የወለኔ ህዝብ የባህል ህግ የጎርደነ ሴረ ይባላል፡፡

የወለኔ ብቼ ሴራ የለቅሶ ዳኝነት

 

Image result for ወለኔ

 

የወለኔ ህዝብ የባህል ህግ የጎርደነ ሴረ ይባላል፡፡ ከዚህ የባህል ህግ ውስጥም የብቼ ሴራ ወይም የለቅሶ ዳኝነት አንዱ ነው፡፡ ይህ የዳኝነት ስርዓት በሌሎች ዘንድ ያልተለመደ በመሆኑ ባህሉን ለየት እንዲል ያደርገዋል፡፡

በወለኔ ህዝብ መኖሪያ መንደር ሰው ሲሞት ወዳጅ ዘመን ተሰባስቦ የቀብር ስርዓቱ እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡ የቀብር ስርአቱ ከተከናወነ በኋላም ቀባሪው በሙሉ በአካባቢው ከሚገኝና አመቺ ከሆነ ሜዳማ ስፍራ ላይ ተሰባስቦ ይቀመጣል፡፡ ሁሉም ተረጋግቶ መቀመጡ እንደታወቀም ከሟች ወገን የቤቱ ዋና የተባለው ሰው ተነስቶ እንዲቆም ይደረጋል፡፡ እህት ወንድምና የቅርብ የሚባሉ የቤተሰብ አባላትም ግራና ቀን በመሆን ያጅቡታል፡፡ የቤቱ ዋና የተባለው ሀዘንተኛም ከቀባሪዎቹ ትይዩ በመሆን መልዕክት ማስተላለፍ ይጀምራል፡፡

ዘመዱን በሞት ያጣው ሀዘንተኛ ይህን የሚያደርገው በማህበረሰቡ ዘንድ ማግኘት የሚገባውን መብት እንዳያጣ በማሰብ ነው፡፡ ግለሰቡ የዳኝነት ደንብ ስርአቱን ባይፈፅም ጋብቻ ሊያጣ፣ መታመንን ላያገኝና ጉርብትናና ጓደኝነት ላይፈቀድለት ይችላል፡፡

ሀዘንተኛው በሚያስተላልፈው መልዕክትም ለቀብር ስርአቱ ሁሉም በያለበት ስራውንና ጉዳዩን  በመተው ላሳየው ወገናዊ ፍቅር በሙሉ የአክብሮት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ከዚህ ቆይታ በኋላም ግለሰቡ ወደነበረበት ስፍራ አይመለስም፡፡ የብቼ ሴራ ወይም የዳኝነት ደንብ እንዲሰጠው ተሰብሳቢውን የይሁንታ ማላሽ እስኪያገኝም መቀመጥ አይፈቀድለትም፡፡ በዳኝነቱ ስርአት መሰረትም ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ጎረቤትና የቅርብ የሚባሉ ሰዎች ምስክርነት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

የለቅሶ ዳኝነት ስርአቱ በሚፈቅደው መሰረትም ምስክር ነን የሚሉ ሰዎች ሀዘንተኛው ለሟቹ ቀደም ሲል ያደረገው እንክብካቤ እንዲሁም በጎና ክፉ ድርጊት ስለመኖር ያለመኖሩ በምስክርነት ለማረጋገጥ ቃላቸውን ለመስጠት ይዘጋጃሉ፡፡ የአካባቢው ጎሳ መረም ምስክሮች ሳያዳሉና ሚዛን ሳይስቱ በተገቢው መንገድ መናገር እንደሚኖርባቸው ያሳስባል፡፡ ሀዘንተኛው ለሟች ተገቢ ሚናውን ተወጥቷል? ወይስ ሲበድለው ነበር? በማለትም በአፅንኦት ይጠይቃል፡፡ መስካሪዎቹ ዘመድ ጎረቤትና ሌሎች የቅርብ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነሱም ሟች በህመሙ ጊዜ ስለተጓደለበት እንክብካቤና ስለተመለከቱት በደል የሚያውቁት ካለ ለመመስከር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ከሀዘንተኛው  አስታማሚ ስላዩትና ስለሚያውቁት  በጎ ድርጊትም የለቅሶ ሴራ ወይም የዳኝነት ስርአት ይገባዋል ሲሉ ያረጋግጣሉ፡፡ ምስክሮቹ በሚሰጡት ቃል ላይም ከተሰብሳቢው የተቃውሞ ሀሳብ የመሰንዘር መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

በለቅሶ የዳኝነት ስርአት ላይ ትኩረት የሚሰጣቸው አበይት ነጥቦች ለውይይት ይቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ ሟችን በህመሙ ጊዜ በአግባቡ መንከባከብ ሲገባቸው ችላ ብለውት  ከሆነ፣ከሟች  ጋር ከፍተኛ በሆነ ጸብና በማይፈቅደው ሁኔታ መቋረጡ ከታወቀ  መስካሪዎች  እውነቱን ሳይደብቁ  ይናገራሉ፡፡ ሟች ሀገር ያወቀው አስቸጋሪ ሰው ከነበረም ሞት ነገ በራሳቸውና በዘር ማንዘራቸው እንደሚመጣ በማሰብ እናውቃለን የሚሉትን በሙሉ ሳይደብቁ ይናገራሉ፡፡

የምስክሮችን ቃል በአግባብ ሲያደምጥ የቆየው የጎሳ መሪም የለቅሶ ዳኝነት ደንብ እንዲሰጠው ህዝብ መሀል በቆመው ሀዘንተኛ ላይ የቀረበውን የበጎና የተቃውሞ ምስክርነትን ቃል መሰረት በማድረግ ለውሳኔ ይዘጋጃል፡፡ ከምስክሮች የቀረበው ቃል ግለሰቡ ለሟቹ ተገቢውን ሁሉ ማድረጉን የሚያረጋግጥ ከሆነ እንዲመሰገን፣ አጥፍቶ ከተገኘም እንዲወቀስና እንዲመከር ያደርጋል፡፡ የምክርና የወቀሳው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላም የብቼ ሴራው ወይም የለቅሶ ዳኝነት ደንብ ስርአቱ እንዲሰጥ ይፈቀዳል፡፡

ይህ በወለኔ ህዝብ ዘንድ ለረጅም አመታት የቆየው የለቅሶ ዳኝነት ስርአት የለቅሶ ዳኝነት ስርአት የለቅሶ  ቤት ሀዘን የሚከበር የሚፈራና የሚወደድ ባህል ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡ የዳኝነትን ሹመት ሁሉም የሚሻው ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የምዕረግ ክብር ያለው በመሆኑ በነፃነት ለመናገርና የማህበረሰቡን ስሜት ለማወቅ ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ልማድ  ማንኛውም ወራሽ የሆነ ተወላጅ መብቱን ማስከበር ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም ጭምር መወጣት እንደሚገባው ያስገድዳል፡፡ በተለይም ልጆች ለወላጆቻቸው ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ እንዲሰጡ የሚያደርግ በመሆኑ ስርአቱን ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ምንጭ-አዲስ ዘመን