የሥነ ጥበብ ት/ቤት መስራች እና የመጀመሪያው መምህር” አለ ፈለገሰላም

የሥነ ጥበብ ት/ቤት መስራች እና የመጀመሪያው መምህር” አለ ፈለገሰላም

 

“የሥነ ጥበብ ት/ቤት መስራች እና የመጀመሪያው መምህር” አለ ፈለገሰላም

  

ሐምሌ 24 ቀን 1915 ዓ.ም በሰላሌ ፍቼ ከተማ ነው የመጀመሪያ፴ው የስዕል መምህር አባት የሆኑት አለ ፈለገሰላም የተወለዱት፡፡ በአለቃ ኅሩይ ቤት ያደጉት ሰዓሊ አለ፤ የቤተ ክህነት ትምህርት ተምረዋል፡፡ በድቁናም አገልግለዋል፡፡ ቅኔ መማርም ጀምረው ነበር፡፡

በአጎታቸው እምአእለፍ ኅሩይ አማካኝነት ዘመናዊ ትምህርትን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት አሀዱ ብለው ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያውን ደረጃ እስከ 8ኛ ክፍል በተፈሪ መኮንን፣ከዚያም ለአራት አመት በተግባረ ዕድ ት/ቤት ተምረዋል፡፡ በተግባረ ዕድ ረዳት መምህር ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ተግባረ ዕድ ት/ቤት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ የሚስሏቸው ስዕሎች ይወደዱ ስለነበር አንድ ቀን ንጉሰ ነገስቱ ት/ቤቱን በሚጎበኙበት ወቅት የወጣቱን አለ የስዕል ስራዎች ለመመልከት ቻሉ፡፡ ንጉሱ ነገስቱም በተመለከቱት የአለ ስራዎች ተደምመው ከሐገር ውጭ ሄደው በሙያው ከፍተኛ ትምህርት እንዲያጠኑ ሃሳብ አቀረቡላቸው፡፡ 

በዚያው ዓመት አሜሪካ በሚገኘው ቺካጎ ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ ተላኩ፡፡ ከአራት ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ በስነ ጥበብ ተግባር ከቺካጎ ዩንቨርሲቲ የባችለር ኦፍ አርት ዲግሪ ተቀብለው ወደ ሃገራቸው ተመለሱ፡፡ ሀገራቸው ሲመለሱ ንጉሱ ዘንድ ቀርበው እጅ በሚነሱበት ወቅት፤የትና ምን መስራት እንደሚፈልጉም ከንጉሱ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ ሰዓሊው አለ ፈለገሰላምም ማስተማር እንደሚፈልጉ ገለፁላቸው፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ተመድበው ለ13 ዓመት የልጆች መማሪያ መፅሐፍትን ከስዕል ጋር (illustration) በማዘጋጀት ቆዩ፡፡ የማስተማር ፍላጎታቸው ከፍ ያለ ነበርና፣የራስ ደስታን 3 ክፍል ቤት ተከራይተው ገቡ፡፡ እዚያ ቤት ውስጥም በነፃ በግላቸው ቅዳሜና እሁድ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ከተፈሪ መኮንን፣ ከዳግማዊ ምኒልክ፣ ከግርማዊ እቴጌ መነን ለሙያው ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች እንዲማሩ በማድረግ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ወጣት ሰዓሊዎች እንዲፈጠሩ አስችለዋል፡፡

በራስ ደስታ ቤት ውስጥ በግላቸው ያለ ክፍያ ያስተማሯቸውን ተማሪዎች፤በዚያው አመት መጨረሻ ላይ ስራዎቻቸውን በኤግዚቢሽን ለህዝብ እንደሚያሳዩ አደረጉ፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ አምባሳደሮች፣ ንጉሳዊ ቤተሰቦች፣ ዲፕሎማቶች ተገኝተው ነበር፡፡ በተጋባዥ ትብብርና እርካታም ብዙ ስዕሎች ተሸጡ፡፡ በጠቅላላ ወደ 76 ሺህ ብር ከስዕል ሽያጭ አገኙ፡፡ ይህን ገንዘብ ባንክ አስቀምጠው፣የት/ቤቱን ነገር ይወተውቱ ጀመር፡፡ ንጉስ ነገስቱም በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር ለነበሩት ለደራሲ ከበደ ሚካኤል እንዲከታተሉ አድርገው ት/ቤቱ እንዲሰራ ምክንያት ሆነ፡፡ ከኤግዚቢሽኑ ባሰባሰቡት ገንዘብና በመንግስት እገዛ ይህ ዛሬ ድረስ ብቸኛ ሆኖ ያለው የስነጥበብ ት/ቤት ተከፈተ፡፡ ት/ቤቱ በይፋ የተከፈተው በንጉሰ ነገስቱ ልደት ቀን ሐምሌ 16 ስለነበር አለ ፈለገሰላም ባደረጉት ጥሪ መሰረት፤ 150 ሺህ ብር ንጉሠ ነገስቱ ስጦታ እንዲሰጡ አደረጋቸው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር በጀመረው ት/ቤት ውስጥ ብቻቸውን ነበር የሚያስተምሩት፡፡ በኋላ የውጭ ሐገር መምህራንን ቀጥረው ያስተምሩ ጀመር፡፡ ት/ቤቱን ለ16 ዓመታት በመምህርነትና በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ እሣቸው በት/ቤቱ ውስጥ አስተምረዋቸው በኋላም እዛው ት/ቤት ውስጥ እንዲያስተምሩ ካደረጓቸው ሰአሊዎች መካከል ገብረክርሰቶስ ደስታ (ጀርመን ሄዶ እንደሚማርም አድርገዋል) እሰክንድር በጎሲያን፣ ታደሰ ግዛው፣ ወርቁ ጎሹ፣ ወርቁ ማሞ፣ ታደሰ መስፍን ይጠቀሳሉ፡፡

