የስኬታማው ቢልየነር ማርክ ዙከርበርግ ያልተሰሙ 11 የስኬት ሚስጢሮች

 

 

የስኬታማው ቢልየነር ማርክ ዙከርበርግ ያልተሰሙ 11 የስኬት ሚስጢሮች

 

እስከ መጋቢት 2015 (እ.ኤ.አ) ድረስ የማርክ ዙከርበርግ ጠቅላላ ሀብት 35.1 ቢሊየን ዶላር እንደሆነ ነው የፎርብስ መጽሔት ዘገባ የሚያመለክተው፡፡ አሜሪካዊው የኮምፒዩተር ፕሮግራመርና የኢንተርኔት ሥራ ፈጣሪ እንዲሁም ከፌስቡክ አምስት መሥራቾች መካከል ዋነኛውና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን እየሠራ የሚገኘው ወጣቱ ቢሊየነር ማርክ ኤሊየት ዙከርበርግ ግንቦት 14 ቀን 1984 (እ.ኤ.አ) ነው የተወለደው፡፡

በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ጓደኞቹ ኤድዋርዶ ሳቬሪን፣ አንድሪው ማክኮለም፣ ደስቲን ሞስኮቪትዝ እና ክሪስ ሂዝ ጋር በመሆን ከማደሪያ ክፍላቸው ሳሉ ነው ፌስቡክን ይፋ ያደረጉት፡፡ ከዛም ወጣቶቹ ድረ-ገጹን በሌሎች ተቋማትም ማስተዋወቅ ከቀጠሉ በኋላ ወደ ካሊፎርኒያ ተሸጋገሩ፡፡

ዕድሜው 23 ሲሞላው፣ ዙከርበርግ የፌስቡክን ተቀባይነትና ስኬት ተከትሎ ወደ ቢሊየነርነት ተሸጋገረ፡፡ በ2012 ብቻ አጠቃላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 ቢሊየን ደርሶ ነበር፡፡

ማርክ ዙከርበርግ ከፌስቡክ መሥራች ጓደኞቹ፣ በተለያዩ ጊዜያት ውዝግቦች ውስጥ ገብቷል፡፡ መሠረታዊው ምክንያትም፣ በፌስቡክ ድርሻ ላይ የነበራቸው አለመግባባት ነው፡፡

ከ2010 ጀምሮ ታይም መጽሔት፣ ዙከርበርግ ከ100 የዓለማችን ሀብታም እና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዱ አድርጎ መርጦታል፡፡ ስያሜው የዓመቱ ቀዳሚው ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ከሚለው ክብር ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡

በ2011 ዙከርበርግ በዓለማችን ላይ ከሚገኙ አይሁዶች ቀዳሚው ተፅእኖ ፈጣሪ ነው ሲለው የኢየሩሳሌም ፖስት መርጦታል፡፡ ዙከርበርግ የስኬት ሕይወቱን የሚተርክ ፊልም በተዋናይ አይስንበርግ ተወክሎ በ2010 ተሠርቶለታል፡፡ ፊልሙ ለኦስካር ጭምር በዕጩነት የቀረበና ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻለ ነው፡፡

ማርክ ዙከርበርግ የተወለደው፣ ከጥርስ ሐኪም አባቱ ኤድዋርድ ዙከርበርግ እና ከሳይካትሪክ እናቱ ካሪን ኤምፕነር በኒውዮርክ ነው፡፡ ረንዲ፣ ዶና እና ኤሪዬሊ ከሚባሉት እህቶቹ ጋርም አድጓል፡፡ ዙከርበርግ አይሁድ በመሆኑም በ13 ዓመቱ እምነቱ የሚፈልጋቸውን ሥርዓቶች ተቀብሏል፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ ጀምሮ የሳይንስ ሽልማቶችን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ለኮሌጅ መግቢያ ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ማርክ የፈረንሳይ፣ የሔብሪው፣ የላቲን እና የቀደምት ግሪክ ቋንቋዎችን መፃፍም ሆነ ማንበብ እንደሚችል ነው አስፍሮ የነበረው፡፡

