የሚወዱትንና የሚያልሙትን ስራ ለማግኘት የስራ አፈላለግ ስልት!

የሚወዱትንና የሚያልሙትን ስራ ለማግኘት የስራ አፈላለግ ስልት!

 

 Image result for ስራ ፍለጋ

 

ማንም ግለሰብ ቢሆን የሚፈልገውንና ያለመውን ስራ ማግኘት ይወዳል። ምክንያቱም ጥሩና ተስማሚ ሥራ ማግኘት ለደመወዝ ብቻ ሳይሆን በራሱ በስራው እርካታ ለማግኘትና እድገት ለመጨመር ነው።

ገና ከጅምሩ ሥራ የማግኘቱን ክፍል ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ እራሱን የቻለ አካሄድና ስልት አለው። ይህ የሥራ አፈላለግ ስልት ውጭ በምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ላይ ያተኮረ ቢሆንም የትም አገር ቢሆን ለማንኛውም ዜጋ ሊጠቅም ይችላል። ምናልባት በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ይህንን የሥራ አሰጣጥና አፈላለግ ስልት ሙሉ በሙሉ ላይጠቀሙበት ይችላሉ። ባደጉ አገሮች ውስጥ ግን ስልቱ የተለመደ ነው፡፡

 

ስለዚህ ማንኛውም ዜጋ አገሩ ውስጥም ሆነ ሌላ አገር ቢኖርም፤ እዚህ ጽሁፍ ላይ የተጠቀሰውን የሥራ አፈላለግ ደንብና ስርአት ቢያውቅ ጠቀሜታ አለው። እርስዎ ይህንን ስልት በተገቢው ከተጠቀሙበት ከአንድ ስራ በላይም ሊያገኙ ስልሚችሉ ስራ መምረጥ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እኔ ባንድ ወቅት ላይ ሁለት ሥራዎች አግኝቼ አንዱን የተሻለውን ልመርጥ ችያለሁ፡፡

 

ይህም ሊሆን የቻለው ሌላ ሥራ ላይ እያለሁ ቢሆንም ሶስት ዓመታት ሙሉ የተሻለ ሥራ ፍለጋ ላይ ነበርኩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ የተለያየ ትምህርት ወስጃለሁ፤ ስህተቶችም ሰርቻለሁ፡፡ የመጀመሪያም ሆነ የተሻለ ሥራ ለማግኘት ቋሚ የሆነ ህግና ደንብ ወይም የስራ አፈላለግ ህግ የለም፡፡ እንደ ሁኔታው ይለያያል፡፡ በግሌ የማውቀውንና የወሰድኩትን ልምድ ለሌሎች ባካፍል ግን በጣም ደስ ይለኛል፡፡

 

እዚህ የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዌ ዌብ ገጽ ላይ የቀረቡት የስራ አፈላለግ ስልቶች በደንብ ተነበው በተገቢው ከተፈፀሙ አንድ ስራ ማግኘት ቀርቶ ስራ ለመምረጥም ጭምር እድል ያሰፋሉ፡፡

እነዚህ ስልቶች የተጻፉት ባንድ ንጋት ምርምር አይደለም፡፡ ውጤትም ለማግኘት ከፈለጉ በስልቶቹ መሰረት ልምምድ፣ ክትትልና ትኩረት ማድረግ አለብዎት፡፡ ስልቱን በቅደም ተከተል አንብበውና ተረድተው በተግባር ከተረጎሙት ስራ የማግኘቱ ዕድል ይሰፋልዎታል! በሦስት አመታት ጊዜ ውስጥ ከመቶ በላይ ማመልከቻዎች ልኬ ወደ በርካታ ቃለ ምልልሶች ተጠርቼ ነበር፡፡ በደንብ እየታሸሁኝና እየበሸቁኝ ስህተትም ሆነ ትምህርት ወስጃለሁ፡፡ ስለዚህ እርስዎ ስልቱን በተገቢው ካዎቁት ልክ እንደኔ ማንም ወገኛ ስራ ቀጥሪ በነገር አያሸዎትም!!! ጫማ ሳያደርጉ በምስማር ላይ መረማመድም የለብዎትም። አሁን ኮተት አታብዛብኝ፥ ይልቅስ ወደ ቁም ነገሩ እንግባ አይሉኝም አንዴ…? እሺ በቃ…

 

ቅድመ ዝግጅትና ሁኔታዎች፤

በስደት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን የፈለግነውንና የተመኘነውን የስራ አይነት በሙያችን ለማግኘት በርካታ መሰናክልቶች ያጋጥሙናል፡፡ በተለይ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለን በምንሆን ጊዜ ደህና የሆነ ስራ በሙያችን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ በዚህም ላይ ደግሞ ጸጉረ ልውጦች ስለሆንን ቀጣሪዎች ጥርጣሬ ይገባቸዋል፡፡ ቀጣሪዎች እኛን ስራ ለመስጠት ቢፈልጉም እንኳን ያገሬው ሰራተኞች አይፈልጉ ይሆናል በማለት ከመቀጠር የሚቆጠቡበትም ጊዜ አለ፡፡

