የቆዳ ድርቀት በዓየር ጸባይ በእድሜ በምግብ አለመስማማት እንዲሁም

ለጤናዎ - የቆዳ ድርቀትን በቀላሉ ለመከላከል

 

 Image result for የፊት ጥራት

 

የቆዳ ድርቀት በዓየር ጸባይ፣ በእድሜ፣ በምግብ አለመስማማት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል።

ይህ ሁኔታ ሲያጋጥመንም በሰውነት ቆዳችን ላይ የመድረቅ እና የመሰነጣጠቅ ምልክቶች ይታዩበታል።

ይህንን ለመከላከል በርከት ያሉ በፋብሪካዎች ውስጥ የሚዘጋጁ ሎሽኖች የሚመረቱ ሲሆን፥ አንዳንዴ ዋጋቸው ወደድ ብሎብን በቀላሉ ለማግኘት እንቸገራለን።

እኛም ዛሬ ብዙ ገንዘብ ሳያስፈልገን በቀላሉ በቤታችን ውስጥ በማዘጋጀት የቆዳ ድርቀትን የምንከላከልባቸው ዘዴዎችን ልንጠቁማችሁ ወደድን።

ወተት፦ ወተት በውስጡ በያዘው የአንቲኢንፍላማቶሪ ንጥረ ነገር እና ቆዳ አለስላሽ ውህድ አማካይት የቆዳ ድርቀትን እና የማሳከክ ስሜትን በቀላሉ ይከላከላል።

በተጨማሪም ወተት በውስጡ ባለው ላክቲክ አሲድ አማካኝነት በሰውነታችን ላይ የሞቱትን የቆዳ ሴሎች በማስወገድ ለስላሳ እና ጤናማ የሰውነት ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል።

አዘገጃጀት፦አራት የሾርባ ማንኪያ መተት ውስጥ ሁለት የሻይ ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ በማድረግ እንድ ላይ በደንብ ማዋሃድ።

አጠቃቀም፦ ከሎሚ ጭማቂ ጋር ያዋሃድነውን ወተት ሙሉ ሰውነታችንን በመቀባት ለ10 ደቂቃ ያክል እንዲቆይ እድረገን በቀዝቃዛ ውሃ ሰውነታችንን መታጠብ።

ይህንን ውህድ በቀን ሁለት ጊዜ መጠቀም ይመከራል።

ማር፦ ማር በተፈጥሮ ለቆዳ ውበት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ንጥረነገሮችን የያዘ በመሆኑ ለቆዳ ውበት ይመከራል።

ማር በውስጡ አንቲ ኦክሲዳንት፣ አንቲ ማይኮባክቴሪያል እና ቆዳን የሚያለሰልሱ ንጥረ ነገሮችን በመያዙም የቆዳ ድርቀትን ለመከላከል ይረዳል።

በተጨማሪም ማር በውስጡ ጠቃሚ ቪታሚኖችን እና ሚኔራሎችን በመያዙ ለቆዳችን ጤንነት በርካታ ጠቀሜታ አለው።

አጠቃቀም፦ሰውነታችንን ከመታጠባችን በፊት ሁሌም ሰውነታችንን ማር በመቀባት ከ5 እስከ 10 ደቂቃ በሰውነታችን ላይ በማቆየት ከዚያም ገላችንን መታጠብ።

ይህንን በየቀኑ ደጋግመን ከተጠቀምን በቀላሉ ለስላሳ እና ከድርቀት በነጻ የሆነ ቆዳ እንዲኖረን ይረዳናል።

እርጎ፦ እርጎ በውስጡ ባለው ንጥረ ነገሮች አማካኝነት የቆዳ ደርቀትን እንደሚከላከል ይነገርለታል።

በተለይም እርጎ በውስጡ ባለው ላክቲክ አሲድ አማካይነት ቆዳችንን ለድርቀት የሚዳርጉትን ባክቴሪያዎችን እና ጀርሞችን ይከላከላል።

አጠቃቀም፦ እርጎውን በሰውነታችን ላይ በደንብ በመቀባት ቢያንስ ለ10 ደቂቃ ካቆየን በኋላ ሰውነታችንን መታጠብ።

ወይም ደግሞ አንድ ብርጭቆ እርጎ፣ ሶስት ሰሾርባ ማንኪያ የተጨመቀ ፓፓያ፣ እንዲሁም ሁለት ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ እና ሶስት ማንኪያ ማር አንድ ላይ በመደባለቅ በደንብ እንዲዋሃድ ካደረግን በኋላ በሰውነታችን ላይ በመቀባት ለ10 ደቂቃ ያክል በማቆየት በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ፣ ይህንን ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ መጠቀም ይመከራል።

አቮካዶ፦ አቮካዶ በፋቲ አሲድ፣ በቫይታሚን እና በአንቲ ኦክሲዳነት ንጥረ ነገሮች የበለጸገ በመሆኑ የሰውነታችን ቆዳ ከውስጥ በኩል ጤናማ እንዲሆን በማድረግ ድርቀትን ይከላከላል።

አጠቃቀም፦ አቮካዶውን በቆዳችን ላይ በመቀባት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ አቆይተን ሰውነታችንን በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ።

ወይም ግማሽ ብርጭቆ የአቮካዶ ጭማቂ ላይ ግማሽ ብርጭቆ ማር በመጨመር አንድ ላይ በደንብ ካዋሃድን በኋላ ሰውነታችን ላይ በመቀባት እስከ 15 ደቂቃ በማቆየት ሰውነታችንን መታጠብ ይህንን ቢበዛ በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ መጠቀም ይመከራል።

እንዲሁም በቀን አንድ ብርጭቆ የአቮካዶ ጭማቂ በመጠጣት ለቆዳቸን ወዛማነት የሚረዱ ጤናማ ስብ በማግኘት የሰውነታችንን ቆዳ ከድርቀት መከላከል እንችላለን።

 

source : FBC