አልበሜን ከልጅ እስከ አዋቂ ወደውልኛል

“አልበሜን ከልጅ እስከ አዋቂ ወደውልኛል ”

 

 ተወዳጅነትን እያተረፈ ያለው ወጣት ድምፃዊ

 

በመጀመሪያ አልበሙ፣ በተለይም “ዘመናይ ማርዬ” በተሰኘው ዘፈኑ ተወዳጅነትን ያተረፈው ወጣቱ ድምፃዊ ሚካኤል ታየ (ልጅ ሚካኤል) አድናቂዎቹን በኮንሰርት ፊትለፊት ለማግኘት፤ ዛሬ ምሽት፣ በቦሌ ፋና ፓርክ ይከሰታል፡፡ ኮንሰርቱን ለማሳመር፣ አዘጋጆቹ፣ ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘርና “ሻዴም” ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ደፋ ቀና

ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከልጅ ሚካኤል ጋር በሙዚቃ ህይወቱ፣ ባሳለፋቸው ፈተናዎችና ስኬቶች፣ እንዲሁም በኮንሰርት ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡

 

ለምንድን ነው “ልጅ ሚካኤል” የተባልከው? በቀድሞው ዘመን “ልጅ” የማዕረግ ስያሜ ነበር ብዬ ነው?

እውነት ነው ሙሉ ሥሜ ሚካኤል ታዬ ነው፤ ቅፅል ስሜ ፋፍ ይባላል፡፡ “ልጅ” የሚለው የመጣው ከወንድ አያቴ ጓደኞች ነው፡፡ አያቴ ልጅ ፅጌ ይባል ነበር፡፡ አያቴ ላይ አልደረስኩበትም፤ቀደም ብሎ ነበር ያረፈው ግን ጓደኞቹ ላይ ደርሼባቸው ነበር፡፡ እነሱን ለመጠየቅ ስሄድ፣ ፋፍ የሚለው የቤት ስሜ ስለማይያዝላቸው “የልጅ ፅጌ ልጅ መጣ” ይሉ ነበር፡፡ ከዚያም “ልጅ ሚካኤል” አሉኝ፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንድ ትልልቅ የሆኑ የቤተሰባችን አባላት “ልጅ ሚካኤል” ብለው መጥራት ጀመሩ፡፡ እኔም ለአልበሜ ተጠቀምኩበት፡፡ አንደኛ አገርኛ ነው፤ ሁለተኛ ልጅ የሚለው መጠሪያ የሚሰጥሽ ለአንድ ነገር ስትታጪ (ስትዘጋጂ) ነው፡፡ እንዳልኩሽ አያቴ ልጅ ፅጌ ነበር የሚባለው፤ከዚያ በኋላ ነው የውትድርና ማዕረጐችን ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው እንዲህ አይነት የማዕረግ ስሞች በአገራችን ጥቅም ላይ መዋላቸው እየቀረ በመሆኑ “ልጅ” የሚለውን ለማስቀጠልም ጭምር ነው የምጠቀምበት፡፡

ተወልደህ ያደግኸው እነ ኩኩ ሰብስቤ፣ ፀሐዬ ዮሐንስና ስለሺ ደምሴ የትውልድ አካባቢ በሆነው ጃንሜዳ ነው፡፡ ሰፈሩ ለስፖርት እንጂ ለሙዚቃ ቅርብ አይደለም ይባላል?

እንዳልሺው ጃንሜዳ የስፖርተኞች አካባቢ ነው፤የሚዘወተረውም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንጂ ሙዚቃ አይደለም፡፡ ነገር ግን የጠቀስሻቸው አርቲስቶችም የወጡት ከዚሁ አካባቢ ነው፡፡ እኔ ወደ ሙዚቃ የገባሁት፣ በልጅነቴ በአንዳንድ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ፣ ከዚያም መድረክ በመምራት እንዲሁም ዲጄዎች የሚያጫውቷቸውን ዘፈኖች አብሬ በመዝፈን ነው፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ሙያው እየተሳብኩ መጣሁ፡፡ ይሄው እንግዲህ አሁን እዚህ ደርሻለሁ፡፡

ብዙ ጊዜ ቀን ቀን በሚዘጋጁ የሙዚቃ ፓርቲዎች (day party) ላይ አትጠፋም ነበር ይባላል?