 

አብዛኛው ስራ የሚገኘውም በዝምድና፣ በትውውቅና በጓደኝነት ነው፡፡ ከዛ የተረፈ የስራ ኣይነት ማስታወቂያ ላይ ይወጣል። ትውውቅና ጓደኝነትም ለመፍጠር አጋጣሚው መፈጠር አለበት፡፡ ይህንንም አጋጣሚ እራሳችን ከጊዜ ጋር ለመፍጠር ሊሳካም ላይሳካም ይችላል።

 

በተጨማሪም ስዴት ውስጥ ሆኖ ተስማሚ ስራ ለማግኘት ወጣገባ ከመሆኑም በላይ ውስብስብ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ግን ስራ ለማግኘት ተጨማሪ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ታዲያ ይህንን ወጣገባ የሆነ ጉዞ እንዴት እንወጣዋለን? ስራ የማግኘት እድላችንንስ እንዴት ማስፋት እንችላለን?

 

ያገሩን ባህልና ቋንቋ ከሞላ ጎደል መቻል፣ የህዝቡን ያኗኗርና የአቀራረብ ዘይቤንም በቅጡ ማወቅ ደህና ስራ ለማግኘት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ይህንን ማዎቅ ስራ ከማግኘትም ባሻገር በግል ህይወታችንና በሌሎች የማህበራዊ ጉዳዮች ላይም ጭምር በዕውቀት እንዲንዳብር ይረዳናል፡፡

 

በትውውቅ፣ በዝምድናና በጓደኝነት ተይዘው ያላለቁ ክፍት የስራ ቦታዎች ማስታዎቂያ ላይ ይዎጣሉ፡፡

ማስታወቂያውም ጋዜጣ፣ መጽሄት፣ ኢንተርኔት ወዘት ላይ ሊሆን ይችላል። በማስታወቂያውም ላይ ስለመስሪያ ቤቱ፣ ስለ ስራው አይነት፣ ምን አይነት የስራ ልምድ ያለው ሰራተኛ እንደሚያስፈልግ ባጭሩ መጥቀስ የተለመደ ነው፡፡ አመልካቾችም ከደወሉ ደግሞ ማንን ማናገር እንደሚቻል ከስልክ ቁጥር ጋር ይገለጻል፡፡

 

ይህንን አጭር የስራ ማስታወቂያ በጥንቃቄ ረጋ ብሎ ማንበብና መረዳት በጣም ይጠቅማል፡፡ ማስታወቂያውንም አንብበው ወዲያውኑ ማመልከቻ ከጻፉ ስራ የማግኘትዎ እድል በጣም የመነመነ ነው። ከዛ በፊት ግን በቅድሚያ ማድረግ ያለብዎትን ነገሮች በዝርዝር እናያለን፡፡ ምክንያቱም ማስታወቂያው ላይ በሰፈረው መረጃ ብቻ ማመልከቻ ከተላከ ስራውን ማግኘት ቀርቶ ለቃለ ምልልስ እንኳን ለመጠራት እድሉ ጠባብ ነው፡፡

 

አንድ የስራ ማስታወቂያ በወጣ ጊዜ በአስሮች የሚቆጠሩ ሰወች እንደሚያመለክቱ የተለመደ ነው፡፡ አመልካቾች በበረከቱ ቁጥር ውድድሩም ይጠነክራል፡፡ ታዲያ ማስታወቂያውን አንብበው በጥሞና ከተረዱ በኋላ ወደ መስሪያ ቤቱ ደውለው የሚመለከተውን ግለሰብ ቢያናግሩ ይጠቅማል፡፡ ከመደወልዎ በፊት ዝግጅ ማድረግ አለብዎት፡፡ ሲደውሉም ስልኩ በጸሃፊ ከተነሳ ማን እንደሆኑ፣ ለምን እንደሚደውሉና ከማን ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ባጭሩ ቀንጨብ አድርገው ይጠይቁ፡፡

 

ማስታወሻ!