ማርክ ዙከርበርግ ኮምፒዩተር መጠቀምና ሶፍትዌሮችን መፃፍ የጀመረው የመካከለኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው፡፡ በ1990ዎቹ (እ.ኤ.አ) አባቱ አንዳንድ መሠረታዊ ፕሮግራሞችን እንዳስተማረው ይናገራል፡፡ ከዛም የሶፍትዌር ማበልፀግ ባለሙያ የሆነው ዴቪድ ኒውማን፣ በአስጠኚነት ተቀጥሮለት ብዙ አስተምሮታል፡፡ በወቅቱ ኒውማን የማርክ አስጠኚ ሆኖ መቆየት በራሱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡

ገና በሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት ሳለ፣ በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ይገኝ የነበረው የሜሪሲ ኮሌጅን ተቀላቅሎ፣ የምረቃ ፕሮግራሞችን ተከታትሎ መመረቅ ችሎ ነበር፡፡ በለጋ ዕድሜው የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳደረው ማርክ፣ ለጌሞችና ለግንኙነት መሣሪያዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በአባቱ የጥርስ ማከሚያ ማዕከልና በመኖሪያ ቤታቸው ያሉት ኮምፒዩተሮች፣ መረጃን እንዲለዋወጡ ለማስቻል ‹ዙክ ኔት› ሲል የሰየመውን ፕሮግራም ማዘጋጀት ችሎ ነበር፡፡

ጆሴ አንቶኒዮ ቫርጋስ የተባለው ጸሐፊ፣ በሁኔታው ላይ የዚያ ዘመን ሕፃናት፣ ማርክ በፈጠራቸው ጌሞች ይጫወቱ እንደነበር አሥፍሯል፡፡ ማርክ ዙከርበርግም በዚያ ዕድሜው አርቲስት ጓደኞቹ ይስሏቸው የነበሩ ነገሮችን በቀላሉ ወደ ጌሞች እንዴት ይቀይራቸው እንደነበር ተናግሯል፡፡

በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ከጀመረ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ፕሮግራሞችን በግሉ በመፍጠር ዕውቅና ለማትረፍ ጊዜ አልወሰደበትም ነው ቫርጋስ የሚለው፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ከኮምፒዩተር ሳይንስ በሻገር ሳይኮሎጂንም አጥንቷል፡፡

እንደ ማደሪያ ክፍል ጓደኛው አሪ ሀሲት ገለፃ፣ ማርክ ሰዎች ከቀረቡላቸው ፎቶዎች መልካሞችን መምረጥ የሚችሉበትና ፌስማሽ የተሰኘ ፕሮግራምን እንደ መዝናኛ በማሰብ ነው የፈጠረው፡፡

በተማሪዎች ማደሪያ ውስጥ የሰዎችን ስምና ፎቶዎችን የያዘና ፌስቡክ የተሰኘ መጽሐፍ እንደነበራቸውም ይናገራል አሪ፡፡ ከዚያም ማርክ ሁለት ወንድና ሁለት ሴቶችን አዲስ በገነባው ድረ-ገፅ ላይ በመለጠፍ፣ ማን ይበልጥ ቆንጆና ሳቢ እንደሆነ መረጃውን የሚጎበኙ ሰዎች እንዲመርጡ ማድረግ እና በመጨረሻም ውጤቱን ማስቆጠርም ዓላማ አድርጎ ነበር፡፡

ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን ኮሌጁ ድረ-ገፁን ዘጋው፡፡ ምክንያት ያደረገው ደግሞ የትምህርት ቤቱን ኔትዎርክ ማጨናነቁና ተማሪዎችንም ኢንተርኔት ከመጠቀም ማገዱ ነው፤ በርካታ ተማሪዎችም ፎቶዎቻቸው ያለፈቃዳቸው ጥቅም ላይ በመዋሉ፣ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ ማርክ በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ ተገዷል፡፡

በ2004 ሁለተኛ ሴሚስተር ማርክ ዙከርበርግ፣ ለአዲሱ ዌብሳይት አዲስ ኮድ በማዘጋጀት የካቲት 4 ቀን 2004 በይፋ ፌስቡክን አስተዋወቀ፡፡ ማርክ የጀመረውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ትምህርቱን ማቋረጥ የነበረበት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2014 በድጋሜ ሀርቫርድን በመቀላቀል ትምህርቱን አጠናቋል፡፡