አዎ በዝግጅቶች ላይ ስልሽ ዴይ ፓርቲውን ጭምር ነው፡፡ ዴይ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ካርኒቫሎችም ላይ ጭምር እገኛለሁ፡፡ ዲጄዎች የሚከፍቱትን ሙዚቃ ከዘፋኞቹ እኩል እጫወት ነበር፡፡

ሙዚቃን ሙያዬ ብለህ የያዝከው ከመቼ ጀምሮ ነው?

እንዳልኩሽ በፊት የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ እዘፍን ነበር፤ነገር ግን ብዙ ሰው በተሰበሰበበት መድረክ ላይ ወጥቼ የዘፈንኩት ኢምፔሪያል ሆቴል ነው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ይሆናል፡፡ ትልቅ ዝግጅት ነበር፤ በርካታ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ትልልቅ ኤግዚቢሽኖች ላይ እየተጋበዝኩኝ መዝፈን ጀመርኩኝ ማለት ነው፡፡

አሁን አንተ የተከተልከውና አልበምህንም የሰራህበት ስልት ሂፕሆፕ ነው፡፡ አማርኛና ሂፕሆፕን እንዴት አጣጣምከው? ከዚህ በፊት ብዙ የሙዚቃ ቡድኖች ስልቱን ሞክረው አልዘለቁበትም?

ሂፕሆፕ በአገራችን ጥሩ ስም የለውም፡፡ የዘርፉ ዋና ችግርም ይሄ ነው፡፡

እንዴት ማለት?

ምክንያቱም ሰው ስልቱን ቀጥታ ወስዶ የሚያገናኘው ከምዕራቡ ባህል ጋር ነው፡፡ የምዕራቡን ባህል ስንመለከት፤ሂፕሆፕን የሚጫወቱት ሙዚቀኞች ወይ ስለ አደንዛዥ ዕፅ አሊያም ስለ መጠጥ ወይም ደግሞ ስለ ግድያ ነው የሚያቀነቅኑት፡፡ እነሱ ይህን ይዘት ይዘው ስለሚጓዙ እሱን ወደ አማርኛ ይዘሽ ብትመጪ ማንም አይቀበልሽም፡፡ ከእኛ ባህል ጋር ከፍተኛ ግጭትም ይፈጥራል፡፡ እኔም ሂፕሆፕን ይዤ ስመጣ ትውልድን ለማበላሸት የመጣሁ ተደርጌ ነው የታሰብኩት፡፡ ግን በህዝቡ አልፈርድም፤ የምዕራቡ ሁኔታ በሁሉም አስተሳሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯልና፡፡ እኔ ግን ስልቱ እንዳለ ሆኖ፣የእኛን ወግና ባህል በሚያሞግስና ማንነታችንን በሚያንፀባርቅ መልኩ ነው የሰራሁት፡፡ ከአቀናባሪው ከሁንአንተ ሙሉ ጋርም በጥልቀት አወራንበትና፣ በቃ እኛ የምንፈልገው እርቅ ነው፣ ከማህበረሰቡ ጋር ለመታረቅ ሂፕሆፕን በአገርኛ ለዛ፣ ባህላችንንና ወጋችንን እንዲሁም እየጠፉ ያሉ እሴቶቻችንን በማንሳት ለማቀንቀን ስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ከዛ ምን ተባባልን? የምንሰራው ስራ በህዝቡ ጆሮ ገብቶ ግንባሩን የማያስቋጥር ሊሆን እንደሚገባ ተማመንን፡፡ እናም ሰራነው፡፡ ውጤቱም እንደምታይው በጣም አሪፍ ሆነ፡፡ እግዚያብሔር ይመስገን፡፡

“ዛሬ ይሁን ነገ” የሚለው አልበምህ ከስድስት ወር በፊት ነው ለአድማጭ የቀረበው፡፡ በተለይ “ዘመናይ ማርዬ”፣ “ሳተናው”፣ “ዛሬ ይሁን ነገ” እና ጉራጊኛው በደንብ ታዋቂ አድርገውሃል፡፡ ግጥምና ዜማውን ማን ሰራልህ?