አንዳን ስራ ቀጣሪዎች እጩ ሰራተኛ ለማግኘት ደላላ ወይም "አዕምሮ አዳኞች" የሚባሉ ጋር ግንኙነት አላቸው። የዚህ አይነት ነገር ከተከሰተ እዛው ማስታወቂያው ላይ ያገኙታል። ስለዚህ እርስዎ በቀጥታ ወደ ቀጣሪውም ሆነ ደላላው ዘንድ ከደወሉ የት እንደሚደውሉና ከማን ጋር እንደሚነጋገሩ ቢለያይም የስልቱ መሰረቱ ግን አንድ ነው።

 

ማነጋገር ከሚፈልጉት ግለሰብ ጋርም በተገናኙ ጊዜ፤ “ እንደምን ዋሉ! ስሜ እከሌ ይባላል፡፡ የምደውለው ከዚህ ቦታ ነው፡፡ የመጣሁት ከዚህ አገር ነው (እንደ ሁኔታው ቢለያይም ይህንን ቢሉ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።) ያወጡትን የስራ ማስታዎቂያ አይቸዋለሁ፡፡ ስራው ይህንንና ይህንን ስለሚመስል እኔም የዚህ አይነት ልምድ ወይም ፍላጎት ስላለኝ ይስማማኛል፡፡ ማመልከቻም ለመላክ አስቤአለሁ፤ ” ካሉ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቁ፡፡ ይህ የስልክ ንግግር በሚካሄድበት ጊዜ ረጋና ቀስ ብለው ባጭሩና በግልጽ ቋንቋ ቢናገሩ ሰሚው በቀላሉ ይረዳዎታል፡፡ በመካከል ሰሚው በሚናገር ጊዜ እንዳያቋርጡት ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ የዚህ ንግግር አላማ ማመልከቻ ከመላክዎ በፊት እርስዎን ባጭሩ ለማስተዋወቅ ነው እንጂ ብዙ ወሬና ኮተት አያብዙ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ባጭሩ ጥሩ ትዝታ ጥለውና አመስግነው ንግግሩን ለመጨረስ ይጣሩ፡፡

 

አሁን ደግሞ ስለ ማመልከቻ አጻጻፍ፣ ሂደቱና ክትትሉን አብረን እናያለን፡፡

 

የስራ ማመልከቻ የአመልካቹን ማንነት የሚገልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ማመልካቻው ሲጻፍ ተገቢ ጥንቃቄና ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

ኮተትም ሳይበዛበት አጠር ብሎ ግልፅና ለመረዳትም ቀላል መሆን አለበት፡፡ ቀጣሪዎችም ብዙ ማመልከቻዎች ስለሚደርሷቸው እጥር ምጥን ያሉ ማመልከቻዎችን ይመርጣሉ፡፡ እንግዲህ ማመልከቻ ሲፅፉ ቀን፣ የእርስዎ ሙሉ ስምና አድራሻ ይቀድማል፡፡ ከዚያም የስራው አይነት ከነ አርእስቱ ጎላ ብሎ በአርእስት መልክ ገባ ብሎ ይሰፍራል፡፡ ወደ ዝርዝር ከመግባትዎ በፊት ስራውን በተመለከተ መቼና ከማን ጋር በስልክ ጥሩ ውይይት እንደነበረዎት ቢጠቅሱ ይታዎሳሉ፡፡ ከዚያም ይህንን ስራ ለምንና እንዴት እንደፈለጉት ባጭሩና በዝርዝር ያቀርባሉ፡፡ የትምህርት ጊዜ፣ የስራ ልምድ፣ በትርፍ ጊዜ የሚደረጉ የተለያዩ ዝንባሌዎች፣ ወዘተ እራሱን በቻለ ገጽ ላይ እጥር ምጥን አድርጎ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡

 

በተጨማሪም አመልካቹ ባሁኑ ጊዜ ምን እንደሚያደርግና ህይወቱም ምን እንደሚመስል ቀንጨብ አድርጎ ቢያቀርብ ማመልከቻውን ሁለገብ ያደርገዋል፡፡ አመልካቹ በራሱ አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን የራሱን ሁኔታዎችና ልዮ ችሎታዎች ቢጠቅስ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ በመጨረሻም እርስዎን የሚያዉቁዎትንና የጠየቋቸውን የሁለት ወይም ሶስት ተጠሪ ግለሰቦች ስም ከነሙያቸው ያሰፍራሉ፡፡ ተጠሪዎቹም ድንገት ተደውሎላቸው እንዳይደናገሩ ጉዳዩን በቅድሚያ ይንገሯቸው፤ ያስታውሷቸውም፡፡

 

