ኢትዮጵያዊው የፈጠራ ባለሙያና የአይ.ቢ.ኤም ተመራማሪ

 

Dr Solomon Assefa IBM Researcher

 

አይ.ቢ.ኤም (International Business Machines) ላለፉት 50 አመታት ባሳየው የአቋም ጥንካሬ እንዲሁም ከገቢ አኳያ ትልቁ የመረጃ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ለመሆን የቻለ ነው። ኩባንያው ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል በትእዛዝ የተዘጋጁ ማይክሮቺፕሶችን በሀርድዌርና ሶፍትዌር መልኩ ለተገልጋዮች ያቀርባል። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የአፕሊኬሽን ሶፍትዌሮች በማዘጋጀት ይታወቃል። በዚህም በርካታ ባለሀብቶችንና ኩባንያዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል። በሌላ መልኩ ደግሞ ይህ ኩባንያ ከDigital Equipment Coopration እና ከHorse Power የተባሉ አንጋፋ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪም ነው። ኩባንያው ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ ዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ አገልግሎት፣ ዓለም ዓቀፍ የንግድ አገልግሎት፣ ሲስተም ቴክኖሎጂ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ፋይናንሲንግ ተጠቃሾች ናቸው። አይ.ቢ.ኤም (IBM) ወይም በሌላ መጠሪያው ቶማስ ዋትሰን የምርምር ማዕከል ልክ እንደተግባሩ በውስጡ በርካታ ሰራተኞችን የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 316‚000 የሚጠጉ ሰራተኞችን በስሩ አቅፋል። ከእነዚህ ሰራተኞች መካከል ኢትዮጵያዊው ዶክተር ሰለሞን አሰፋ አንዱ ነው። ዶክተር ሰለሞን ትውልዱ እና እድገቱ በአዲስ አበባ ሲሆን እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበት ስፍራ ከሚገኝ የቀድሞው ድል በትግል የአሁኑ ICS (International Community School) የተሰኘ ትምህርት ቤት ውስጥ ተከታትሏል። በመቀጠልም ወደ አሜሪካን ሀገር በመሄድ የመጀመሪያ ዲግሪውን በፊዚክስ፣ የሁለተኛ ዲግሪውን (ማስተርሱን) ደግሞ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪግና ኮምፒውተር ሳይንስ በማጥናት የከፍተኛ ትምህርቱን እስከ ፒ.ኤች.ዲ (PHD) ድረስ በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት በመከታተል በርካታ እቅዶቹን አሳክቷል።

Hawassa Online Articles: Ethiopian Scientist Dr Solomon Assefa

የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርት እንደሚስበው የሚናገረው ዶክተር ሰለሞን አቅሙን ከተረዱት የትምህርት ቤቱ ፕሮፌሰር እና በዙርያው የሚገኙት የስራ ባልደረባዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ የማይለየው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ አርአያ አድርጎ የሚከተለው ታላቅ ወንድሙ የሚሰጠውን ድጋፍና ፅናት እንደ ህይወቱ መመሪያ ይጠቀምበታል። የአይ.ቢ.ኤም (International Business Machines) ተመራማሪና የምርምር ስታፍ አባል የሆነው ዶክተር ሰለሞን አሜሪካን ሀገር የሚገኘውን አይ.ቢ.ኤም ኩባንያ የተቀላቀለው 2004 ላይ ሲሆን የMIT Technology Review መፅሄት እድሜያቸው ከሰላሳ አምስት አመት በታች የሆኑ የዓለማችን ምርጥ ሰላሳ አምስት የፈጠራ ባለቤቶች ተፅዕኖ ፈጣሪ በሚል ዝርዝር ባወጣው እትም ላይ አካቶታል።እርግጥ ነው ዶክተር ሰለሞን የበርካታ ፈጠራ ስራዎች ባለቤት ሲሆን ለዚህ እጩነት ያበቃው የፈጠራ ስራ የሚያተኩረው ሀይል ቆጣቢ እና ፈጣን የሆነ ሱፐር ኮምፒውተር የኤሌክትሪክ ሲግናልን ከመጠቀም ይልቅ ቺፕስን በመጠቀም ማሻሻል ሲሆን ይህ ግኝት አሁን ካለው አንድ ሺህ እጥፍ ፍጥነት ያለውም ነው። በሌላ በኩል የአይ.ቢ.ኤም (IBM) ሳይንቲስት የሆኑት ዩሪ ቭላሶቭ፣  ዊልያም ግሪን እና ኢትዮጵያዊው ዶክተር ሰለሞን አሰፋ በመሆን በጋራ ያፈሩት ኮሞስ የተባለው አዲሱ ቴክኖሎጂ አስር አመት የጥናት እድሜን የፈጀ ሲሆን ይህ ቴክኖሎጂ የኮምፒውተር ቺፕሶች በተሻለና በላቀ መልኩ እንዲሰሩ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ፣ አሁን ከምንጠቀምበት አስር እጥፍ ያህል የላቀ አገልግሎትና ፍጥነት አለው።