አልበሜን ሙሉውን ግጥም ራሴ ነኝ የሰራሁት፡፡ ዜማውንም ከአቀናባሪው ከሁንአንተ ጋር እየተመካከርን ነው የሰራነው፡፡ እንዳልሽው በተለይ “ዘመናይ ማርዬ” በጣም ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እሱን ዘፈን ለመስራት ትልልቅ ሰዎችን ማግኘት ነበረብኝ፡፡ መጽሐፎችን ማንበብ ነበረብኝ፡፡ “ዘመናይ” ማለት ትርጉሙ ምን እንደሆነ ማወቅ ስለነበረብኝ ማለቴ ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ “ዘመናይ ናት” የምትባል ሴት ምን አይነት ናት? የሚለውንም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡  በእናቶቻችን ወይም አያቶቻችን ጊዜ፤“ዘመናይ ሴቶች” የሚባሉት ደርበብ ያሉና ስልጡን ናቸው፡፡ ለምሳሌ እቴጌ ጣይቱን ስትመለከቺ፣ በአስተሳሰባቸውም በመልካቸውም ዘመናይ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ በዘመናቸው የነቁ፣የሰለጠኑ ሴቶች ዘመናይ ይባሉ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ካረጋገጥኩኝና የቃሉን ትርጓሜ ካወቅሁኝ በኋላ ነው የሰራሁት፡፡ “ማርዬ” ማያያዣ ሆና ግን የነቃ የሰለጠነ፣ ጥሩ አስተሳሰብ ያለው ሰው፤ ያው ጣፋጭ ነው አይደለም?! “ዘመናይ ማርዬ” ከዚህ እሳቤ በመነሳት ተሰርቶ በሂፕሆፕ ስልት ቀረበ፤በጣም ተወደደ፡፡

የሙሉ አልበሙ ተቀባይነት እንዴት ነው?

ተቀባይነቱን በተመለከተ ቆንጆ ነው፡፡ ከምጠብቀው በጣም፣ እጅግ በጣም የበለጠ ነው የሆነብኝ፡፡ አልበሙን ስሰራው አድማጭ እንደማገኝ እጠብቅ ነበር፣ ግን በወጣቱና በታዳጊዎቹ ብቻ ይወሰናል ብዬ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ቤተሰቦች ሁሉ ገብቶ ከምገምተው በላይ አስደምሞኛል፡፡

በተለይ “ዘመናይ ማርዬን” አስመልክቶ ወንዶች እያማረሩ ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ “ልጅ ሚካኤል የስራህን ይስጥህ፤ ሚስቶቻችን፣ ፍቅረኞቻችን ወይ ዘመናይ አሊያም ማርዬ ብለህ ካልጠራኸን እያሉ አስቸግረውናል” ይላሉ ይባላል፡፡  ይህን ነገር ሰምተሃል?

(በጣም እየሳቀ…) በጣም የሚገርምሽ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሰለኝ ያየሁት፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በጣም አክቲቭ የሆኑ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች ያልሺውን ነገር ጽፈውት አይቻለሁ፡፡ በጣም ስስቅ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ከተማው ላይ ስንመለከት፣ ብዙ ጊዜ “ማርዬ ማሬ” ነው የሚባባሉት፡፡ ወንዶቹም “ዘመናይ” ይላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተፅዕኖ መፍጠርና ውጤታማ መሆን ደስ ይላል፤አይደለም እንዴ!?

እንደሰማሁት በሙዚቃው እዚህ ለመድረስ ብዙ ችግሮችንና ውጣ ውረዶችን አልፈሀል፡፡ ከዘመነኞችህ ድምጻውያን የተለየ መስዋዕትነት ከፍያለሁ የምትለው ነገር አለ?

በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፌያለሁ፡፡ የመጀመሪያው በእኛ አገር ሙዚቃዎችን ለመስራት በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በዚህ ላይ አዲስና ጥሩ አመለካከት የሌለውን የሂፕሆፕ ስልት ይዘሽ ስትመጪ፣ችግርሽ ከሌላው እጥፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ ይህን ስልት ይዘሽ ተቀባይነትን ለማግኘት የእያንዳንዱን ሰው በር እያንኳኳሽ  መግባት ግድ ይልሻል፡፡