ማመልከቻውም ከተላከ ከሶስት እስከ አምስት ቀናት በኋላ ከዚህ በፊት ያነጋገሩት ሰው ዘንድ መደወል ጥሩ ነው፡፡ ስልኩንም እራሱ ሰውዬው ካነሳው/ችው በስም “ ሰላም እከሌ” ብሎ ንግግር መጀመር ነው፡፡ ለምሳሌ “በዚህ ቀን ላይ ስለዚህ ስራ ተነጋግረን ነበር፡፡ ማመልከቻ ልኬአለሁ፡፡ ስለ ማመልከቻው ምን ይመስልዎታል? ሌላ ተጨማሪ ነገር የምትፈልጉት ካለ እልካለሁ፡፡” ብሎ መጠየቅ ይጠቅማል፡፡ ማመልከቻው እስከዛሬ ድረስ ያልተነበበ ከሆነ አርስዎ ስለደወሉ ማመልከቻው ከተቀመጠበት ተነስቶ ወይም ተመዞ አሁን ሊነበብ ይችላል።

 

ዋናው ቁም ነገር ግን አርስዎ አሁን እራስዎን እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ አስተዋወቁ፡፡ የራስዎንም ማመልከቻ በቅጡ ተከታተሉ፡፡ ከዚህ በፊት ያነጋገሩትንም ሰው በስም አስታወሱ፡፡ ይህንንም ስራ ለማግኘት ፍላጎትዎን እንደገና አሳዩ፡፡ ማመልካቻውም ከንብብሩ ላይ ተነስቶ ወይም ተመዞ ታየለዎት፡፡ ቀጣሪውም አርስዎን በቀላሉ ያስታውሰዎታል፡፡

ንግግሩም በሚካሄድበት ጊዜ እርስዎ እንደ ስራ ለማኝ ወይም ተስፋ ቢስ አይነት ሆነው መቅረብ የለብዎትም፡፡ ባነጋገር ሁኔታና በድምፅ ቃና በራስዎ የሚተማመኑ መሆንዎን ማሳወቅ መቻል አለብዎት፡፡ ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ላልተጠበቁ ጥያቄዎችና መልሶች በስልክም ቢሆን ቅሉ ዝግጁ መሆንና በተቻለ መጠን ምክንያታዊ ጥያቄ ማቅረብና መልስም መስጠት ከቀጣሪው ዘንድ ነጥብ ያሰጣል፡፡ መጨረሻም ላይም አመስግኖ ለቃለ ምልልስ እንድምጠራ ተስፋ አደርጋለሁ ሳይሆን ለቃለ ምልልስ እንደምጠራ እጠብቃለሁ ብለው በጨዋነት የስልኩን ንግግር መደምደም ነው፡፡ ዘንድሮ እኮ በጣም ፈጣጣና አይን አውጣ ሆንኩኝ ብለው አይስጉ።

 

ዋናው ነገር ወሬ ሳያበዙ ባጭሩ መጠየቅ፣ መልስ መስጠትና በጊዜው ውይይትዎን መጨረስ ነው።

 

በሚቀጥሉት ቀናት ወይም ሳምንታት ውስጥ ለቃለ ምልልስ ካልተጠሩ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሌላ ስራ ለማግኘት አደናውን መቀጠል ነው፡፡ ለቃለ ምልልስ ከተጠሩ ደግሞ እሰየው ነው፡፡ አንድ እርምጃ ወደፊት፡፡ አሁን ደግሞ ይህንን ስራ ለማግኘት ምን መደረግ እንዳለበት በዝርዝር እናያለን፡፡

 

ለማስታወስ ያህል የመጀመሪያው የስራ አፈላለግ ስልት ላይ በዝርዝር የሚከተሉትን ነጥቦች አይተናል፤

 

ለስራ ፍለጋ ቅድሚያ ዝግጅት፣

ክፍት የስራ ቦታዎች ምን ላይና እንዴት እንደሚዎጡ፣

ማመልካቻ ከመጻፉ በፊት ስለሚደርጉ ቅድመ ዝግጂቶችና፣

የማመልከቻ አጻጻፍና ክትትሉን አይተናል፡፡

አሁን ደግሞ ለቃለ ምልልስ ከተጠሩ ምን አይነት ዝግጅትና ትኩረት ማድረግ አንዳለብዎት በዝርዝር አብረን እናያለን።

ለቃለ ምልልስ መጠራት ማለት ስራውን ለማግኘት እጩ መሆን ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ሌሎች ተቀናቃኝ አመልካቾች እንደርስዎ ለቃለ ምልልስ ስለሚጠሩ ውድድሩ ተፋፋመ እንጂ አላለቀለዎትም፡፡ የሚዎዱትንና የፈለጉትን ስራ ማግኘት ያስደስታል፡፡ ያረካልም፡፡ የፈጠራ ችሎታዎንም ከተጠቀሙበት እድገትዎ ይጨምራል። ደመወዝም የቤተሰብ ማስተዳደሪያና የተለያዩ ወጭወችን መሸፈኛ ስለሆነ ለማንም ቢሆን ስራ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ስራ ለማግኘት እራስዎን አስማምተውና አቀራረብዎን አሳምረው ለቀጣሪው ክፍል መሸጥ አለብዎት፡፡ ቀጣሪውም ክፍል እስካሁን ድረስ በድምጽና በማመልከቻዎ ብቻ ያውቅዎታል፡፡ አሁን ግን በአካል ተገኝተው ፊት ለፊት እንዲዎያዩ ተጋብዘዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ የሆነ ዝግጅት ማድረግም አለብዎት፡፡ ለዕድልም ቦታ መስጠት የለብዎትም፡፡

