ለመሆኑ የስኳር በሽታ ምንድን ነው

የስኳር በሽታ (Diabetes melitus)

 

ለመሆኑ የስኳር በሽታ ምንድን ነው ?

                 ይህ በሽታ ስኳር ወይም ጉሉኮስ (glucose) በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ሆኖ ሲገኝ የሚከሰት ነው። የዚህ ችግር መንስሄው ከቆሽት (pancreas) የሚመነጨው አንሱሊን (insulin) የተባለው ሆርሞን ( ንጥረ ነገር ) ጭራሽ መጥፋቱ ወይም መጠኑ መቀነሱ፤ ወይም ደግሞ የሚያከናውነው ሥራ ሲሰናከል ነው። ጉሉኮስ ከደም ወደ የአካላት ሕዋሳት (cells) ውስጥ በመግባት ቢያንሰ እንደ ነዳጅ ሆኖ ለሰውነት የሚያገለግል ንጥረ ነገር ወይም የምግብ አይነት ሲሆን፤ ይህንን ለማድረግ የኢንሱሊን መኖር ወይም እንሱሊኑ ሥራውን በሚገባ ማካሄድ አለበት። ጉሉኮስ ከተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ( ለምሳሌ ያህል እንደ ስንዴ ዳቦ፤ እንጀራ፤ ድንች፤ ስኳርነት ያላቸው መጠጦች የመሣሠሉ) ሊግኝ የሚችል አስፈላጊ የሆነ የምግብ ክፍል ነው። መጠኑ በደም ውስጥ ከልክ በላይ እስካልሆነ ድረስ ጎጂነት የለውም። ምግብ ከተወሰደ በኋላ ጉሉኮስ በደም ውስጥ በርከት ብሎ በመገኘት ቆሽት ኢንሱሊንን እንዲያመነጭ አድርጎ ጉሉኮሱ ከጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። ሆኖም ግን በኢንሱሊን እጥረት ወይም የሥራ መሰናከል የተነሳ ጉሉኮስ በደም ውስጥ በብዛት እንዲኖር ከሆነ በሰውነት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን በማምጣት መታመምን ያስከትላል። ስለሆነም የጉሉኮስን የደም መጠን ማስተካከሉ ሕመምን የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም ለመቆየት የሚረዳ ነው።

የተለያዩ የሰኳር በሽታ አይነቶች አሉ ?

          መነሻቸውን አስመልክቶ የተለያዩ የስኳር በሽታዎች መኖራቸው የተመዘገበ ሲሆን፤ ዋናዎቹ  ሦስት ናቸው። እነሱም፦

·      አይነት አንድ፤

·      አይንት ሁለትና

·      በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታዎች ናቸው።

                አይነት አንድ፡ የስኳር በሽታ በቆሽት መጎዳት የተነሳ ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ እንደሚገባው መኖር ባለመቻሉ የሚከሰት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከልጅነት ጀምሮ የሚኖር በሸታ ነው። ከመቶ ውስጥ ከ 5 እስከ 10 እጅ የሆኑ የስኳር በሽተኞች በዚህ አይነቱ ሕመም የሚሰቃዩ ናቸው። እርግጠኛም ባይሆንም ይህ የስኳር በሽታ በዘር ሊተላለፍ የሚችል ለመሆኑ አንዳንድ ፍንጮች አሉ።

               የስኳር በሽታ አይነት ሁለት ከጊዜ በኋላ የሚከሰት ሆኖ ሣለ ከቆሽት የሚመነጨው ኢንሱሉን ሥራውን እንደሚገባው ሊሠራ ባለመቻሉና ቀጥሎም መጠኑ በማነሱ ጭምር የሚመጣ ሕመም ነው። ከመቶ ውስጥ ከ 90 እስከ 95 እጅ የሆኑ የስኳር ሕሙማን በዚህ አይነቱ የስኳር በሽታ የተያዙ ናቸው። ይህም የስኳር በሽታ በዘር የመተላለፍ ፀባይ አለው።

              በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የሽኳር በሽታ ደግሞ እስከ 7 እጅ (7%) የሆኑ ነፍሰጡሮችን የሚያጋጥም ነው። ይህ ሕመም በእርግዝና ጊዜ ተደጋግሞ የመታየት ፀባይ ሲኖረው በዘር ስለመተላለፊፉ ጎዳይ በውል የታወቀ አይደለም። ሆኖም ግን ሕመሙ በእርግዝና ወቅት ያጋጠማቸው ነብሰጡሮች ከወለዱ በኋላ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ሊይዛቸው እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