እኔ እያንዳንዱ ሰው ቤት እያንኳኳሁ፤“ይህንን ነው የምሰራው አግዙኝ” ስል ጥሩ ምላሽ ሳላገኝ ብዙ ደክሜያለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ አይነት ሙዚቃ እዚህ አገር ላይ በምንም ተዓምር ይቀነቀናል ብለው የማያምኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ይህን ጥያቄ ይዤ ስቀርብ ከሚያሳዩኝ የፊት ገጽታ ቢመቱኝ አሊያም ቢናገሩኝ ይሻለኝ ነበር፡፡

 አንዳንዶቹ የሚናገሩሽ፣ ቅስም ይሰብራል፡፡ አንዳንዶቹ አያናግሩኝም፡፡ ይህን ሁሉ አልፌ ሳልሰበር ዓላማዬን ብቻ በማየት፣ አስቸጋሪውንና አባጣ ጐርባጣውን መንገድ አልፌዋለሁ፡፡ በተናገሩኝም ሆነ ፊት ባኮማተሩብኝም እንዲሁም ምላሽ በነፈጉኝ በማናቸውም ላይ ቂም አልያዝኩም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ አሁን ላይ “በጣም ጐበዝ፤ እንዲህ ይሳካል ብለን አልገመትንም ነበር” ይሉኛል፡፡ እኔም የምፈልገው ይሄን የአስተሳሰብ ለውጥ ስለሆነ እደሰታለሁ፡፡

በኮንሰርት ደረጃ ሥራህን ስታቀርብ ዛሬ በቦሌ ፋና ፓርክ የሚካሄደው የመጀመሪያህ ይመስለኛል፡፡ ዝግጅት እንዴት ነው?

እንዳልሺው ኮንሰርት ስሰራ የዛሬው የመጀመሪዬ ነው፡፡ አዘጋጆቹ የጆርካ ኤቨንትስ ኃላፊዎች፣ በስራዬ አምነውበት ነው ለዚህ ትልቅ ነገር ያጩኝ፡፡ ከዜማ ላስታስ ባንድ ጋር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል፡፡ ኮንሰርቱ የመጀመሪያዬ ቢሆንም ለመድረክ አዲስ አይደለሁም፡፡ በዕለቱ የምጠብቀውና የምመኘው፣ከአድናቂዎቼ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቼ፣ በእኔ ሲደሰቱ ማየት ነው፡፡ ኮንሰርቱን አሪፍ ለማድረግ የጆርካ ኤቨንት ኃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም የኮንሰርቱ ሚዲያ አጋር ሻዴም ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሌት ተቀን እየለፉ ቆይተዋል፡፡ ዛሬ እንግዲህ በጣም ጥሩ የሆነ ስራ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ በጣም ነው የጓጓሁት፡፡

ከድምፅ ባሻገር ዳንስ ላይስ እንዴት ነህ?

በጣም የሚገርምሽ ነገር እኔ የዳንስ ሰው አይደለሁም፤ዳንስ አልችልም፡፡ ነገር ግን አሁን አዘጋጆቹ ኮንሰርቱን የተለየ ለማድረግና ህዝቡን ለማስደሰት ስለፈለጉ ዳንስ እንድለማመድ አስገድደውኛል፡፡

ያው ራፕ ወይም ሂፕሆፕ ሲባል ትንሽ ነው ነቅነቅ የምትይው፡፡ ይህንን ለመቀየር ሲባል፣ለምን አትደንስም የሚል ነገር መጣ፡፡ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፤ ልምምድ ላይ ነኝ፤ በጣም ከባድ ነው ብታይ፡፡ ግን እንደ ምንም እየሞከርኩ ነው፡፡

ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ የሙዚቃ አፍቃሪያን የሚያደንቁት አንጋፋ ድምፃዊ እንደመሆኑ፣ ከእርሱ ጋር ኮንሰርት የመስራት እድል ስታገኝ ምን ተሰማህ?

ከሚካኤል በላይነህ ጋር መስራት ያኮራል፡፡ በጣም ጐበዝ፣ በሳልና ሰውን በስራው የሚመዝን መልካም ሰው ነው፡፡ የእኔን ስራ ወደደው፡፡

እሱም ብቻ ሳይሆን እነ ሸዋንዳኝ ሀይሉና ሌሎችም በእነሱ አካባቢ ያሉ ድምፃዊያን ስራዬን ወደውታል፡፡ እሱም ተጠይቆ “ከልጅ ሚካኤል ጋር እሰራለሁ” ሲል በጣም ተደሰትኩ፡፡ በቃ መንገድ ተጀመረ ነው ያልኩት፡፡ ጆርካ ኤቨንስት ናቸው ሄደው ያናገሩት፡፡ እነሱ ከአንተ ጋር የሚዘፍን አሪፍ ሰው አገኘን ሲሉኝና፣ ሚኪ መሆኑን ስሰማ ሰርፕራይዝ ነው የሆንኩት፡፡

የራስህን አልበም ከማውጣትህ በፊት ሌሎች የአማርኛ ዘፈኖችን ወደ ሂፕሆፕ ለውጠህ ትሰራ ነበር?