የአለ አያት አለቃ ህሩይ ወ/ጊዮርጊስ ሰዓሊ ነበሩ፡፡ አባታቸውም ፈለገሰላም ሰዓሊ ነበሩ፡፡ አያትየውም በጣም የታወቁ ሰዓሊ በመሆናቸው የእንጦጦ ማርያምና የአራዳ ጊዮርጊስ ውስጥ ያሉ ስዕሎችን እሳቸው ነበር የሣሉት፡፡ የአራዳ ጊዮርጊስ ውስጥ ያለውን ስራቸውን ጣሊያን ቢያቃጥለውም የእንጦጦ ማርያም ስራቸው ግን ዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ አጎታቸው እማዕለፍ ኅሩይም ጎበዝ ሰአሊ ነበሩ፡፡ ጣሊያን የቃጠለውን የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንደገና የሰሩት እማዕለፍ ናቸው፡፡

ሰዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ከስዕል ት/ቤት መመስረትና ማስተማር ጎን ለጎን በርካታ የስዕል ሥራዎች በመስራት፣ በተለያዩ ሐገሮች፡- በአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ግሪክ፣ ዩጎዝላቪያ አሳይተዋል፡፡ ለቤተመንግስትና ለፓርላማ የሰሯቸው በርካታ ስዕሎች አሉ፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ ሀገር ላሉ ታላላቅ አድባራት፣ ካቴድራልና አብያተ-ክርስትያናት የእሳቸው የጥበብ አሻራዎች ናቸው፡፡በ1947 የተሰራው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉልላቱ ላይ ያለውን ጨምሮ ሙሉ የውስጥ ስዕሎች፤ በናዝሬት አዳማ የቅድስት ማሪያምን ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ የጎፋ ገብርኤልን፣ የቁልቢ ገብርኤልን፣ በመርካቶ የቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያንና የመርካቶ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሥዕላትን በመስራት አሻራቸውን ያስቀመጡ ታላቅ የሥነጥበብ ባለሙያ ነበሩ፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ የቅዱስ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያንን ሥዕል በውብ መልኩ የሰሩ ታላቅ ሰዓሊም ናቸው፡፡

ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም፤የኢትዮጵያ ትውፊታዊውንና ዘመናዊ የእውነታ አሳሳልን ያቀናጁ፣ ብሄራዊ ድባብን የተላበሱ፣ስሜትንና ህሊናን የሚስቡና የተረጋጉ ስዕላትን የሚሰሩ ሰዓሊ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ በስራቸውና በባለውለታነታቸው የተለያዩ ሽልማቶችን፣ ሰርተፍኬቶችን  ከንጉሰ ነገስቱ፣ ከተለያዩ የመንግስት ተቋሞች፣ ከውጭ ሀገር አምባሳደሮች ከታዋቂ ምሁራንና ግለሰቦች እጅ ተቀብለዋል፡፡ ለዚህ የህይወት ዘመን ታላቅ ስራቸውም ራሳቸው የመሰረቱት የሥነጥበብ ት/ቤት በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ (በ2007 ዓ.ም “ለበጎ ሰው ሽልማት” ታጭተዋል ተብለው፣በ92 ዓመት ዕድሜያቸው፣በድካምና በህመም ላይ እያሉም  በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ አሸናፊው የእሳቸው ተማሪ ሰዓሊ ታደሰ መስፍን መሆኑ ሲገለፅ ታዲያ ታደሰ፤“እሳቸው እያሉ እኔ በጭራሽ ልሸለም አልገባም” ብሎ ነበር፡፡)

ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም የአንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ አባት ሲሆኑ የሦስት የልጅ ልጆችና የአንድ ልጅ ቅድመ አያት ነበሩ፡፡ 

እኝህ ታላቅ የአገር ባለውለታ ባለፈው ሰኞ በተወለዱ በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ረቡዕ ዕለት በደብረሊባኖስ ገዳም የቀብር ሥነስርዓታቸው ተፈጽሟል፡፡

ምንጭ- አዲስ ዘመን ጋዜጣ