 

መቼም ለቃለ ምልልስ ሲጠሩ፤ እንዳው ቀጣሪዎች ሲያዩኝ ይወዱኝ ይሆን? ምን ይጠይቁኝ ይሆን? ምን አይነት መልስ እሰጥ ይሆን? ምን ልልበስ? ወዘተ እያሉ ማወራረድዎ አይቀርም፡፡ እንዴት እንደሚዘጋጁ የማውቀውን በደንብ እነግረዎታለሁ፡፡ ምን አይነት መልስ እንደሚመልሱ ግን ምን አይነት ጥያቄዎች እንደሚጠየቁ ስለማላውቅ ሊጠየቁ የሚችሉትን ጥያቄዎች ብቻ አብረን እናያለን፡፡ መልሶቹም ምናልባት ለርስዎ ባይሆኑም መንደርደሪያ መልሶች ይሆኑልዎታል፡፡ በጣም ብዙ ነገሮች ግምትና ቁጥር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ለምሳሌ አቀራረብዎ አንሶ ትምህርትና የስራ ልምድ ብቻቸውን ግቡን አይመቱም፡፡ አቀራረብ ለስራ ማግኘትም ሆነ ለማህበራዊ ኑሯችን ጭምር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አቀራረብ ወሳኝ ከመሆኑ የተነሳም ስራ ለማግኘት ከመቶ ግማሹን ያህል ሊቆጠር ይችላል፡፡ ልብ ይበሉ! በሚቀጥለው ደግሞ "ጥያቄና መልሶች ለምልልስ" የሚለውን እናያለን።

 

ልብስና አቀራረብን ከማየታችን በፊት አንዳንድ ሊጠየቁ የሚችሉ ጥያቄዎችን በዝርዝር እናያለን፡፡ ብዙ አይነት ጭያቄዎች አሉ፡፡ እንደ ስራው አይነትና ፀባይ ቢለያዩም ተደጋግመው የሚጠየቁ ጥያቄዎች እንደሚከተሉት ናቸው፤

 

1. ስለኛ መስሪያ ቤት ምን ያውቃሉ?

2. ከሌሎች ነጥለን እርስዎን ብቻ ለምን እንቀጥረዎታለን?

3. ለመስሪያ ቤታችን ምን አይነት አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ?

4. ከአምስት አመታት በኋላ እራስዎን እንዴት ያዩታል?

5. ደካማ ጎንዎ ምንድነው?

6. ጠንካራ ጎንዎ ምንድነው?

7. አሁን ምን እየሰሩ ነው?

8. ደመወዝዎ ስንት እንዲሆን ይፈልጋሉ? ወዘተ ናቸው፡፡

 

ስለ መስሪያ ቤቱ ለማወቅ ለቃለ ምልልስ በተጠሩ ጊዜ አንዳንድ ቁልፍ መረጃዎችን ቢያሰባስቡ በጣም ይጠቅምዎታል፡፡

ከነዚህም መረጃዎች አንዳንዶቹ፤ መስሪያ ቤቱ ከተመሰረተ ስንት ጊዜ እንደሆነው፣ ምን አይነት አገልግሎትና ምርት እንደሚያቀርብ፣ ደንበኞቹ እነማን እንዴሆኑ፣ ስንት ሰራተኞች እንዳሉት ወዘተ ናቸው፡፡ የምንኖርበት ዘመን የመረጃ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ስለመስሪያ ቤቱ በመጠኑ ለማወቅ የተለያዩ ምንጮችን መገልገል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ መስሪያ ቤቱ የራሱ የኢንተርኔት ገጽ ሊኖረው ስለሚችል ብዙ ነገር እዛ ያገኛሉ፡፡ ካልሆነም ሌሎች የጽሁፍ መረጃዎችን መሻት ይቻላል፡፡ ሰውም መጠየቅ ይቻላል፡፡

 

መስሪያ ቤቱ እርስዎን መርጦ እንዲቀጥርዎት ደግሞ ጉረኛ ሳይመስሉ ታታሪ ሰራተኛ መሆንዎን ለማሳመን ይጣሩ፡፡ ለምሳሌ ስራው ከትምህርትዎ፣ ከፍላጎትዎና ከልምድዎ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሊጠቅሱ ይችላሉ፡፡ ወደፊትም ለማደግና ለመዳበር ስለሚፈልጉ ስራው ለርስዎ ጥሩ በር ከፋች ሊሆንልዎት እንደሚችልም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ለስራው እርስዎ ተስማሚ እጩ መሆንዎን ማስመር ይችላሉ፡፡