እንግሊዝኛዎቹን በፊት ዲጄዎች ሲከፍቱ እዘፍን ነበር፡፡ አገርኛ የሆኑ የሌሎች ድምፃዊያንን ዘፈን ግን ዘፍኜ አላውቅም፡፡ አማርኛን በሂፕሆፕ ሀ ብዬ መጫወት የጀመርኩት ራሴ በጻፍኩት ግጥም ነው፡፡

ሂፕሆፕን በአማርኛ ሞክረው ተሳክቶላቸዋል የምትላቸው ድምፃዊያን አሉ? ቀደም ሲል በሂፕሆፕ ስልት የሚጫወቱ የሙዚቃ ቡድኖች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡

ከእኛ በፊት የነበሩ የሙዚቃ ቡድኖች በጣም ታግለዋል፡፡ ለምሳሌ “ሀበሻ ፊኖምና”፣ “አቢሲኒያ ቦይስ”፣ “ማድ ቦይስ” --- የሚባሉ ነበሩ፡፡ “ሀበሻ ፊኖምና” ውስጥ እንደ ሳምቮድ የመሳሰሉ ጐበዝ ልጆች፣ በዚህ የሙዚቃ ስልት ብዙ እርቀት ለመጓዝ ብዙ ፍዳ አይተዋል፡፡ ነገር ግን ሰብረው መውጣት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ማንም አይደግፍሽም፡፡ በፋይናንስም በሞራልም ካልተደገፍሽ ደግሞ የትም መድረስ አትችይም፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ከዘርፉ ወጥተዋል፡፡

አልበም ሲወጣ በአብዛኛው በስፖንሰር ነው የምትደገፊው፡፡ ሂፕሆፕ ሲሆን ማንም ይህን አይቀበልም፡፡ በዚህ ፈተና ውስጥ እኔም እንዳለፍኩ ቀደም ብዬ ነግሬሻለሁ፡፡ ግን ለመስማት እድል ሰጥተው፣ “ይሄማ ጥሩ ነው” ያሉ ናቸው ድጋፍ ያደረጉልኝ፡፡ እንደ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ያሉ የኪነጥበብ አጋሮች ናቸው የደገፉኝ፡፡

በቀጣይ ሂፕሆፕና አማርኛ ተጣጥመው እንዲቀጥሉ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

አሁን በትልቅ ተጋድሎ የተዘጋውን መንገድ ትንሽ ከፍተነዋል፡፡ እንዴትና በምን ሁኔታ መንገዱ ተከፈተ? ለሚለው ዘፈኖቹንና ይዘታቸውን ጠንቅቆ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ከተከተሉ በዚህ ዘርፍ መቀጠል የሚፈልጉ ልጆች ያለ ችግር መግፋት ይችላሉ አማርኛችንን በትክክለኛው መንገድ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ሂፕሆፕ ለመዝፈንና ወደ ምዕራቡ ለመውሰድ አማርኛን አፋቸው ውስጥ የሚያጉላሉት አሉ፡፡ ትክክል አይደለም፡ ለዚያውም እዚሁ ተወልደን አድገን፣አፍ መፍቻችን አማርኛ ሆኖ፣ተገቢ አይመስለኝም የግልም የመንግስትም ት/ቤት ብትማሪ እዚህ አገር ከሆነ፣ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሔረቡልጋ አንድ ፊደል ነው የሰሩት፡፡ ሀሁን ማለት ነው፤ሀሁን ሳንቆጥር አላደግንም፡፡ “ሀ”ን በ“ሀ” ነቱ፣ “ለ”ን በ“ለ” ነቱ እየጠራን፤ ሂፕሆፕ ከዘፈንን የማንወደድበት ምክንያት የለም፤ባህልንም አለባበስንም መጠበቅ፣ራስን መሆን ያስፈልጋል፡ 

አልበምህ ተወዳጅ እየሆነ ሲመጣ፣ የውጭ አገር የኮንሰርት ግብዣዎች አልቀረበልህም? የትዳር ጥያቄዎችስ አልጎረፈልህም?