2010 ላይ ዙከርበርግ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች 500 ሚሊዮን መድረሱን ይፋ አድርጓል፡፡ በዛው ዓመት ቫኒቲ ፌር መጽሔት በመረጃ ዕድሜ ከመረጣቸው 100 ሰዎች መካከል ማርክ ዙከርበርግን በአንደኝነት አስቀምጦታል፡፡ በዚሁ መጽሔት የሀብታሞች ዝርዝር ውስጥም የ23ኛ ደረጃን ነበር የያዘው፡፡ በኒውስቴትስ ማን ዓመታዊ ሰርቬይም፣ በ2010 ከ50 የዓለማችን ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል የ16ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ ነበር፡፡ ዙከርበርግ በአንድ የቴክኖሎጂ ኮንፈረንስ ላይ ከኢንተርኔት ጋር የማይተዋወቁ፣ 5 ቢሊዮን ሰዎችን ለመርዳት እየሠራ መሆኑንም ግልፆ ነበር፡፡

ማርክ ዙከርበርግ፣ ምን ዓይነት የፖለቲካ እሳቤ ይኖረው ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ እሱ ግን እስካሁንም ስለ ዝንባሌው ምንም ፍንጭ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ አንዳንዶች ከወግ አጥባቂዎች ጎራ ሲመድቡት ቀሪዎቹ ደግሞ የሊበራል አራማጅ እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ ማርክ በ2013 ለመጀመሪያ ጊዜ ለኒው ጄርሲው አስተዳደሪ ክሪስ ክሪስት ለምርጫ የሚያግዛቸውን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አሰናድቶ ነበር፡፡ ከዛም ለኒውዮርኩ ከንቲባ ኮሪቡክር ለሴኔት ምርጫ የገቢ ማሰባሰቢያ ሌላ ዘመቻም እንዲሁ መርቷል፡፡

የግል ሕይወት

ማርክ አዲስ ተማሪ ሳለ አንስቶ፣ በፍቅር አብሯት ከቆያት ፕሪሲላ ቻን ጋር ነው የሚኖረው፡፡ ቻን ወደ አሜሪካ ከመጡ የቻይና እና የቬትናም ቤተሰቦች በብሬንትሪ ማሳቹሴት ነው የተወለደችው፡፡ በ2012 ማርክ እና ቻን ከምረቃ በዓላቸው ቀን ጎን ለጎን ሠርጋቸውን አከናውነዋል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ በአስገራሚ ሁኔታ እየተለወጠ ነው የሚለው ማርክ የቀጣይ ጊዜ የኢኮኖሚ ደግሞ ዕውቀት ነው የሚሆነው ይላል፡፡ ‹‹ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ኦንላይን ቴክኖሎጂ በማምጣት፣ የቢሊየኖችን ሕይወት ብቻ አይሆንም የምትታደገው፡፡ በሌላ መልኩ እነዚህ አካላት ምርታማነታቸው እና ለዓለም የሚያበረክቱት ነገር ሲጨምር የራሳችንንም ተጠቃሚነት እያሳደግን እንሄዳለን›› የሚል አመለካከት ይዞ ለለውጥ እና ለዓለም መሻሻል ሀብት አዕምሮውን የሚጠቀም ወጣት ነው፡፡

ማርክ ዙከርበርግ የጉግል ፕላስ ማኅበራዊ ትስስር ገፅ ተጠቃሚ ነው፡፡ በ2011 በዚህ ገፅ የጉግልን መሠራቾች ላሪ ፔጂ እና ሠርጄይ ብሪንን በመብለጥ በፌስ ቡክ ላይ ብዙ ተከታዮችን ማፍራት የቻለ ግለሰብ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በ2012 ደረጃው ወደ 84 ወርዷል፡፡ ማርክ በገፁ ላይ አንድ ፎቶ ብቻና ስለራሱ የሚገልጽ መረጃ ብቻ ነው ያስቀመጠው፡፡