 

ለመስሪያ ቤቱ ሊያበረክቱ የሚችሉት ነገር ቢኖር ደግሞ ከአዲስ ነገር ጋር እራስዎን ፈጠን ብለው ስለሚያለማምዱት ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተጨባጭ የሆነ ውጤትም ለማስገኘት ታታሪ ሆነው እንድሚሰሩ ማሳወቅም ይገባል፡፡ በመስሪያ ቤቱ ላይ ለውጥ አመጣለሁ እንዳይሉ ግን ይጠንቀቁ፡፡ በኋላ እንደሁኔታው ይደርሱበታል፡፡ ያኔም ቢሆን በተግባር እንጂ ለውጥ አመጣለሁ እያሉ አይደለም።

 

ከአምስት አመታት በኋላ ምን እንደሚመስሉ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኛ ስራ ቀጣሪዎች ግን ሊፈታተኑዎት ይፈልጋሉ። ቢሆንም ግን የተለያዩ አላማዎች ሊኖርዎት ይገባል፡፡ ለምሳሌ ስለቤተሰብ፣ ስለስራ፣ የተለያዩ ነገሮችን ስለማድረግ እና ስለ ስኬታቸው ወዘተ፡፡ ህይዎት እራሷ ትምህርት ቤት እንደመሆኗ መጠን በሚቀጥሉት አመታት ውስጥ በተለያዩ ነገሮች ላይ የበለጠ በእውቀት እንደሚዳብሩ መግለፁም አይከፋም፡፡

 

ብዙዎቻችን ከደካማ ጎን ይልቅ ጠንካራ ጎናችንን መናገር ይቀለናል፡፡ ጠንካራ ጎንዎን ሲናገሩ ጉራ እንዳይመስልብዎት ጓዴኞቼ እንዲህና እንዲህ ይሉኛል ማለቱ ይሻላል፡፡ ለምሳሌ ማዳመጥን፣ ፍላጎትዎን፣ የትርፍ ጊዜ እንቅስቃሴዎን፣ አቀራረብዎን፣ የተለያዩ አስተያየትዎን ወዘተ በተመለከተ ሊሆን ይችላል፡፡

 

ደካማ ጎንን ለመናገር ሲሆን ግን ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ግን ሰው ፍፁም አይደለምና ደካማ ጎንም ሊኖርዎት ይገባል፡፡ ይህንን ሲናገሩ ግን ድፍን ያለ ደካማ ጎንዎን መናገር የለብዎትም፡፡ ለምሳሌ ወደ ትልቅ ከተማ ስሄድ ፎቆችን መቁጠር ስለለመደብኝ መንገደኞች ጋር መጋጨት ያጠቃኛል ማለት ጭልጥ ያለ ሁለት አይነት ሞኝነት ነው፡፡ በምትኩ ግን “ ጓደኞቼ ግትር አይነት ነህ፤ ምክንያቱም አንድ ጊዜ የተባለውና የታቀደው ነገር ሳያልቅ በቂ እረፍት አታደርግም " ይሉኛል ማለቱ ይሻላል፡፡ ግትር አይነት ቢሆኑም በዕቅድ መመራትዎን ያሳውቅልዎታል፡፡ እራስዎን የሚያረክስ ነገር ቢጠየቁም ስራ ለማግኘት እስከመጡ ድረስ እራስዎን ሙሉ በሙሉ ማርከስ የለብዎትም፡፡ በአርካሹ መልስዎ ይዘት ውስጥ ለስራ ሰጪው ክፍል የሚጥቅም ነገር ማዘል አለበት፡፡ በምሳሌው እንደተረዱኝ ተስፋ አለኝ፡፡

 

ብዙውን ጊዜ ቀጣሪወች አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ከተጠየቁ አሁን የሚያደርጉትንና የሚሰሩትን ባጭሩና በዝርዝር ማስረዳት አለብዎት፡፡ ስራ እሚቀይሩም ከሆን አሁን ያሉበት የስራ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ገና ከት/ቤት የወጡ ከሆነም ስለመጨረሻው ትልቁ ፕሮጀክትዎ ዙሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ስራ ብቻ የሚፈልጉም ከሆነ የከተማ አውደልዳይ እንዳይመስሏቸው በትርፍ ጊዜዎ የተለያዩ ነገሮችን እንደሚያደርጉ መጥቀሱ አይከፋም፡፡ ዋናው ነገር ግን አሁን እርስዎ ለራስዎም ሆነ ላካባቢዎ የሚጠቅምና ፍሬማ ነገር የሚያደርጉ መሆንዎን የቀጣሪወቹ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡

