የጉራጌ ሴቶች በመስቀል

የጉራጌ ሴቶች በመስቀል

 

የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን

ማለትም ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን

መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በእምነቱ

ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል:: ንግሥቲቷ

መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት

ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው

መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ::

የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት

ጠይቃ፣ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት

መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች:: መስቀሉም

ከወራት ቁፋሮ በኋላ ወጥቷል:: ከዚያን ወቅት ጀምሮ

መስከረም 16 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓትና መስከረም

17 የመስቀል በዓል ይከበራል::

በንግሥት እሌኒ አማካይነት ከተቀበረበት የወጣው

መስቀል ክፋይ በሰሜን ኢትዮጵያ በግሸን ማርያም

ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሲሆን፣ በዓሉን ለማክበር ወደ

አካባቢው የሚሄዱ በርካቶች ናቸው::

አዲስ አበባ ውስጥ መስቀል አደባባይ ላይ

ከሚካሄደው ታላቅ የደመራ ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ

በየአድባራቱና በየመኖሪያ ቤት ደጃፍም ደመራ

ይደመራል:: ተመሳሳይ አከባባር በሌሎች ከተሞችም

ይከናወናል:: በየአካባቢያቸው በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎች

በአደይ አበባ ያሸበረቀ ችቦ ደመራ አብርተው በነጋታው

(በመስቀል በዓል ዕለት) ማለዳ ችቦው የበራበት

ቦታ በመሄድ በአመዱ ግንባር ላይ የመስቀል ቅርፅ

የመሥራት ልማድም አለ::

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለ

ሆኖ በየአካባቢው እንደየማኅበረሰቡ ባህልና ወግም

ይከበራል:: ከሌሎች ዐውደ ዓመቶች የመስቀል በዓል

በተለየ በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች የብዙ

ጎብኚዎችን ትኩረትም ይስባል:: በዓሉ በተባበሩት

መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት

(ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም

ቅርስነት የሰፈረውም ለዚሁ ነው::

መስቀል ሲነሳ የጉራጌ ብሔረሰብ ለበዓሉ

የሚሰጠው ልዩ ቦታ ተያይዞ ሊወሳ ይችላል:: የጉራጌ

ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ስለ

በዓሉ አከባበር ባዘጋጀው ጽሑፍ መስቀል፣ ‹‹የመስቀል

በዓል የጉራጌ ብሔረሰብ የበአላት ሁሉ አውራ ሆኖ

ለዘመናት ሲያከብረው የነበረና የሚቀጥልም በዓል

ነው፤›› በማለት ተገልጿል:: ከደመራና መስቀል ቀናት

በፊትና በኋላም በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች የሚከበረው

መስቀል፣ የጉራጌ ተወላጆች ወደቀዬአቸው በመሄድ

በአንድነት የሚያከብሩት በዓል ነው::

የመስቀል በዓል አከባበር ከመስከረም 12 እስከ

ጥቅምት 5 ድረስ በተለያየ ሥነ ሥርዓት የሚቀጥል

ሲሆን፣ ሴቶች ከበዓሉ ዝግጅት ጀምሮ በልዩ ሁኔታ

የሚያከብሯቸው ዕለቶችም አሉ:: መስቀል በጉራጌ

ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም ሰፊ ነው:: የመስቀል

በዓል ከተከበረበት ዕለት ጀምሮ ለሚመጣው ዓመት

መስቀል መሰናዶ ይጀመራል:: ከትውልድ ቀዬአቸው

ርቀው የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለመስቀል በዓል

ቤተሰቦቻቸውን ለመቀላቀል ውሳኔ ላይ የሚደርሱትም

ከወራት በፊት ነው:: ተወላጆቹ የአቅማቸውን ያህል

ገንዘብ አጠራቅመው ወደ ትውልድ መንደራቸው

ያቀናሉ::

ለመስቀል በዓል ዝግጅት ሲደረግ ሥራ በጾታና

በዕድሜ ይከፋፈላል:: በዚህ መሠረት ልጆችና ወጣት

ወንዶች ለደመራ የሚሆን እርጥብ እንጨት ከጫካ

ለቅመው፣ ከደረቀ በኋላ ይፈልጣሉ:: በዕድሜ ከፍ

ያሉት አባወራዎች ደግሞ ለበዓሉ የሚታረዱ ከብቶችን

ሳር በመቀለብ ያደልባሉ::