ማርክ ዙከርበርግና የበጎ አድራጎት ስራዎቹ

ማርክ ዙከርበርግ፣ ዲያስፓራ ለሚባልና የመረጃ ትስስርን ለማሠራጨት ለሚሠራ ተቋም መጠኑ ያልተገለፀ ገንዘብ ሰጥቷል፡፡ በ2010 በኒውጄርሲ ለሚገኝ ኒዋክ የሕዝብ ትምህርት ቤት አዲስ ለሚቋቋመው የኔትዎርክ ፐብሊክ ትምህርት ቤት 100 ሚሊየን ዶላር ለግሷል፡፡

ዙከርበርግ ከቢሊየኖቹ ቢልጌትስ እና ዋረን ቡፌት ጋር በመሆን በጊዜ ሂደት፣ የሀብታቸውን ግማሽ ለበጎ አድራጎት ሥራ ለመለገስ የሚያስችላቸውንና የስጦታ ቃል ኪዳን ያሉት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ጥር 2013 (እ.ኤ.አ) ዙከርበርግ ለሲሊከን ቫሊይ ኮሙኒቲ ፋውንዴሽን፣ የፌስቡክን 18 ሚሊየን ድርሻ አስተላልፏል፡፡ በወቅቱ የፌስቡክ አጠቃላይ ድርሻ 990 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ይሄ ልግስና በ2013 ተከታዩ የስጦታ መጠኖች በሙሉ በቀዳሚነት የተቀመጠለት ነበር፡፡

ማርክ ዙከርበርግ እና ባለቤቱ ፕሮሲላ ቻን፣ በዛው ዓመት በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በመለገስ ከ50 ሰዎች መካከል በቀዳሚነት በመጽሔቶች ላይ ሰፍረዋል፡፡ የኢቦላ ቫይረስን ለመዋጋት በ2014 ተጀምሮ ለነበረው ጥረትም 25 ሚሊዮን ዶላር ለግሰዋል፡፡

 

የማርክ ዙከርበርግ ያልተሠሙ 12 የስኬት ምስጢሮች

ለመሆኑ ማርክ ዙከርበርግ ፌስ ቡክን በመፍጠር ረገድ ሃሰቡን ከየት አመጣው? በዓለም ላይ ወጣቱ ቢሊየነር በመባል በኮከብነት የሚጠራው ይህ ሰው እንዴት ከምንም ተነስቶ ወደ ወጣት ቢሊየነርነት ተሸጋገረ?

ማርክ ዙከርበርግ ከምንምነት በመነሳት በዓለማችን የቢሊየነሮች ተርታ ውስጥ ለመሰለፍ የቻለ ወጣት ነው፡፡ በአምስት ዓመታት ውስጥ፡፡ አጋጣሚ የፈጠረው ቢሊየነር በሉት ወይም በዕድለኛ አሁን ላለበት ሃብቱ ግን የሚገባው ሰው ነው፡፡

“It is not because of the amount of money for me and my colleagues; the most important thing is that we create an open information flow for people.” Mark Zuckerberg ‹‹ዋናው እና እጅግ ጠቃሚው ነገር ለእኔም ሆነ ለባልደረቦቼ የሠራነው ገንዘብ ሳይሆን ለህዝቡ ነፃ የመረጃ ስርዓት እንዲኖር የፈጠርነው መድረክ ነው፡፡›› የሚለው ማርክ ዙከርበርግ ከቢሊየነርነቱ ይልቅ ትልቁ ነገር ለህዝብ ጥቅም የሠራው ስራ የሚያስደስተው መሆኑን ይናገራል፡፡ ለዚያም ነው ከዚህ መሰሉ በወጣትነቱ ቢሊየነር ከሆነው ማርክ ዙከርበርግ የሚከተለውን አንድንማር የመረጥነውም፤

