መለያየታችን የፈጠረብኝን ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

መለያየታችን የፈጠረብኝን ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

 

Image result for separate

 

“ለአምስት ዓመት ጓደኛሞች የነበርን ሲሆን ለስድስት ወራት ያህል ደግሞ ስንጠናና ቆይተናል። ከእኔ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማቆም ሲወስን ግን ሊነግረኝ እንኳ አልፈለገም። እንዲሁ በድንገት ዘጋኝ። ነገሩ ስሜቴን በጣም ጎዳው። ልቤ በሐዘን ተሰበረ። ‘ምን አድርጌው ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር።”—ሬቸል

 

ከፍቅር ጓደኛ ጋር መለያየት አንድን ሰው ደስታውን ሊያሳጣውና በሐዘን እንዲዋጥ ሊያደርገው ይችላል። ለሁለት ዓመት ያህል ሲጠናኑ የቆዩትን ጄፍንና ሱዛንን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጄፍና ሱዛን እየተዋደዱ መጡ። ጄፍ በቀን ውስጥ በርካታ የፍቅር መልእክቶችን በሞባይል ይልክላታል። ከዚህም በተጨማሪ እንደሚወዳት ለማሳየት አንዳንድ ጊዜ ስጦታዎች ይሰጣታል። ሱዛን እንዲህ ብላለች፦ “ጄፍ ትኩረት ሰጥቶ የሚያዳምጠኝ ከመሆኑም ሌላ ስሜቴን ይረዳልኝ ነበር። እንዲሁም እንደምወደድ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር።”

 

ብዙም ሳይቆይ ጄፍና ሱዛን ትዳር ስለ መመሥረት ብሎም ከተጋቡ በኋላ ስለሚኖሩበት ቦታ ማውራት ጀመሩ። ሌላው ቀርቶ ጄፍ ቀለበት ሊያስርላት እንዳሰበ ሱዛን አውቃለች። ይሁንና ጄፍ በድንገት ከእሷ ጋር ያለውን ግንኙነት አቆመ! በዚህ ጊዜ ሱዛን ልቧ ተሰበረ። ስሜቷ በጣም በመጎዳቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋን ታከናውን የነበረው በደመ ነፍስ ነበር። “አእምሮዬም ሆነ ሰውነቴ ደንዝዞ ነበር” በማለት ተናግራለች።*

 

መለያየት ልብ የሚሰብረው ለምንድን ነው?

 

አንቺም እንደ ሱዛን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞሽ ከሆነ ‘ይህን ሁኔታ አልፌ እንደ ድሮዬ መሆን እችል ይሆን?’ ብለሽ ራስሽን ትጠይቂ ይሆናል። እንዲህ ቢሰማሽ የሚያስገርም አይደለም። ንጉሥ ሰለሞን “ፍቅር እንደ ሞት የበረታች . . . ናት” ሲል ጽፏል። ከወንድ ጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ በሕይወትሽ ውስጥ ካጋጠሙሽ ሁኔታዎች ሁሉ የበለጠ ስሜትሽን ጎድቶት ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች መለያየት የሞት ያህል ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። አንቺም እንዲህ ይሰማሽ አሊያም ከታች እንደተጠቀሱት ያሉ ሌሎች ስሜቶች ይፈራረቁብሽ ይሆናል።

 

ነገሩን አለመቀበል። ‘በፍጹም ሊሆን አይችልም! ነገ ከነገ ወዲያ ሐሳቡን መቀየሩ አይቀርም።’

 

ንዴት። ‘እንዴት እንዲህ ያደርገኛል? ከአሁን በኋላ ዓይኑን ማየት አልፈልግም!’

 

በጭንቀት መዋጥ። ‘እኔን ማንም አይወደኝም። ከእንግዲህ የሚፈልገኝ አይኖርም።’

 

እውነታውን አምኖ መቀበል። ‘ግንኙነታችን መቋረጡ ስሜቴን የጎዳው ቢሆንም ይህ ሁሉ አልፎ እንደ ድሮው ደህና መሆኔ አይቀርም።’

 

ደስ የሚለው ግን ሁሉም ነገር አልፎ እውነታውን አምነሽ ወደ መቀበል ደረጃ መድረስ የምትችዪ መሆኑ ነው። እርግጥ ነው፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድብሽ ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ ነው፤ በመጠናናት ረጅም ጊዜ ቆይታችሁ ከሆነና በጣም ተቀራርባችሁ ከነበረ መለያየታችሁን ለመቀበል ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድብሽ ይችላል። ታዲያ የተሰበረውን ልብሽን ለመጠገን ምን ማድረግ ትችያለሽ?