         የስኳር በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?ሁሉም የስኳር በሽታ አይነቶች ተወራራሽ የሆኑ ጸባዮችን የሚያሳዩ ቢሆንም እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆኑ ልዩ የመለያ ምልክቶች አሏቸው። ከዚህም ሌላ የእያንዳንዱ የሕመም ምልክቶች እንደ በሽተኛው ሁኔታ ሊለያዩ ይችላሉ።

ከዋናዎቹ የአይነት አንድ የስኳር በሽታ ምልክቶች መካከል

·      ቶሎቶሎ(አዘውትሮ) መሽናት

·      በብዛት ውሃ መጠጣት

·      የአፍ መድረቅ

·      ቶሎቶሎ መራብ

·      በብዛት ክብደት መቀነስ (መክሳት)

·      አዘውትሮ በሆነው ባልሆነው መበሳጨት

·       የድካም ስሜት

·      የአይን ግርዶሽ ይገኙበታል።

እነዚህ ምልክቶች በድንገት ወይም ጊዜ ሳይወሰዱ ሊከሰቱ የሚችሉ ይሆናሉ።

ቀጥሎ የሰፈሩት የአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ዋነኛ ምልክቶች ናቸው።

vከላይ የሰፈሩት የአይነት አንድ ምልክቶች ሁሉም ወይም በከፊል ለዚህም የሚያገለግሉ ናቸው። ሆኖም ግን በአይነት ሁለት በሽታ እነዚህ ምልክቶች የሚታዩት መለስ ባለ ሁኔታ ነው።

·      በተደጋጋሚ ተላላፊ በሆኑ የበሽታ አይነቶች (infections) መያዝ

·      ከቁስል በቶሎ ለመዳን አለመቻል

·      እግርና እጅ ከሚያቃጠልና ከሚያደንዘዝ ስሜት መሰቃየት

·      በተደጋጋሚ በቆዳ፤ በአፍ (ወይም በጥርስ ) እና በኩላሊት በሽታዎች መያዝ

ሌላ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ብዙ የሆኑ የአይነት ሁለት የስኳር በሽተኞች ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች በግልጽ ሳያሳዩ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ ነው። የደማቸው የስኳር መጠን ከፍ ያለ ቢሆንም እነዚህ በሽተኞች መያዛቸውን ሳያውቁ በበሽታው ሊጉዱ የሚቸሉ ናቸው። በርግዝና ወቅት የሚፈጠረው የስኳር ሕመም ብዙውን ጊዜ ከሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ጋር ተቀራራቢ የሆኑ ምልክቶችን የሚያሳይ ነው። ከዚህ ጋር በማገናዘብ በሽተኞቹ በብዛት በውሃ መጠማትን፤ ሽንት መሽናትንና መራብን የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ። ይህ ሕመም በትክክል መኖሩ የሚታወቀው ግን የደምና የሽንት ስኳር ( የጉሉኮስ ) መጠን ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ነው።

        የስኳር በሽታ ጥንቃቄ ሳይደረግለት እንዲቀጥል ከተደረገ ምን ችግሮችን ያስከትላል ? ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ከተደረግ በሽታው በተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን በማምጣት ከፍተኛ የጤንነት መጓደልን ያስከትላል። የረጅም ጊዜ ዋነኛ ችግሮች ተብለው የተመደቡት ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው።

·      የደም መዘዋወሪያ ቧንቧን በመጉዳት የደም ብዛት ወይም ግፊት የመጨመር በሽታን ማምጣት

·      የልብ በሽታ መከሰት

·      የአይን በሽታን(Diabetic Retinopathy) ብሎም መታወርን ማስከተል

·      የኩላሊት በሽታን(Diabetic Nephropathy) ማምጣት ወይም ማባባሰ

·      የነርቭ በሽታና(Diabetic Neuropathy) ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች ማስከተል

·      የደም መዘዋወርን ችግር በእግርና በሊሎች አካላት ውስጥ ፈጥሮ የተያያዙ ጉዳቶችን ማስከተል፤ በተለይም ደግሞ ለእግር መታመምና መቆረጥ ምክንያት መሆን