1. ራዕይ ይኑርህ፡- ብዙ ሰዎች የሚያስቡት ይህ ሰው ከባዶ ሜዳ ተነስቶ ቢሊየነር ሊሆን እንደቻለ ነው፡፡ ፌስቡክንም በቀላሉ በእጅ ጣቶቹ ንክኪ እንደፈጠረውም ያስባሉ፡፡ ይህ ግን የዚህን ሰው ታላቅነት አይገልፀውም፡፡ ማርክ ዙከርበርግ በአንድ ቀን ምሽት የተፈጠረ ሰውም አይደለም፡፡ የሥኬቱና የዝናው ጉዞ የጀመረው በራዕዩ ውስጥ ነው፡፡ ለህዝብ ጥቅምና እድገት የመስራት ፍላጎትና ፍቅር ነው ለዚህ ያበቃው፡፡ በአንድ ወቅት ናፖሊዮን ሒል እንዳለው “ዝነኛና ስኬታማ ለመሆን የሚጀምረው ከእያንዳንዳችን ከፍተኛ ውስጣዊ ፍላጎት ውስጥ ነው፡፡” ይላል፡፡ ታዲያ አንተ ለመሆኑ አሁን ባለህበት ህይወት ውስጥ ምን ሆነህ ራስህን ማግኘት ትፈልጋለህ? በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ራስህን እንዴት ልታገኘው ትሻለህ? በሞት ከተሠናበትክስ በኋላ እንዴት መታወስ ትፈልጋለህ?

2. ትልቅ ደረጃ እንዳትደረስ ትልቅ አሰብ፡- ፌስቡክ በማርክ ዙከርበርግ ኮምፒውተር ወስጥ የተቀረፀ ትንሽ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ለሎችም እንዲሸጡት ጠይቀውት ነበር፡፡ እምቢ አለ እንጂ፡፡ አልሸጥም ብሎ አሻፈረኝ ያለበት ምክንያት ለደከመበት በቂ ገንዘብ ስላልተከፈለው አልነበረም፡፡ ፍላጎቱ ገንዘብ ለሚከፈልበት ስራ መድከሙ ላይ አይደለም፤ ትልቅ ፍላጎቱ ዓለምን መቀየር በትልቁ ማሰቡ እንጂ፡፡ በወቅቱ የፌስቡክ ፕሮጀክት ትንሽ ነበር፤ የወቅቱ የዙከርበርግ ፍላጎት ግን ትልቅ ነበር፡፡ የጓደኞቹ የፌስቡክ ፕሮጀክት በኮሌጅ ደረጃ ብቻ ስሙ ላይ እንዲውል የሚያልም እቅድ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን የዙከርበርግ ፍላጎት ደግሞ ፕሮጀክቱ የዓለም ፕሮጀክት እንዲሆን ነበር፤ ሕዝብ እርስ በእርሱ የሚገናኝበትን ትስስር የሚፈጥርበት፡፡ ሰዎችም በወቅቱ ያስቡ የነበረው የፌስቡክ ፕሮጀክት የሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት አድርገው የነበረ ሲሆን ማርክ ዙከርበርግ ግን ያስብ የነበረው ፕሮጀክቱ የቢሊዮን ዶላር ኩባንያ ሊሆን እንደሚችል ነበር፡፡

እናንተስ አሁን ባላችሁ ትንሽ የንግድ ሃሳብ ውስጥ ምን ይታያችኋል? በቀጣይ አጭር ጊዜያት ውስጥ የዛሬው ትንሽ ቢዝነስ የት የሚደርስ ይመስላችኋል? እያለማችሁ ያላችሁት የሚሊየን ዶላር ኩባንያ ነው ወይስ የቢሊየን ዶላር ኩባንያ? አንድ ነገር ልብ እንበል፤ ስኬት በአንድ ቀን ውስጥ እውን የሚሆን ሳይሆን ትልቅ በማሠብና ለዚህም አዋጭ መድረሻ ስትራቴጂ በመንደፍ ውስጥ ነው!!

 