 

ሐዘኑን ለመቋቋም የሚረዱ እርምጃዎች

 

ጊዜ የማይሽረው ቁስል እንደሌለ ሲነገር ሰምተሽ ይሆናል። ከወንድ ጓደኛሽ ጋር በተለያየሽ ሰሞን ይህ አባባል ብዙም ትርጉም አይሰጥሽ ይሆናል። ምክንያቱም የጊዜ ማለፍ ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ነገር ቢቆርጥሽ ቁስሉ ከጊዜ በኋላ መዳኑ እንደማይቀር ታውቂያለሽ፤ ያም ቢሆን ግን በወቅቱ ማመሙ አይቀርም። በመሆኑም መድማቱን ለማስቆምና ሕመሙን ለማስታገስ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብሻል። በተጨማሪም ቁስሉ እንዳያመረቅዝ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ። ስሜት በሚጎዳበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ ላይ በውስጥሽ የሚሰማሽ ሥቃይ ይኖራል። ይሁንና ሥቃዩን ለማስታገስ እንዲሁም ቁስሉ እንዳያመረቅዝ በሌላ አባባል በውስጥሽ ጥላቻ እንዳይፈጠር አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችያለሽ። ጊዜ እያለፈ መሄዱ በራሱ የሚያመጣው ለውጥ አለ፤ እስከዚያው ድረስ ግን አንቺ ምን ማድረግ ትችያለሽ? የሚከተሉትን እርምጃዎች ለመውሰድ ሞክሪ፦

 

● ስሜትሽን አምቀሽ አትያዢ። ሐዘንሽ እንዲወጣልሽ ብለሽ ብታለቅሺ ምንም ስህተት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “ለማልቀስ ጊዜ አለው” እንዲሁም “ዋይ ለማለት ጊዜ አለው” ይላል። ማልቀስ የድክመት ምልክት አይደለም። ደፋር ተዋጊ የነበረው ዳዊትም እንኳ ስሜቱ በጣም ተጎድቶ በነበረበት ወቅት “ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤ መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ” ሲል ተናግሯል።

● ጤንነትሽን ተንከባከቢ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ስሜትሽ በመደቆሱ የተሟጠጠው ኃይልሽ እንዲታደስ ይረዳሻል።

ከጤንነትሽ ጋር በተያያዘ ለየትኞቹ ነገሮች ትኩረት መስጠት ያስፈልግሻል?

 

․․․․․

● ራስሽን በተለያዩ ነገሮች አስጠምጂ። የሚያስደስቱሽን ነገሮች ከማድረግ አትቆጠቢ። በተለይ በዚህ ወቅት ራስሽን ማግለል አይኖርብሽም። ከሚያስቡልሽ ሰዎች ጋር መቀራረብሽ አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንድታተኩሪ ይረዳሻል።

 

ምን ዓይነት ግቦች ልታወጪ ትችያለሽ?

 

․․․․․

 

․․․․․

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ

 

መለያየታችሁ ያስከተለው የስሜት ቁስል እንዲሽር ጊዜ ከሰጠሽው በኋላ መለስ ብለሽ ስለነበራችሁ ግንኙነት ማሰብሽ ሊጠቅምሽ ይችላል።

የፍቅር ግንኙነት ስትጀምሪ መጨረሻው ይህ እንደሚሆን እንዳልጠበቅሽ ጥያቄ የለውም። ሆኖም ልትረሺው የማይገባ ነገር አለ፤ ኃይለኛ ዝናብ እየጣለ ባለበት ወቅት በአብዛኛው ትኩረት የምናደርገው በጠቆረው ሰማይና በሚጥለው ዶፍ ላይ ይሆናል። ትንሽ ቆይቶ ግን ዝናቡ ማቆሙና ሰማዩ ጥርት ማለቱ አይቀርም። በተመሳሳይም በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ወጣቶች ያጋጠማቸውን ሁኔታ በጊዜ ሂደት መርሳት ችለዋል። አንቺም እንዲሁ ማድረግ እንደምትችዪ አትጠራጠሪ!

 

ምንጭ፡- የወጣቶች ጥያቄ