Hawassa Online Science articles

 

ቴክኖሎጂው በሲራዊ መሳሪያን (Optical devices) በማዋሀድና በቀጥታ ወደ ሲልከን ቺፕስ በመውሰድ የሚሰጠውን ውጤት በመጠቀም፣ እንዲሁም በርካታ የሲልከን ናኖ ኦፕቲክስን ውጤቶች በማካተት የተሰራ ሲሆን እነርሱም ክምክም (modulator) ፣ ጀርማኒየም ፎቶዲቴክተር እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ሞገድን ያጠቃልላል። ይህ የቴክኖሎጂ ግኝት የኮምፒውተር ቺፕሶችን ፍጥነታቸውን ከመጨመር ባሻገርም የአይ.ቢ.ኤም ኩባንያ ስኬትን አንድ እርምጃ ወደፊት ያስኬደ ውጤት ነው። የበርካታ ተግባራት ተሳታፊና ውጤታማው ዶክተር ሰለሞን ወደ ሰላሳ ስምንት ገደማ የሚደርሱ ሳይንሳዊ ፅሁፎች ላይ በምክትል ፀሀፊነት የተሳተፈ ሲሆን በዓለማችን የተካሄዱ በርካታ የኮንፈረንስ ዝግጅቶች ላይ ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ትርጉም የሚሰጡና አስገራሚ ንግግሮችንም በማድረግ ይታወቃል። The Wall Street Journal, BBC News, Forbes, Technology Review, እንዲሁም EE Times የተሰኙ አንጋፋ የመገናኛ ብዙሀን ጣቢያዎች ላይ በርካታ ፅሁፎችንም በቋሚነት ይፅፋል። ትጋቱም የተለያዩ የማህበረሰባዊ ተቋማትንና ሳይንሳዊ መዋቅሮችን እንዲያንቀሳቅስና በቴክኖሎጂ የሚፈቱ ማንኛውም አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ውጤቶችን ለማፍራት ረድቶታል። ሳይንሳዊ ብቃቱንና ዕውቀቱን በመጠቀም United nations childrens fund የሚል ስያሜ ያለው የበጎ አድራጎት ማህበርን ለመርዳት፣ የአይ.ቢ.ኤም ተመራማሪዎችን በማሰባሰብና ፕሮጀክት በመቅረፅ በአፍሪካ የሚገኙ በሚሊዮን ደረጃ የሚቆጠሩ የተቸገሩ ህፃናትን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ የማህበራዊ መረብን በመዘርጋት የበጎ አድራጎት ተግባር ላይም ተሳታፊ ነው። ዶክተር ሰለሞን ከቀረፃቸው ፕሮጀክቶች መካከል በUNICEF ስር የሚገኝ U-report የተባለ ሲስተምን በመዘርጋት በስልክ አማካኝነት የፅሁፍ መልዕክትን በመለዋወጥ ዩጋንዳ ውስጥ የሚገኙ ህፃናቶችና ወጣቶችን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ምን እንደሚያጋጥማቸው መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ዘዴ ነው። ከዚህም በዘለለ መልኩ ይህ የመረጃ መንሸራሸር 240‚000 በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችን የያዘ ሲሆን ጠቀሜታውም ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና የተለያዩ ብዝበዛዎችን ለማስቀረት የሚደረግ ከፍተኛ ጥረት ነው።