3. በትንሹ መጀመር፡- ማርክ ዙከርበርግ ትልቅ ህልምና ምርጥ ስትራቴጂያዊ እቅድ አለው፤ ዓለማቀፋዊ የሆነ ፕሮጀክትና በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚያወጣ ዋጋ ያለው የንግድ ሃሳብ በእጁ ላይ እንዳለ ያምናል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዞውን የጀመረው ከትንሹ ነበር፡፡ በዚህ መሠል ትንሽ አጀማመሩም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ በሚሊየን ዶላሮች የሚቆጠርን መነሻ ካፒታል እስኪያገኝ ድረስም ቆሞ አልጠበቀም፡፡ የኮሌጅ በመኖሪያውን (ዶርሚተሪ) አንድ ቢሮ በመጠቀም፤ ያችውን ትንሽ ካፒታል እንደጨው በመገልገልና ያለውን በዛ ያለ የጉልበት፣ የእውቀትና የላብ ዋጋ (sweat eguity) በመጠቀም ነበር የጀመረው፡፡ ሆኖም ማርክ ዙከርበርግ ዛሬ ላይ በዓለማችን ላይ እጅግ በወጣትነት ዕድሜያቸው ከፍተኛ የሃብት ጣሪያ ( ቢሊየነርነት) ላይ ከደረሡ ወጣቶች ውስጥ ቀዳሚው ለመሆን ችሏል፡፡ ከትንሽና ከምንም ጀምሩ እንጂ በፍፁም ፍራት ሊሠማችሁ አይገባም፡፡ እንደውም የንግድ ስኬትና አስደሳች ውጤት ያለው በትንሽ ውስጥ መጀመሩ ላይ ነው፡፡

4. .በራስ መተማመን፡- በየትኛውም ውሳኔ ውስጥ ስኬታማ ሆኖ ለመገኘት በራስ እንደመተማመን ጥሩ ነገር የለም፡፡ ማርክ ዙከርበርግ በዚህ በኩል የሞላው ነበር፡፡ ንግድን መጀመርም ሆነ ወደ ስኬት መለወጥ እንደሚቻል በቅድሚያ በራስ መተማመን ይጠበቅብናል፡፡ ይህንንም ራሳችን ልናሳካው እንደምንችል ጭምር፡፡ ራስህን ጠንካራ ሰው አድርገህ እመንበት፡፡ ፈጣሪ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችል አቅም በውስጥህ እንደ ሰጠህ በማመንም ተጠቀምበት፡፡

5. የውስጥህን የፍቅር ስሜት ተከተለው፡- ምን የበለጠ ብትሰራ ውስጥህን የሚያረካው ይመስልሃል? የውስጥህ ስሜት በሚመራህ ነገር ለመጓዝ ዝግጁ ነህ? ውስጥህ ለሚመራህና ለምታፈቅረው ነገር መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተሃል? የማርክ ዙከርበርግን ዓይነት የስኬት ታሪክ በራስህ ላይ ለመድገም ከፈለግህ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅብሃል፡፡

ማርክ ዙከርበርግ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ፍቅር የነበረው ሲሆን በዚህ ፍቅሩም ቀጥሎበታል፡፡ ሁሉም ሰው የማርክ ዙከርበርግን ስኬታማነት ያፈቅራል፤ ይመኙታልም፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂቶች ብቻ ናቸው ምን ያህል ውስጡ ለሚገዛለት ሙያ ፍቅሩን ለማስቀጠል ሲል የኮሌጅ ትምህርቱን ለማቋረጥ እንደተገደደ የሚያውቁት፡፡ ይህ መሠሉም መስዋዕትነቱ ማርክ ዙከርበርግን በዓለም ላይ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ቢሊየነር መሆን በቻሉ ሰዎች ዝርዝሮች ውስጥ ስሙ እንዲካተት አድርጎታል፡፡ የማይሞት ቁርጠኝነት ከምንም ተነስቶ በቢሊየን የሚቆጠርን ሃብት ለመገንባት ቁልፉ ጉዳይ መሆኑን ታዲያ ዙከርበርግ ያስተምረናል፡፡

6. ለትችት ተዘጋጅ፡- “በእኔ ዙሪያ ከመሞቴ በፊት ማንም ፊልም እንዲሰራብኝ አልመኝም” ይላል ማርክ ዙከበርግ፡፡ እንደየትኛውም ስኬታማ ስራ ፈጠሪ ማርክ ዙከርበርግም ከትችት አልዳነም፡፡ ይሁን እንጂ ትችት ግን ወደኋላ አልመለሰውም፡፡ ትችት እንደውም ወደ ላይ ለመውጣት አስፈላጊ ጉዳይ ሲሆን ይህን ተቀብሎ ወደ ፊት ለመቀጠል ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ትችትን ወደ ስኬት ለመቀየር ዝግጁ መሆንም ይጠበቅብናል፡፡