ሴቶች በበኩላቸው ለሚመጣው መስቀል በዓል

የሚሆን ቅቤ ማጠራቀም የሚጀምሩት የመስቀል

በዓል እንደተጠናቀቀ ነው:: የወራት ዝግጅታቸው ቤት

ማሳመርንም ያካትታል:: በዓሉ ሦስት ወራት ሲቀሩት

መሰናዶውም ይጧጧፋል:: ወጣት ሴቶች ቤት ቀለም

ሲቀቡ፣ የእማወራዎች ድርሻ እንሰት ፍቆ ማዘጋጀትና

ጅባ መሥራት ይሆናል:: በተለይ የቡሔ በዓል ከተከበረ

በኋላ የመሰናዶውን ፍጥነት ይጨምራሉ::

የጉራጌ ሴቶች የመስቀል በዓል መከበር

በሚጀምርበት መስከረም 12 ቀን ለምግብ ማቅረቢያ

የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከግርግዳ ያወርዳሉ:: ዕለቱ

ሌማት ይወርድቦ ቀነ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣

በዕለቱ የመመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም ቤት ይፀዳል::

በየቤቱ አዳዲስ ጅባዎች ይነጠፋሉ:: ቀጣዩ ቀን ወሬት

ያሸና ወይም ወልቀነ ይባላል:: ሴቶች የጎመን ክትፎ

የሚያዘጋጁበት ሲሆን፣ ከቆት የሚበላበት ዕለት በመባል

ይታወቃል::

በጉራጌ ባህል መስከረም 14 ደንጌሳት ይባላል::

የጎመን ክትፎ በሸክላ ጣባ ለመላው ቤተሰብ

የሚቀርብበት ዕለት ነው:: በዕለቱ የሚወጣውን ወጪ

በሙላ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው:: ሴቶች ዓመቱን

በሙሉ ለመስቀል ባጠራቀሙት ገንዘብ ሙሉ ዝግጅቱን

ሸፍነው ቤተሰባቸውን ያስተናግዳሉ:: በደንጌሳት ማታ

በየቤቱ ደመራ ይለኮሳል:: ሥርዓቱ የባዮፕ ኧሳት ቀን

ይባላል:: ደመራው ሲቃጠል ሴቶች እልልታ ያሰማሉ::

ለበዓሉ በሰላም በመድረሳቸውም ፈጣሪን ያመሰግናሉ::

ወከመያ ወይም ጨርቆስ አልያም በሌላ አጠራሩ

የእርድማይ የሚባለው መስከረም 15 ነው:: በዕለቱ

እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለትና ከዚያ በላይ የደለበ

በሬ ያርዳል:: እርዱ ተጠናቆ የከብት ሥጋ ወደ ቤት

እንደገባ ጥሬ ሥጋ በቅቤ ተነክሮ ይበላል:: ቡና በቅቤም

ይጠጣል::

የአካባቢው ማኅበረሰብ በኅብረት ደመራ የሚያበራበት

የባንዳ ኧሳት ወይም የጉርዝ እሳት የሚባለው መስከረም

16 ቀን ይከበራል:: ዕለቱ በየአድባሩ ደመራ የሚበራበትና

ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት ነው:: ትልቁን

ደመራ የማብራት ሥነ ሥርዓት ሲጠናቀቅ በየአካባቢው

መጠነኛ ደመራዎች ይበራሉ:: ደመራው ሥር ይበላል፣

ይጠጣል፣ ይጨፈራል::

ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቆ ወደቤት ከተገባ በኋላ በጣባ

ክትፎ ይበላል:: በነጋታው ንቅባር (የከሰል ማይ) የተባለ

ሥርዓት አለ:: ሥርዓቱ በአንድ አካባቢ ያሉ ዕድርተኞች

ደመራ የተቃጠለበት ቦታ ተሰባስበው ቃል የሚገባቡበት

ነው:: በዕለቱ አዳዲስ የዕድር ዳኞች ይሾሙና ካለፈው

ዓመት ዳኞች ጋር የኃላፊነት ርክክብ ይካሄዳል:: አዳዲስ

የዕድር አባላት ምዝገባም ይኖራል::