·      ከመድረቅ አንስቶ የተለያዩ የቆዳ ህመሞችን መፍጠር

·       በአንጉል ውስጥ ደም የመፍሰስ ወይም የመርጋት ችግር መፍጠር

         እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የረጅም ጊዜ ችግሮች በተለይ ሊኖሩ የሚችሉት አይነት አንድና ሁለት የስኳር በሽታ ባላቸው ሕመምተኞች ላይ ነው።ሆኖም ግን ችግሮቹ በሁሉም በሽተኞች በአንድ ጊዜ በእኩል ደረጃ ላይታዩ ይችላሉ።በነዚህ ሕመሞች የተነሳ የስኳር በሽተኞች ከጤነኞች ስዎች ጋር ሲነጻጸሩ የመሞት እድላቸው ቢያንስ እጥፍ እንደሚሆን ተመዝግቧል። በእርግዝና ጊዜ የሚፈጠረው የስኳር ሕመም ጥንቃቄ ሳይወሰድ እንዲቀጥል ከተደረገ ማሕፀን ውስጥ ያለው ልጅ ከመጠን በላይ የመወፈር(የማደግ) እድል ይኖረዋል።በዚህም ምክንያት በወሊድ ወቅት ህጻኑ ትልቅ በመሆኑ ከማሕፀን የመውጣት ችግር ይኖረዋል።ብልሃት ሳይታከልበት በግድ እንዲወለድ ከተደረገ በህጻኑ ሰውነትና በእናቱም ማሕፀን ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። የዚህ ዓይነቱን ችግር ለማቃለል በሆስፒታል አካባቢ ብዙውን ጊዜ ልጆች በቀዶ ጥገና እንዲወለዱ ይደረጋሉ። ለወደፊቱም ቢሆን የዚህ አይነቱ ችግር ያላቸው እናቶችም ሆኑ ልጆች (ሁሉም ባይሆኑ) ቢያንስ በአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ሊታመሙ ይችላሉ።

                           ለስኳር በሽታ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጠንቆች (risk factors) አሉ።አይነት አንድን በተመለከተ የተረጋገጠ ቀጥተኛ የሆነ ጠቋሚ ምክንያት የለም። ነገር ግን በተዘዋዋሪ ከዚህ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ጥቂት አመልካች ነገሮች አሉ። እነሱም

·      በቤተሰብ ውስጥ ሕመሙ ቀደም ብሎ መታየቱ

·       ለአንዳንድ የጀርም አይነቶች (ቫይረስ) መጋለጥ

·      በትውልድ ጊዜ ልጆች ለአንዳንድ የበሽታ አይነቶች መጋለጥ ናቸው ።

አይነት ሁለትን አስመልክቶ የአንዳንድ ሰዎች በበሽታው የመያዝ ወይም ያለመያዝ ምክንያቶች በግልፅ የታወቁ ባይሆኑም፤ ቀጥሎ የሰፈሩት ጉዳዮች ብዙ ሰዎች በሽታውን በግልፅ ለማሳየታቸው በምክንያትነት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።

ü ሕመሙ በቤተሰብ ውስጥ መኖር-የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) አለማድረግ

ü ዉፍረት ወይም ክብደት ከሚገባ በላይ መጨመር

ü በእድሜ መግፋት

ü  የደም ስኳር (ጉሉኮስ) ፤

ü የመጥፎ ኮሌስትሮል (LDL) እና የሌላ የመጥፎ ቅባት አይነት መጠን መጨመር

ü በርግዝና ወቅት በስኳር በሽታ መታመም

ü  ክብደቱ ከፍተኛ  (ከ 4 ኪሎ በላይ) የሆነ ልጅ መውለድ

ü የደም ብዛት ወይም ግፊት ከመጠን በላይ ሆኖ መገኘት

ü  የልብ በሽታ መኖር በእርግዝና ጊዜ የሚታየው የስኳር በሸታ ብዙውን ጊዜ ከታች ከተገለፁት ጠቋሚ ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ü ነፍሰጡሯ ከ 25 ዓመት በላይ እድሜ ያላት

ü  በቤተሰብ ውስጥ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ መኖሩ ወይም ወደዚያ የሚያመራ ሁኔታ መፈጡሩ