7. ትጋት ይኑርህ፡- “ትጉ ሰው ሲሰራ ታያላችሁ? ትጉ ሰው በነገስታት ፊት ይቆማል፡፡ በፍፁም ትጉ ስው በደካማ ሰዎች ተርታ አይሰለፍም” ሲል መፅሀፈ ምሳሌ ይናገራል፡፡ መልዕክቱ ግልፅ ነው፤ ከጣፋጭ ስኬቶች በፊት ላብ ቀድሞ እንደሚመጣ ነው፡፡ ማንም ሁለት እጆቹን ኪሱ ውስጥ ከቶ ወደ ላይ መሠላል መውጣት አይችልም፡፡ ሁሉም ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎችና ከኮሌጅ አቋርጠው ቢሊየነር መሆን የቻሉ ስዎች ለስኬታቸው ትልቁ ነገር ጠንክረው መስራታቸው ነው፡፡ ሌሎች ሲተኙ እነሱ ሌሊት እየተነሱ መስራታቸው ጭምር ነው፡፡

8. ታላላቆች ጋር ለመግጠም አትፍራ፡- ማርክ ዙከርበርግ ፌስቡክ እንዲሆን የሚሻው የኢንተርኔት ልብ እንዲሆን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መሠናክል ገጠመው፡፡ ያም በቀላሉ ሊያንቀሳቅሱት የማይችሉት ቋጥኝ ዓይነት የነበረው ጉግል ነው፡፡ ማርክ ዙከርበርግ ጉግል የተባለውን ተፎካካሪ ፊት ለፊት ለመግጠም ፈርቶ ነበርን? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ አልፈራም የሚለው ነበር፡፡ አንዳንዴ እንዳውም ስኬት የሚገኘው ከግዙፎች እግር ስር ነው፡፡ አዎን በአንበሶች ዙሪያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዳፋሮች ብቻ ወደዚህ ያመራሉ፡፡ ለዚያም ነው ድፍረት ከስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች በስተጀርባና ትልቁ የሥኬት ሚስጢራቸው እንደሆነ የሚነገረው፡፡ ያለ ድፍረት የምንወስደው የውሳኔ ድፍረት (Risk) ሊኖር አይችልም፡፡ ያለ ደፋር ውሳኔ ደግሞ ስኬት የለም፡፡ አራት ነጥብ!!

9- ትኩረት ይኑርህ፡- ‹‹በጣም ጥንቃቄ የሚያደርገው ለቆምኩለት ተልዕኮዬ ነው፡፡ ዓለምን ለሁሉም ክፍት ማድረግ ብዬ ለተነሳሁበት ተልዕኮዬ!›› ይላል ማርክ ዙከርበርግ፡፡ ፌስቡክ ለማቋቋም የቻለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? መልሡ ማርክ ዙከርበርግ የፌስቡክን ትልቅ ተል ዕኮ (missions) ለማስፈፀም በትልቁ ትኩረት ያለው ስለነበረ ነው፡፡ ለዚያም ነው የዓለማችን ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች ማለትም ዋረን ባፌት፤ ቢል ጌትስ፣ አንድሪው ካርኒጌ በየጊዜው የትኩረትን ሃይል የምንሠማው፡፡ ያልተከፈለ ልፋት የሚያመጣው ውጤት ትንሽ ነው፡፡ በአንድ ነገር ላይ የተነጣጠረ ልፋት ግን ውጤቱ እጅግ ሃያል ነውና፤ አንድን ነገር ዳር እስክታደርሰው ድረስ በጥረት መስራትን ልመድ፤ ዋረን ባፌት እንደሚለው ‹‹FOCUS፤ Follow One Course Until Successful!››:: አንድሬ ካርኔጌ እንደሚለው ‹‹Concentrate your energy your thoughts and your Capital!››::