መስከረም 18 የፊቃቆማይ ይባላል:: ሴቶች

የተለያዩ የስፌት ቁሳቁሶች ለማዘጋጀት የሚውል

ስንደዶ መልቀም የሚጀምሩበት ነው:: የአካባቢውን

ባህላዊ ዜማ እያሰሙ ስንደዶ ይለቅማሉ:: ከመስከረም

17 እስከ መስከረም 23 ያለው የጀወጀ ወይም የጀወቸ

አማች መጠየቂያ ጊዜ ነው::

በአማች መጠየቂያ ወቅት ሴቶች ለእናቶቻቸው

የፀጉር ቅቤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ይገዛሉ::

ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት ይሸምታሉ:: ወቅቱ ልጆች

በወላጆቻቸው እንዲሁም ባለትዳሮች በአማቾቻቸው

የሚመረቁበትም ነው::

የመስቀል በዓል አከባበርን ከሚያጎሉ ሥርዓቶች

መካከል የአዳብና ባህላዊ ጭፈራ ሥነ ሥርዓት ተጠቃሽ

ነው:: አዳብና ከመስከረም 16 ቀን እስከ ጥቅምት

በዓል ባሉት ቀናት ይከናወናል:: በመገበያያ ቦታዎችና

ሌሎችም የጋራ መሰብሰቢያ ቦታዎች አዳበና ሲጨፈር

ወንዶችና ሴቶች ሎሚ፣ ብርቱካንና ሸንኮራ አገዳ

በመለዋወጥ ይተጫጫሉ::

ወጣቶች ክብ እየሠሩ በሚዘፍኑበትና

በሚጨፍሩበት የአዳብና ሥርዓት ብዙዎች የትዳር

አጋራቸውን ይመርጡበታል:: አንድ ወንድ ለወደዳት

ሴት ሎሚ በመስጠት ፍላጎቱን ያሳውቃል:: የወንዱ

ጓደኞች ስለልጅቷ ማንነት አጥንተው ለቤተሰቦቹ

ያሳውቃሉ:: ከዛም ለሴቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ በመላክ

የጋብቻ ሒደቱ ይቀጥላል::

ባጠቃላይ በበዓሉ ዝግጅትና አከባበርም ሴቶች

ያላቸውን ጉልህ ሚና ማየት ይቻላል:: የበዓሉ

ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ቀላል

አይደለም:: መስቀል በጉራጌ ብሔረሰብ ዓመቱን

ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦችና አብሮ አደጎች

የሚገናኙበት ነው:: በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበትና

ወጣቶች የሚተጫጩበትም ነው::

መስቀል እንደ ዕድር ያሉና ማኅበረሰቡን

የሚያስተሳስሩ መስተጋብሮች የሚጠናከሩበት ወቅት

ነው:: የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት

ኮሙዩኒኬሽን ስለ በዓሉ አከባበር በድረ ገጹ ያሰፈረው

መግለጫ፣ በዓሉ የቀዬው ሰው የሚመራረቅበትና

ስለቀጣይ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዕቅድ የሚወጣበት ነው

ይላል:: በዓሉ በአዲስ ዓመት የሚሠሩ ሥራዎች

እንዴት መከናወን እንዳለባቸው የሚታቀድበት

መሆኑንም ይጠቀሳል::

በመስቀል ስለ ግብርናና ንግድ ሥራ ይወራል::

ወጣቶች ከዕድሜ ባለፀጎች ኃላፊነት ይረከባሉ:: በቢሮው

በተዘጋጀው መግለጫ፣ ‹‹መስቀል ወላጆች ለበዓሉ

የተዘጋጀውን ከብት ከፊታቸው አቁመው ሻኛውንና

ጀርባውን በመዳሰስ ትውልዱን የሚመርቁበት ነው::

ለአገር ሰላምና ብልፅግና ፈጣሪን የሚለምኑበት፣

የተቸገረ የሚጠየቅበት፣ በዳይና ተበዳይ ይቅር

የሚባባሉትም ወቅት ነው፤›› በማለት ተገልጿል::

ምንጭ፡- ሪፖርተር ቅፅ 22 ቁጥር 17 13