 

ደመወዝስ? ጥያቄው አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ስለመስሪያ ቤቱ አጥንተው ከሆነ የደመወዙን መጠንና አካባቢ ያውቁታል፡፡ ከት/ቤት በቅርቡ የጨረሱ ከሆነ፣ የስራ ልምድ ካለዎት፣ የመስሪያ ቤቱ አይነት፣ የሰራው አይነትና ሃላፊነት የደመወዙን መጠን ይወስነዋል፡፡ ቁጥር ከመጥራትዎ በፊት ግን “ለኔ ለእድገት በር ከፋችና የምወደውን ስራ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ስራ ለማግኘት ያመለከትኩት ለዚሁ ነው “ ብለው ቢጀምሩ ነገሮች ይለሰልሳሉ፡፡ ቁጥርም መጥራት ካስፈለገ ምክንያታዊ ሆኖ ጥሩ ደመዎዝ መጠየቅ ይገባል፡፡ እርካሽ ደመወዝ መጥራት አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የስራ ለማኝ ያስመስላል፡፡ በሚቀጥለው ክፍል ላይ ስለ አቀራረብና ልብስ የመሳሰሉትን እናያለን።

 

ለቃለ ምልልስ ሲጠሩ ምን ልልበስ? ምን ልጫመት? ምን ልኳኳል? እያሉ ማሰብ አይቀርም፡፡ ልብስ የእርቃን መሸፈኛ ብቻ ነው ብሎ ችላ ማለትም አያስፈልግም፡፡

እንዳገሩ ሁኔታ ቢሆንም ገላን ታጥቦ ንፁህና ለሰውነትዎ የሚስማማ ልብስ ከለበሱና ከተጫመቱ በቂ ነው፡፡ ከረባት የግድ ማድረግ የለብዎትም፡፡ ለጋብቻ እንደተጠራ አሸብርቆ ወይም አጊጦ መሄድም አያስፈልግም፡፡ የቀለሙ ቅንብርና ለሰውነት የሚስማማ ልብስ መምረጥና መጠቀም እራሱ ችሎታ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ስንቱ በየመንገዱ ተንጀርፎ የምናየው፡፡

 

 

 

 

ስለዚህ ለእርስዎ የሚስማማዎትን የልብስና የጫማ አይነት መምረጥ ይኖርብዎታል፡፡ ጥፍር መከርከምና ፀጉር መበጠር አለበት፡፡ ከሩቅ የሚጣራ ሽቶ ያስገምታል፡፡ የከንፈር ቀለምና ኩላኩል ነገርም ማብዛት አያስፈልግም፡፡ ደረትም ባይጋለጥ ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ወንዶች አንገት የሚደርስ ሙሉና ክብ ሹራብ ለብሰው ኮት ቢደርቡበት ያምርባቸዋል፡፡ ሴቶች አመልካቾች ደግሞ ከልብሳቸው ቀለም ጋር የሚስማማ ሻሽ ነገር አንገታቸው ላይ ሸብ አድረገው በደረታቸው ላይ ጠልጠል ቢል የሚያምርባቸው ይመስለኛል፡፡ ያየሩ ንብረት ከፈቀደም ሴቶች ቀሚስ ቢለብሱ ይመረጣል፡፡

 

አቀራረብ ፊት ለፊት

የተለያዩ አቀራረቦች ቢኖሩም ማንም ቢሆን የሚመርጠው ቀና የሆነ አቀራረብን ነው። ታዝበው ከሆነ መጥፎ ነገር ቀርቶ ደህና ነገር ላይ እንኳን ሲያስቡ፣ ሲናገሩና ሲመለከቱ ሳያውቁት በተለምዶ ፊታቸው የሚኮሰተር ሰዎች በርካታ ናቸው። በጊዜው ለኛ ባይታየንም ተመልካቹ ግን ያውቀዋል፡፡

 

የመጀመሪያ ግምገማ ወሳኝ እስከሆነ ድረስ ስራ ፍለጋ ሄደው ፊትዎን አኮሳትረው እራስዎን እንዳይቀጡ፡፡ አደራ፡፡ ሲናገሩና ሲያስቡ ፊትዎ ምን እንደሚመስል በመስታወት ወይም በጓዴኛዎ በቅድሚያ መለማመድ ይችላሉ፡፡