 

ዶክተር ሰለሞን ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ኢንጅነሪንግ ተቋም፣ የአሜሪካን በሲራዊ ማህበረሰብ እንዲሁም የአሜሪካን ፊዚክስ ማህበረሰብ አባል ሲሆን፣ በሲራዊ የፋይበር ኮንፈረንስ እና ጨረር አመንጪ መሳሪያና ኤሌክትሮ-በሲር ኮንፈረንስ ላይ የኮሚቴ ሀላፊ እና የወርክሾፕ አዘጋጅ በመሆን የነቃ ተሳትፎን አድርጓል። ዶክተር ሰለሞን ስትራቴጂካዊ የሆነ ሀሳብ የማመንጨት ችሎታውን በመጠቀምና ከአይ.ቢ.ኤም የስራ አስፈፃሚዎችና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ሳይንስና ቴክኖሎጂን ባማከለ መልኩ የገበያን እድገት ለማሳካት በፕሮግራም ማናጀርነት ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል። ከዚህም በዘለለ መልኩ በአፍሪካ የመጀመሪያ የአይ.ቢ.ኤም ቅርንጫፍ ወይም አጋር ኩባንያ የሆነው የኬንያ አይ.ቢ.ኤም የምርምር ላብራቶሪ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው ሲሆን እነዚህ ምሳሌያዊ ተግባራቱ በርካታ ሽልማቶችን መረከብም ችሏል። ይህ ተግባሩ ለበርካታ ሽልማቶች ባለቤት እንዲሆን የረዳው ሲሆን ለምሳሌ ያህል ቴክኒካዊ አፈፃፀም ሽልማት እና የማህበራት የእውቅና ሽልማት እንዲሁም አይ.ቢ.ኤም ኩባንያ የሚያዘጋጃቸውን በርካታ የማበረታቻ ሽልማቶችን የግሉ ያደረገ ተመራማሪ ነው።

 

Solomon Assefa

 

በፈረንጆች አቆጣጠር 2013 ላይ ዶክተር ሰለሞን ከዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ወጣት ዓለምዓቀፍ የክብር መሪ በሚል ሽልማቱን ተቀብሏል። ዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም 199 ወጣት ዓለም ዓቀፍ መሪዎች በሚል የተጠቀሱት ግለሰቦች ከ70 የዓለም ሀገራት የተመረጡ ሲሆን፣ 19ኙ ከአፍሪካ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ተወስደዋል፤ ሌሎች አስራሁለት ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እንዲሁም ከሰሜን አፍሪካ የተመረጡ ግለሰቦች ናቸው። የሽልማቱ አላማ እነዚህ ወጣት የዓለም መሪዎች የዓለምን ከተሞች ተግባሮቻቸውንና አርቆ አሳቢነታቸው ያጠናከሩና ያዳበሩ ከተሞችን መፍጠርና ማቆራኘት ሲኖርባቸው፣ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት ዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ወደ 756 ገደማ የሚደርሱ አባላትን የያዘም ነው። የ32 አመቱ ኢትዮጵያዊ ልሂቅ በማለት በርካታ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች ያወደሱት ዶክተር ሰለሞን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ታዳጊ ሀገራት እድገታቸውን ለማፋጠን ሳይንስና ቴክኖሎጂ የራሱ የሆነ ከፍተኛ እድገትን እንደሚቸር የታወቀ ነው። ስለዚም ዶክተር ሰለሞን እና በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዊ የፈጠራ ባለሙያዎች ለሀገራቸው እድገት መሳተፍና የሳይንሱን ዓለም ለመቀላቀል የሚያስችሉ በርካታ ግኝቶቻቸውን ለሀገራቸው እንዲቸሩና መንግስትም ሆነ የግል ባለሀብቶች የተመራማሪዎቹን ህልምና አላማ ተግባር ላይ ለማዋል በማንኛውም መንገድ በመደገፍ ሀላፊነታቸውን መወጣት መቻል አለባቸው።


ምንጭ፡  ሳይንስ ቴክ ቅጽ 1፣ 2006 

 

  

Related Topics