የአስም ህመም ጉዳት ምልክቶች አና ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች

የአስም ህመም ጉዳት ፣ ምልክቶች አና ሊወሰዱ የሚገቡ ቅድመ እና ድህረ ጥንቃቄዎች

 

የአስም በሽታ ሳንባችንን የሚጎዳ የህመም አይነት ሲሆን በዓለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበሽታው ተጠቂዎች ይገኛሉ፡፡ የአስም ህመም በአብዛኛው ከልጅነት ጀምሮ በመከሰት ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄድ የመተንፈሻ አካል ህመም ቢሆንም አልፎ አልፎም ቢሆን እድሜ ከገፋ በኋላም የሚጀምር የህመም አይነት ነው፡፡ ለአስም በሽታ መከሰት ምክንያት የሚሆኑ መንስኤዎች በትክክል ያልተወቁ ሲሆን እስካሁንም ድረስ በሽታው ሙሉ በሙሉ ሊፈውስ የሚችል መድሃኒት አልተገኘም፡፡

 

በአብዘኛው አንድ የቤተሰብ አባል የበሽታው ተጠቂ ከሆነ በዘር የመተላለፍ ባህሪም አለው፡: የአስም በሽታ የሚያጠቃው የሳንባችንን የአየር ቧንቧዎች ሲሆን እነዚህን ቧንቧዎች በማጥበብ እና በቂ አየር ወደ ሳንባችን እንዳይገባና እና እንዳየወጣ በማድረግ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡

 

የአስም በሽታ ምልክቶች

1. ሳል ፡- በተለይም በምሽት ግዜ የሚበረታ
2. ትንፋሽ (አየር) ማጠር
3. የደረት መጨምደድ ወይም መውጋት
4. ደረት አካባቢ በምንተነፍስበት ወቅት የሚሰማ ሲር ሲርታ (Wheezing)

 

የአስም በሽታን ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተጠቅሰዋል ነገር ግን ከሰው ሰው ሊለያዩ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈጋል፡፡

1. ሲጋራ ማጤስ ፡-

ሲጋራ ማጤስ የጤና ጠንቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡በተለይም ለአስም በሽታ ተጠቂዎች ማጨስም ሆነ ሲጋራ የሚጤስበት አካባቢ መሆን በሽታው እንዲቀሰቅስ እና እንዲያገረሽ ያደርጋል፡፡

 

2. የአየር ብክለት ፡-

ከተለያዩ ፋብሪካዎች እና ተሽከርካሪዎች ከሚለቀቁ በካይ ጭሶች እና የአካባቢን አየር ከሚበክሉ ሽታዎች ካላቸው ቆሻሻዎች ተጋላጭነትን ማስወገድ አሊያም መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጉዳይ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በከተማ እና በሃገር ደረጃ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

 

3. በረሮዎች

ጥናቶች እንደሚመለክቱት ከሆነ በረሮዎች እና የሚያመነጩት ብናኝ ለአስም በሽታ መቀስቀስ ምክንያት ናቸው፡፡ በረሮዎች በአብዛኛው በቤታችን የሚገኙ እና ለጤና ጠንቅ ስለሚሆኑ ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡

 

4. የቤት እንስሳት

የቤት እንስሳትን በመኖሪያ ከማኖር ይልቅ ከመኖሪያ ቤት ውጪ ቤት መስራት እና ንጽህናቸውን ጠብቆ ማኖር ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ እንስሳት ብናኝ ስለሚኖራቸው ለአስም ህመም መቀስቀስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

 

5. ከዚህ በተጨማሪ እንደ ጉንፋን ፣ የተለያዩ የሳንባ ህመሞች (ኢንፌክሽኖች) ፣ ቅዝቃዜ ፣ የአየር ለውጥ እና የተለያዩ መኣዛ ያላቸው ሽቶዎች የአስም በሽታን ሊቀሰቅሱ እና እንዲያገረሽ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

 

ሁሉም የአስም በሽታ ተጠቂዎች የህክምና መድሃኒት መውሰድ አይጠበቅባቸውም፡፡ የአስም በሽታን ከላይ የተዘረዘሩትን የበሽታው ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ እና የአካል ብቃት እንቀቅስቃሴ በማድረግ መቆጣጠር ይችላል፡፡የአስም ህክምና መከታተል የጀመረና መድሃኒት የሚወስድ የበሽታው ተጠቂ ሃኪም በሚያዘው መንገድ መድሃኒቶቹን በአግባቡ እና በትክክል መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ወላጆች አስም በሽታ ተጠቂ ከሆኑ ልጆች በሚወልዱበት ግዜ የህክምና ምርመራ እንዲዲርጉ እና በሃኪሞች የሚሰጡ ምክሮችን መከታተል ተገቢ ነው፡፡

Source:http:www.honeliat.com

(በዶክተር ሆነሊያት ኤፍሬም)