ከሪዮ እንዲቀሩ የተደረጉት አትሌቶች በዓለም አደባባይ ባለድል እየሆኑ ነ

ከሪዮ እንዲቀሩ የተደረጉት አትሌቶች በዓለም አደባባይ ባለድል እየሆኑ ነው

 

 

የሪዮ ኦሊምፒክ ከተጠናቀቀ የስድስት ሳምንታት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ውድድር ወቅት የነበሩ ውዝግቦች ዛሬም ይታወሳሉ፡፡ እንደነ ቀነኒሳ በቀለ የመሳሰሉ አንጋፋ አትሌቶች ተሳትፎ ላይ ሲነሳ የነበረው ውዝግብ ሚዛን እንደደፋ ዘልቋል፡፡ ቀነኒሳም ሆነ አበሩ ከበደ በዚሁ አነጋጋሪ በነበረው ምርጫ ከሪዮ ኦሊምፒክ መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ሁለቱ አትሌቶች ሰሞኑን በተከናወነ ታላቅ ውድድር ላይ ባለድል ሆነዋል፡፡

 

የዓለም በርካታ አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን የሰባበረው ቀነኒሳ፣ ለሪዮ ኦሊምፒክ ሚኒማ (ሰዓት) ባለማሟላቱ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ጋር ሳይካተት መቅረቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በምርጫው ከቀነኒሳ የተሻለ ሰዓት እንደነበራቸው የተነገረላቸው አትሌቶችም ቀነኒሳ በምርጫው እንዲካተት በተጠየቀበት ርቀት የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገቡ ሳይችሉ ሪዮን ተሰናብተዋል፡፡ በወቅቱ አትሌቱ ባለው ልምድና ተሞክሮ ሪዮ ላይ 10,000 ሜትር አገሪቱን እንዲወክል ፌዴሬሽኑን ሲማፀኑ ከነበሩ የቀድሞ አትሌቶች መካከል ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ይጠቀሳል፡፡

 

በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚጠቀሱት ቶኪዮ፣ ቦስተን፣ ለንደን፣ ችካጎና ኒዎዮርክ ማራቶኖች እኩል ደረጃ ያለው በርሊን ማራቶን መስከረም 15 ቀን 2009 ዓ.ም. 41,000 ተሳታፊዎችን አሳትፎ ተከናውኗል፡፡ ኢትዮጵያን ከወከሉ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ ርቀቱን 2፡03፡03 በሆነ ጊዜ አጠናቆ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ቀነኒሳ ያስመዘገበው ሰዓት በርቀቱ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ሲመዘገብለት ይህም ከዓለም ማራቶን ክብረወሰን በስድስት ሰከንድ የዘገየ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይሁንና አትሌቱ ከዚህ በፊት በኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተይዞ የነበረውን 2፡03፡59 ክብረወሰን ማሻሻሉ ታውቋል፡፡

 

በርቀቱ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ኬንያውያኑ ዊልሰን ኪፕሰንግና ኢቫንስ ቼቤት 2፡03፡13 እና 2፡05፡31 በሆነ ጊዜ አጠናቀው ሁለተኛና ሦተኛ በመሆን ሲያጠናቅቁ፣ ኢትዮጵያዊው ሲሳይ ለማ ርቀቱን 2፡06፡56 ሰከንድ ጨርሶ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡

 

በሴቶች መካከል በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ እንስቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡ እንደ ቀነኒሳ ሁሉ በሪዮ ኦሊምፒክ ምርጫ ወቅት በሴቶች ማራቶን መካተት እንደነበረባት ቢነገርም ሳትካተት የቀረችው አበሩ ከበደ ለሦስተኛ ጊዜ የበርሊን ማራቶን ባለድል በመሆን አሸናፊ ሆናለች፡፡ አትሌቷ የገባችበት ሰዓት 2፡20፡45 ሰከንድ ሲሆን፣ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ተከታትለው የገቡት ብርሃኔ ዲባባ እና ሩቲ አጋ ርቀቱን 2፡23፡58 እና 2፡24፡41 ሰከንድ አጠናቀው መሆኑ የአይኤኤኤፍ ዘገባ አመልክቷል፡፡

 

እ.ኤ.አ. በ1974 እንደተጀመረ የሚነገርለት በርሊን ማራቶን በቢኤምደብሊው የመኪና አምራች ኩባንያ ዋና ስፖንሰርነት በዓመት አንድ ጊዜ የሚከናወን የማራቶን ውድድር ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን ዶላር በቀረበበት በዚሁ ውድድር አሸናፊ አትሌቶች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡ በሴቶች ያሸነፈችው አበሩ ከበደ እ.ኤ.አ. በ2010፣ በ2012 እና በ2016 ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ብቸኛዋ እንስት ሆና ተመዝግባለች፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር ቅፅ 22 ቁጥር 17 13