪዝም ማህበራትም በየቱሪዝም መደራሻዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡

የቱሪስቶች ቁጥር በየዓመቱ አያደገ ሲሆን በጎርጎሮሳዊያኑ 2012 አሜሪካ፣ ቻይናና እንግሊዝ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጎብኚዎችን በመላክ ሶስቱን ቀዳሚ ስፍራዎች ይዘዋል፡፡ በጎርጎሮሳዊያኑ 2002 ዓ.ም 200  ሺህ እንኳን የማይሞላው የቱሪስቶች ቁጥር በ2012 ወደ 600 ሺህ ከፍ ብሏል፡፡  በውጭ ምንዛሪ ረገድ ደግሞ በጎርጎሮሳዊያኑ 2009 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የነበረው ገቢ ከሶስት አመት በኋላ ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ የሚረዳ ፕሮግራም ወጥቶ እንዲተገበር ተደርጓል፡፡ የቱሪዝም ልማትን ከነበረበት 23 በመቶ ወደ 53 በመቶ ለማድረስ እንዲሁም የቱሪዝም ማርኬቲንግና ፕሞሽን ስራዎችን ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ፡፡

በመጀመሪያዎቹ ሶስት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት ክንውን አፈጻጸም መሰረት በቱሪዝም ልማትና መዳረሻ ልማት ስራዎችን ለማጠናከር የታቀዱ ስራዎች እንዲሁም የቱሪዝም ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ሽፋን ከ80 በመቶ በላይ ተከናውኗል፡፡  በዚህም ከቱሪዝም አንጻር በዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ አንጻር 80 በመቶ የሚሆነው ተሳክቷል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ከባህልና ቱሪዝም መጽሄት ልዩ ዕትም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በዕቅድ ዘመኑ ጉዟችን እጅግ በርካታ ስኬቶችን ያከናወንበትና እንደ ዘርፍ ትስስር የፈጠርንበት ነው" ብለዋል፡፡

በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያሉ መሰረተ ልማቶችን ከመገንባት ባለፈም ያሉትን የማደስ ስራዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ እስከ 12 በሚደርሱ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኤግዝቢሽኖች ላይ በመሳተፍ ያለውን እምቅ ሀብት ለማስተዋወቅ የተጀመረው ጥረትም እየተሰራበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በለንደን ኤግዝቢሽን ምርጥ ተሞክሮ የተወሰደ ሲሆን በቀጣይነት ደግሞ በጣሊያን፣ ጀርመንና ቻይና ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን አቶ ሰለሞን ታደሰ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ለባህልና ቱሪዝም መጽሔት ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት አንድ ሚሊዮን ቱሪስቶችን ለመቀበል የሚደረገው ጥረትና በጎርጎሮሳዊያኑ 2012 ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስት ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ሀገራት መካከል አንዷ ለማድረግ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት የተጀመረው ስራ ግን በቂ አይደለም፡፡

ይህንን እምቅ ሃብት ለመጠቀም በሚንስትሮች ምክር ቤት ነሃሴ 2005 የጸደቀው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ተመስርቷል፡፡ ምክር ቤቱ የሁሉንም ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የማህበራት መሪዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ ሲሆን 68 አባላት አሉት ፡፡

 የኢፌዲሪጠቅላይሚንስትርናየምክርቤቱሰብሳቢአቶኃይለማርያምደሣለኝ"የምክርቤቱዋነኛተልዕኮየሚሆነውየ ቱሪዝምድርጅቱንበበላይነትየሚመራውንቦርድአፈጻጸምመከታተልናድርጅቱእንደሀገርየተሰጠውን ተልዕኮእያከናወነመሆኑንበመገምገም  አቅጣጫማስቀመጥ  ነውብለዋል በምስረታው ላይ፡፡

አሁን ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ የምትሆን ሀገር ናት ፡፡ እስካሁን ድረስ 22 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡ የ24 ብሔራዊ ፓርኮች፤ 4 የዱር እንስሳት መጠለያዎች፤ 18 የዱር እንስሳት ቁጥጥር አደን ቀበሌዎች፤ 7 የዱር እንስሳት መኖሪያ ቀጠና እንዲሁም ብዛት ያላቸው ተፈጥሮአዊ አካባቢ ዎች ባለቤት ናት፡፡ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያና ያልተበረዙ ባህልና እሴቶች ባለቤት መሆኗ ለቀጣይ የቱሪዝም ዕድገቷ ተስፋዎቿ ናቸው፡፡

ለዚህም ነው ዶ/ር ታሌብ "እመኑኝ ትንሽ በመስራት ብዙ ለውጥ ታመጣላችሁ፡፡ደግሞም ትችላላችሁ ዓለምን ሁሉ የሚጣራ ቅርስ ነው ያልችሁ" ያሉት፡፡

2008

በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅቱ የተመሰረተበትን ቀን በማሰብ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓልን መስከረም 17ተከብሯል፡ ፡፡ በዓሉ በየተራ በሚመረጥ ሀገርና መልዕክት በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥም በዓሉ ላለፉት 27 ዓመታት ተከብሯል፡፡ በዓሉ ቱሪዝም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚያበረክተውን ማህበራዊ፤ ባህላዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ፖለቲካዊ ፋይዳዎች ከግምት በማስገባት ይከበራል፡፡ የኢትዮጵያን ሚሊኒየም ተከትሎ በየክልሉ በመዘዋወር  7 ጊዜ ተከብሯል ፡፡   በዚህም መስህቦቹ ባሉበት አካባቢና የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች የቱሪዝም ዕውቀት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡ 

 

  • 2001 በኦሮሚና በጋምቤላ ክልሎች
  • 2002 በሀረሪና ድሬዳዋ ክልሎች
  • 2003 በደቡብ ብሄር ብሀረሰቦችና ህዝቦች ክልል
  • 2004 በትግራይ ክልል
  • 2005 በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል
  • 2006 በአማራ ክልል
  • 2007 በአፋር ክልል
  • 2008 በሱማሌ ክልል   የዓለም ቱሪዝም ቀን ተከብሯል፡፡

 

ኢትዮጵያ በአውሮፓ የቱሪዝምና የንግድ ምክር ቤት የ2015 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻና የባህል ተመራጭ ሀገር በሚል እውቅና  ሓምሌ 3፣2007 በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀበላለች። ምርጫውን ያካሄደው የአውሮፓ የቱሪዝም እና ንግድ ምክር ቤት ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ31 ሀገራት ጋር ተወዳድራ የአሸናፊነት ዘውዱን እንደደፋች ይፋ አድርጓል ። ምክር ቤቱ ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ላላቸው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግንባር ቀደም የአለም ቱሪዝም መሪ በማለት ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

 ምንጭ፡- ኢትዮጵያና የቱሪዝም ሃብቶች