ü ቀደም ብሎ በእርግዝና ወቅት ለተመሳሳይ ችግር መጋለጥ

ü  ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ውፍረት ወይም ክብደት መኖር

         የስኳር በሽታንና ጠንቆቹን እንዴት ለመከላከል ወይም እንዳይባባሱ ለማደረግ ይቻላል?የትኛውም አይነት የስኳር በሽታ ቢሆን የሕመሙ ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የሕክምና አዋቂን ማየት አስፈላጊ ነው።ስለዚህ ምልክቶቹን ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው።ነገር ግን ምልክቶቹ በግልፅ ሲይታዩ፤በተለይ አይነት ሁለትን የስኳር በሽታ አስመልክቶ፤ ለረጅም ጊዜ ህመሙ ሊኖር ስለሚችል አልፎ አልፎ የጥንቃቄ ምርመራ ማድረግ መለመድ ያለበት ጉዳይ ነው። ይሄ እርምጃ በተለይ አሰፈላጊነቱ ቀደም ብሎ የተጠቀሱት ጠቋሚ ነገሮች በሚኖሩበት ወቅት ነው። እነዚህ ጥንቃቄዎች በጊዜ ከተወሰዱ እንደ በሽታው አይነት ሕመሙን ለመከላከል፤ ለማዘግየት ወይም ደግሞ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚቻል ነው። ይህ ከተደረገ ሕመምተኛውን መርዳት ብቻ ሳይሆን በበሽታው ጠንቅ ለሕክምና ተብሎ ሊወጣ የሚችለውን ክፍተኛ የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ይቻላል።

             አንዳንድ የምርምር ጥረቶች እየተካሄዱ እንዳሉ ቢታወቅም አይነት አንድን የስኳር በሽታ ለመከላከል እስካሁን የሚቻል አልሆነም።ሆኖም ግን በመድኃኒትና (ኢንሱሊን) ሌሎች ለጤንነት የሚበጁ እርምጃዎችን በመውሰድ በሽታው የሚያስከትለውን የአካል ጉዳት መቀነስና እድሜን ማራዘም ይቻላል። በአንፃሩ አይነት ሁለት በሸታን በጊዜ አስፈላጊ የሆኑ ለጤና ጠቀሜታ ያላቸውን እርምጃዎች በመውሰድ ከተወሰዱ በሽታውን ለመከላከል ወይም ማዘግየት ይቻላል።ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች የሚጠበቀውን ውጤት ለመስጠት ብቁ ሆነው ካልተገኙ በሽታኛው በመድኃኒቶችም ጭምር ሊታገዝ ይገባዋል።በእርግዝና ወቅት የሚከስተውን የስኳር በሽታ መከላከል የሚቻል ቢመስልም የዚህ እርምጃ አስተማማኝነት አጠራጣሪ ነው። ስለሆነም ብዙውን ጊዜ መድኃኒቶችና ሌሎች ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አብረው መወሰድ ይኖርባቸዋል። ቀጥሎ የተመለከቱ ለሶስቱም የስኳር በሽታ አይነቶች መደረግ ያለባቸው መሠረታዊ ጠቃሚ ነገሮች ናቸው።

vየደምን የስኳር መጠን መከታተል።ይህ የበሽታውን ሁኔታ ለማወቅ የሚረዳ መሠረታዊ መረጃ ሰጪ ተግባር ነው ። ቀጥሎ ሊወስድ የሚገባውን እርምጃ ጠቋሚ ሊሆን የሚችል ነው። RBS

vጤነኛ የሆነ ምግብ መመገብ። ይህ ምግብ አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት የያዘ ሆኖ ፤ ስኳርነትና ቅባት ነክ የሆኑ ነገሮች ያልበዛበት ቢሆን ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።ሆኖም እንደ አሣ ዘይት፤ ተልባ፤ የወይራ ዘይት የመሳሰሉት በዚህ የሚጠቃለሉ እንዳልሆኑ መጠቀሰ አለበት። ተጣርተው ከተፈጩ የእህል ዘሮች ይልቅ ገለባማ የሆኑት ለምግብነት ይመረጣሉ። በማዕድ ወቅት ምግብም ሲወሰድ በአንዴ ብዙ ከመመገብ ይልቅ ከፋፍሎ በየጊዜው መመገቡ የተሻለ ውጤት አለው።

vተገቢ በሆነ የሰውነት ክብደት ወይም ውፍረት ላይ መገኘት

v አዘውትሮ የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) መሥራት። ለምሳሌ ያህል በየቀኑ ግማሽ ሰዓት በመውስድ በሳምንት ውስጥ ለአምስት ቀናት ያህል መሮጥ

vሲጋራ ወይም ትንባሆ ነክ የሆኑ ነገሮችን አለመጠቀም

vለተላላፊ በሽታ መከላከያ ተብለው የተሰጡትን ክትባቶች መውሰድ

vየአልኮል ነክ የሆኑ መጠጦችን አለመጠጣት

vጨው በብዛት አለመጠቀም፤ በሰውነት ላይም ጭንቀት የሚያመጡ ነገሮችን በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ማስወገድ፤ በቂ የሆነ እቅልፍ ማግኘት

v የእግርና የጥርስን ጤንነት መንከባከብ

vከሁሉም በላይ ስለ ጤንነት ሁኔታ አጠቃላይ ግንዛቤ ለማግኘት በየጊዜው በሕክምና አዋቂ መመርመር።ይህ ድርጊት ቀደም ብሎ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጠቃሚ ነው።