ለቃለ ምልልስ የሚሄዱበትን ቦታ ቀደም ብለው አድራሻውን ካዎቁ ከሃሳብና ጭንቀት ይድናሉ፡፡ በቀጠሮውም ሳይዘገዩ አምስት ደቂቃ አካባቢ ሲቀረው በስፍራው መገኘት ይጠቅመዎታል፡፡ እጅዎንም ካላበዎት በመሃረም ነገር ያድርቁት፡፡ ቀጣሪው ክፍልም በሚቀበልዎት ጊዜ አንገትዎን ቀና፣ ፊትዎንና ትካሻዎን ዘና አድርገው ፊት ለፊት እያዩ ሞቅና ጠበቅ ያለ ሰላምታ ይስጡ፡፡ ከዚህ በፊት በስልክ ያነጋገሩት ግለሰብ መጥቶ ከተቀበለዎትና በስሙ እርግጠኛ ከሆኑ፤ “ከርስዎ ጋር ከዚህ በፊት ስለስራው ተነጋግረናል” ብለው መጥቀስ ይችላሉ፡፡

 

ወደ ውይይት ክፍሉ ሲወሰዱ መተላለፊያው፣ ጓዳውና ኮተቱ የበዛበት ከሆነ፤ በኋላ ሲወጡ መውጫው እንዳይጠፋዎት ያስታውሱ፡፡ በኋላ እንዳይታዘቡዎት፡፡ እኔ ኣንድ ጊዜ ተሸውጃለሁ።

 

ክፍሉም ውስጥ እንደገቡ ሌሎች ሁለት አካባቢ የሚሆኑ በነገር የሚያፋጥጡዎት ግለሰቦች መኖራቸው ስለማይቀር ለነሱም ሞቅ ያለ ሰላምታ ያቅርቡ፡፡ ስማቸውንም ለማስተዎስ ይሞክሩ፡፡ ክፍሉም ጥሩ ከሆነ ወይም ጠረንጴዛው በቅጡ የተዘጋጀ ከሆነ ወይም ግድግዳው ላይ ጥሩ ስዕል ካዩ ጥሩ መሆኑን ቢገልጹ ጥሩ ታዛቢ መሆንዎን ያሳያል፡፡ ካላማረዎት ግን ማስመሰል ስለሚሆን አፍዎን አያበላሹ፡፡ ሲቀመጡም ሌሎቹን መጀመሪያ ቢያስቀድሙ ጥሩ ነው፡፡

 

ከተቀመጡ በኋላም ተዝናንተው በስርአት ይቀመጡ እንጂ ዝልፍልፍ አይበሉ፡፡ የፈሩም አይምሰሉ፡፡ እግርዎን ሳያነባብሩ ቁጭ ብለው እጆችዎ ጭነዎ ላይ አርፈው አገጭዎ ፎቶ እነደሚነሳ ሰው ቀና ብሎ፤ ትካሻዎና ወገብዎ ሲዝናና ከተሰማዎት ግሩም አቀማመጥ ይመስለኛል፡፡ ፊትዎም ዘና ማለቱን ሁልጊዜ ያስታውሱ። ይህ አቀማመጥ እንደተጠበቀ ሆኖ እጅዎንም ሆነ ሰውነትዎን በተገቢው ለማንቀሳቀስ ምቹ ነው፡፡ በሚናገሩ ጊዜ የጠየቀዎትን ግለሰብ በ ቀጥታ እያዩ ቢሆንም ሌሎቹንም ለአፍታ ገረፍ ማድረግ አለብዎት፡፡ ሌሎች በሚናገሩ ጊዜ እንዳያቋርጧቸው ጠንቀቅ ይበሉ፡፡ አቀርቅረው አያውሩ፡፡ የሚናገሩት ቋንቋም አንድ ሆኖ ግልፅና ሙሉ መሆን አለበት፡፡ አፉን እንደሚፈታ ህጻን ልጅም መንተባተብ አይገባም፡፡ ቀጣሪዎቹ “ምን አሉ?” እንዲሉዎት እድል አይስጡ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር እጅዎን አያወናጭፉ፡፡ ነገርን ባጭሩ ይመልሱ እንጂ ያለአስፈላጊ ብዙ ትንተና ውስጥ ገብተው ነገር አይበላሽብዎት፡፡ የማያውቁት ነገር ከተጠየቁ “ይህንን አላውቅም” ማለት ይሻላል፡፡ ሲያዳምጡም ሆነ ሲናገሩ የፊትዎ ገጽታ የዘናና የተዝናና መሆኑን በውስጥዎ ያስታውሱ፡፡ አቀራረብ!!

 

ቃለ ምልልሱም እንዳለቀ ሲያሰናብቱዎት ካመሰገኑ በኋላ ውልቅ ብሎ መውጣት ነው፡፡ ውጤት በቀናት ወይም በሳምንታት ጊዜ ውስጥ መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ይቅናዎት!!

 ምንጭ፡-.ethionorway