የትዳሩንማ ተይው፤በጣም ብዙ ነው፡፡ ብቻ ሰው ሲወድሽ ደስ ይላል፡፡ የኮንሰርት ጥያቄዎች ከተለያዩ ቦታዎች በእርግጥ እየመጡ ነው፡፡ ቅድሚያ እዚሁ ላሉት ልስጥ ብዬ ነው፡፡ በንግግር ደረጃ ላይ ያሉ የውጭ ስራዎች አሉ፡፡ በአንድ አገር ብቻ ከሶስትና ከአራት ፕሮሞተሮች በላይ ያነጋግሩኛል፤እሱ ጊዜውን ጠብቆ የሚከናወን ይሆናል፡፡

የአገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አርቲስቱን የሚያበረታታ ነው ወይስ ---- ?

እውነት ለመናገር ኢንዱስትሪው ለእኔ ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እኔ በተወሰነ የእድሜ ክልል ብቻ ተቀባይነትን ጠብቄ፣እያደር ግን ሁሉም ተቀብሎኛል፡፡ ሰው ከወደደሽ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሲስተም ውስጥ ገባሽ ማለት ነው፤ዋናው እኮ ህዝቡ ነው፡፡ እኔ ያበረታታል እላለሁ፤ተቀባይነት ለማግኘት አዲስ ነገር ይዞ መምጣት፣ ስራን ተጠንቅቆና አድማጩን ግምት ውስጥ አስገብቶ መልፋት ያስፈልጋል፡፡

ከውጭ የሂፕሆፕ አቀንቃኞች የምታደንቃቸውና ተፅዕኖ ፈጥረውብኛል የምትላቸው አሉ? 

ከውጭ ተፅዕኖ አሳርፈውብኛል የምላቸው የሉም፤ምክንያቱም 98 በመቶው ቃላታቸው የተበላሸ ነው፡፡ እነሱ እኔ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ አይችሉም፡፡

ታዲያ እንዴት ስልቱን ልትወደውና ልትከተለው ቻልክ?

አልፎ አልፎ ጥሩ ጥሩ የሚናገሩ፣ደህና መልዕክት የሚያስተላልፉና ቁምነገር የተሞላበት ስራ የሚሰሩ አሉ፡፡ እነሱን ስሰማ ውስጤ ይመሰጣል፡፡ ለምሳሌ ቱፓክን እወደዋለሁ፡፡ እሰማው ነበር፡፡ በአብዛኛው ስለ ጭቆና፣ ስለ እናት ፍቅርና መሰል ፋይዳ ያላቸው ነገሮች ነው የሚዘፍነው፡፡ ሌሎችም አሉ፤እነሱን ስሰማ ወደ አገራችን ብናመጣው ብዙ ልንሰራበት እንችላለን በሚል ነው ወደዚህ ስልት ጠልቄ የገባሁት፡፡

በመጨረሻ የምትለው ካለ

በሙዚቃ አልበሜ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውና ለውጤት ያበቁኝ ብዙ ሰዎች አሉ፤ዘርዝሬ አልጨርሳቸውም፡፡ ሁሉንም እግዚአብሔር ያክብርልኝ እላለሁ፡፡

በተለይ አቀናባሪዬ ሁንአንተ፤አዲስ ነገር አድናቂና ተቀባይ ነው፡፡

 በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡ በቀጣይም አዲስ ስራ ይዤ፣ የተሻለ ሰርቼ ህዝቡ የጣለብኝን እምነት እወጣለሁ፡፡ ከሁንአንተ ጋር ብዙ አቅደናል፡፡ የጆርካ ኤቨንት ሃላፊዎችን፣ ሚዲያ ፓርትነራችንን ሻዴምን፣ ስፖንሰሮቻችንንም አመሰግናለሁ፡፡ አዲስ አድማስንም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ በተረፈ----ወደ ኮንሰርቱ ኑ፣ ከእኔም ጋር ተዝናኑ እላለሁ፡፡ 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