           ምርምር የሚደርግባቸው ነገሮች ብዛትና አይነት እንደ በሽታውና በሽተኛው ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የደምን የስኳር ( ጉሉኮስን ) ፤ የኮሊስትሮልን፤ የደም ብዛትን (ግፊትን) መጠንና የአይንን ጤንነት፤ የልብን አሰራር፤ የኩላሊትን ጤንነትና የእግርን ደህንነት የሚመለከት ሊሆን የሚችል ነው።

            የስኳ በሽታን በምግብ፤ በሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) እና በሌሎች ለጤንነት ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ለመቆጣጠር ካልተቻለ ሕመምተኛው መድኃኒት መውሰድ አለበት። የሚወሰደው መድኅኒት መጠንና አይነት እንደ በሽታውና በሽተኛው ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ቢያንስ ቀጥሎ የተጠቀሱት መድኅኒቶች መሠረታዊ ናቸው።

vለአይነት አንድና ለነፍሰጡር የስኳር በሽታ በመርፌ መልክ የሚወሰዱ የተለያዩ የኢንሱሊን ዝግጅቶች

vለአይነት ሁለት የስኳር በሽታ በአፍ የሚወሰዱ የተለያዩ መድኅኒቶች ለብቻቸው ወይም ከኢንሱሊን ጋር የሚወሰዱ ናቸው።

             እነዚህ መድኅኒቶች የበሽተኛውን የደም ስኳር(ጉሉኮስ) መጠን ለማስተካከል ተብለው የሚወሰዱ ናቸው። ህመምተኛው ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ካሉት (ለምሳሌ እንደ ደም ብዛት (ግፊት)፤ የኩላሊት ሕመም ፤ የልብ ሕመም፤ የኮሊስትሮል መብዛት የመሳሰሉ) ለነዚህም የሚሆኑ ተጨማሪ መድኅኒቶች እንዲወስዱ ይታዘዛል። ብዙውንም ጊዜ አንዳንዶቹ መድኅኒቶቹ ተጓድኝ የሆኑ ሕመሞች ከመታየታቸው በፊት ለመከላከል ተብለው የሚወሰዱ ናቸው። መድኅኒቶችን ከመጠቀም ውጬ እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችም ለስኳር ሕመምተኛው የሚሰጡበት ጊዜ አለ። የደም የስኳር ( ጉሉኮስ ) መጠንን ለመቀነስ ( ለማስተካከል ) ተብለው በሐኪም የሚታዘዙ መድኅኒቶች አንድንዴ ስኳሩን ከሚፈለገው በላይ ሊቀንሱ HYPOGLYCEMIA ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚሆነው መድኅኒቶቹ ከመጠን በላይ ከተወሰዱ፤ ምግብ ሳይበላ ሆድ ባዶ ከሆነና በፍጥነት የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) በሚሰራበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ሕመምተኛው ያልበዋል፤ ይርበዋል፤ ይንቀጠቀጣል፤ ይደክመዋል፤ ያዞረዋል፤ ልቡ በብዛት ይመታል፤ ራስምታት ይይዘዋል ፤ አይኑን ይጋርደዋል ፤ ያበሳጨዋል፤ ንግግሩንም ይይዘዋል ፤ አዙሮት ሊወድቅ ይችላል። የዚህ አይነት ስሚቶች ሲጀምሩ ቶሎ ብሎ ስኳርነት ያላቸው ለስላሳ መጠቶች (ምሳሌ፤ ሰኳርነት ያላቸው የአትክልት ጭማቂዎች፤ ኮካ ኮላ የመሳሰሉ ) ወይም የሚበሉ ነገሮች ( ምሳሌ፤ እነደ ከረሜላና ሰኳር ራሱን የመሳሰሉ ) መወሰድ አለባቸው። ለዚህ አይነቱ ችግር መጠባበቂያ እነዚህን ነገሮች በቅርብ ማስቀመጡ ጠቃሚ ነው።