10. ሪስክ ለመውሰድ ተማር፡- ‹‹በአሁኑ ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ የድፍረት ውሳኔን በመውሰድ ወደ ስራ የሚገቡ ካሉ ለመውደቅ የደፈሩ መሆን አለባቸው፡፡›› ይላል ታዋቂው ደራሲ ሮበርት ኪየዛኪ፡፡ ድፍረታዊ ውሳኔን (Risk) ተግባራዊ ሳያደርግ ስኬታማ መሆን የቻለ ስራ ፈጣሪ ማግኘት አይቻልም፡፡ ማርክ ዙከርበርግ የፌስቡክን ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ የኮሌጅ ትምህርቱን ሲያቋርጥ በውሳኔው የሚመጣውን ውጤት ለመቀበል፣ አላቅማማም ነበር፡፡ ጉጉልን ፊት ለፊት ሲጋፈጥ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ለመቀበል ‹‹Risk›› ወስዷል፡፡ ፌስቡክን መጀመርም በራሡ እርግጠኛ ባልሆነ የወዳፊት ሂደት ውስጥ የተወሰደ ‹‹Risk›› ወይም ድፍረታዊ ውሳኔ ነው፡፡ ኢንተርፕረነርሽፕ በጥቅሉ በድፍረታዊ ውሳኔ የተመላ ሂደት ነው፡፡ ያለምንም ዓይነት ‹‹ሪስክ›› ዓለም ራሷ ደባሪና የቆመች ትሆናለች፡፡

11. በሂደቱ ውስጥ ቀጥል፡- “ በኢንተርፕረነርሽፕ የጌም ጨዋታ ውስጥ ከወደፊቱ ይልቅ የበለጠ አስደሳች የሚሆነው የሂደቱ ፍሠት ነው፡፡ አንዳንድ ንግድ ስትጀምር የጀመርከው ሂደቱን ወይም ጉዞውን ነው፡፡ በመጀመሪያና መጨረሻ ሂደት ውስጥ የተለያዩ መሠናክሎችን ማለፍ ይጠበቅብሃል፡፡ በመጨረሻ ከመጀመሪያው ተነስተህ ወደ መጨረሻው አሸናፊነት መድረስ የምትችለው እነዚህን በሂደቱ ውስጥ ያሉ መሠናክሎች እያለፍክ ስትጓዝ ነው፡፡” ይላል ሮበርት ኪዮዛኪ፡፡

የሥራ ፈጠራ በራሱ ሂደት ነውና መጀመሩ አንድ ነገር ነው፡፡ በሂደቱ ውስጥ መቆየቱ ደግሞ ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ ፌስቡክ የ24 ሠዓት ስኬት አይደለም፡፡ ስኬቱ የመጣው በየጊዜው በሚከፈለው የሥራ ትጋት ነው፡፡ ማርክ ዙከርበርግ በአንድ ቀን ውስጥም ቢሊየነር መሆን የቻለ አይደለም፡፡ ለዓመታት መስራት ነበረበት ፡፡ አሁንም በመስራት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ነው የሥራ ፈጠራ ጥበብ ትልቁ መንፈስ፤ ወደፊት የመቀጠል ውስጣዊ መንፈስ፡፡

Press on Nothing in the world can take the place of persistence. Talent will not; nothing is more common than unsuccessful men with talent. Genius will not; its the world is full of educated derelicts. Persistence and determination alone are omnipotent!” pay kroc.

በአጠቃላይ ስለማርክ ዙከርበርግ የተለየና ተዓምር የሆነ ነገር የለም፡፡ በዓለም ላይ ወጣት ቢሊየነር ሆኖ ለመውጣት የተለየና ከተለመደው ውጭ የሆነም ነገር የለም፡፡ አሁን ላለበትና ለበቃው ስኬት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ሕልሙ ነበርና፡፡ እቅዱ ነበርና፡፡ የስራውም ውጤት ነበርና፡፡ ውስጡ በነበረው ፍቅር ቀጥሏልና፡፡ ይህንንም ለማሳካትና የፌስቡክ ተልዕኮን ከዳር ለማድረስ በትኩረት ቀጥሏልና፡፡ ለዚያም ነበር በዓለም ላይ በላባቸው /ሳይወርሱ/ በቢሊየነር የሃብት ጣሪያ ላይ ከደረሱ ጥቂት ወጣቶች መሃከል አንዱ ለመሆን የቻለው፡፡ አዎ፤ ስኬቱ ከስራ አንጅ ከዕድለኝነት ጋር አይያያዝምና፡፡ ይህንንም ነው ሁላችንም የምንማረው፡፡

ምንጭ፡- ከስኬት ሚስጥሮች መጽኀፍ የተወሰደ  

 

  

Related Topics