                  በተቃራኒው የስኳር በሽታ ያላቸው ሰዎች የሚገባውን መድኃኒት ሳይወስዱ ስኳርነት ያለው ምግብ ወይም መጠጥ በብዛት ከወሰዱ ወይንም ደግሞ ለአንዳንድ ለተለዩ የበሽታ አይነቶች ከተጋለጡ የሰውነታቸው የስኳር ( ጉሉኮስ ) መጠን በጣም ከፍ HYPERGLYCEMIA ሊል ይችላል። በዚህን ጊዜ፤ ሕመምተኞቹ የማቅለሽለሽ፤ የመበሳጨት፤ የመራብ፤ አዘውትሮ የመሽናት፤ የመጠጣት፤ የመድከም፤ ያለማተኮር፤ የአይን ግርዶሽና የአፍ መድረቅ ስሜት ወይም ችግር ይኖራቸዋል። ለዚህ ችግር መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ሳይዘገዩ አስፈላጊውን መድኃኒት መውሰድና ምግብን ወይም መጠጥን ማስተካከል ነው። አንዳንድ የስኳር በሽታ ሕመምተኞች፤ በተለይ አይነት አንድ በሽታ ያለባቸው፤ በሰውነታቸው ዉሰጥ የኢንሱሉን እጥረት ወይም እጦት ምክንያት ጉሉኮስን ከመጠቀም ይልቅ ሰዉነታቸው ( ፋት ) ነክ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ለመጠቀም ይገደዳል። ይህ ሁኔታ ለሰውነት ጉጂ ሊሆኑ የሚችሉ ኬሚካሎች (ማለት፡ ኬቶንስ (ketone bodies) የተባሉ ) በብዛት እንዲፈጠሩ በማድረግ የሚከተሉትን የጤንነት ችግሮች ሊያሰከትል ይችላል።

·      የሆድ ህመም ማምጣት

·       ማቅለሽለሽና ብሎም ማስታወክ

·       ክብደት መቀነስ ወይም መክሳት

·       ድካም ማምጣት

·       ትኩሳት መኖር

·      ትንፋሽ ወደ ሽቶ መሳይ ነገር መቀየር በኬቶንሰ ከመጠን በላይ በሰውነት ውሰጥ መከማቸት የተነሳ እነዚህ ችግሮች እየጨመሩ ከመጡ በአፋጣኝ የሕክምና አዋቂን ማየት አሰፈላጊ ነው።

ማጠቃለያ

 

              እስካሁን እንደተገለፀው የስኳር በሽታ የብዙ ሰዎች ችግር እየሆነ የመጣ በሽታ እንደሆነ ታምኗል። የዚህ በሽታ ሕመምተኛ ሆኖ መኖር ቀላል አይደለም፤ በተለይም አይነት አንድ የሰኳር በሸታ ላለባቸው። ከማንም በላይ በሽታው የሚመለከተው ሕመምተኛውን እራሱን መሆኑ ታውቆ ሃላፊነቱን በመውሰድ በተቻለ መጠን በጤንነት ለመኖር የሚቻለው ነገር ሁሉ መደረግ አለበት። በዚህ የጽሑፍ ዝግጅት ለዚህ ሃላፊነት የሚረዱ ዋና ዋና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ተገልፀዋል። ሕመምተኛውም ሆነ የሚያክመው የሕክምና አዋቂ ከሚያደርጉት ጥረቶች በተጨማሪ ችግሩ በዚህ ብቻ ውሱን ሰላልሆነ የሌሎችም ትብብርና ድጋፍ የሚያስፈልገው ነው። ከሌሎች አገሮች ልምድ ለማወቅ እንደሚቻለው በዚህ ተግባር ላይ ያተኮሩ የድጋፍ ወይም የመረዳጃ ድርጅቶች ቢቋቋሙ በተቀናጀና ጠቀም ባለ መልክ ለሕመምተኞች ተቃሚ አገልግሎት ለመስጠት ይቻላል ። ችግሩ ሰፋ ተደርጎ ሲታይ የስኳር በሽታ የግለሰቦች የጤንነት ቀውሰ ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ሊነካ የሚችል የሶሻልና የኢኮኖሚም ችግር ጭምር መሆኑ መታወሰ ይኖርበታል። በዚህ መሰረት ሰፊው የሕብረተሰብ ክፍል የስኳር በሽታን ችግር ለመቆጣጠር ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባና እንደሚችልም መጠቆም አለበት ።

ምንጭ፦Our Golden Health

 

  

Related Topics