የመጀመሪያውን ዓመት የትዳር ሕይወት ስኬታማ ማድረግ

የመጀመሪያውን ዓመት የትዳር ሕይወት ስኬታማ ማድረግ

 

 አንዲት ሚስት ባሏ ባደረገው ነገር ተናዳ

 

ባል፦ “ሚስቴና እኔ ይህን ያህል የተለያየን ሰዎች መሆናችንን ሳውቅ ተገረምኩ! ለምሳሌ ያህል፣ እኔ በጧት መነሳት እወዳለሁ፤ እሷ ደግሞ ማምሸት ትወዳለች። ስሜቷ ሲለዋወጥ ደግሞ ግራ ይገባኛል! ሌላው ነገር ደግሞ እኔ ምግብ ሳበስል፣ በተለይም እጄን በዕቃ ማድረቂያው ጨርቅ ሳደርቅ ስታየኝ በጣም ትተቸኛለች።”

 

ሚስት፦ “ባሌ ብዙ መናገር አይወድም። እኔ ደግሞ ከቤተሰቦቼ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ብዙ የማውራት ልማድ ነበረኝ። ቤተሰቦቼ፣ በተለይ በምግብ ሰዓት ብዙ ይጫወታሉ። ባለቤቴ ምግብ ሲያበስል በዕቃ ማድረቂያው ጨርቅ እጁን ያጸዳል! ይህ ደግሞ ያናድደኛል! ወንዶች የሚያስቡበት መንገድ አይገባኝም! በዚህ ዓይነት፣ ሰዎች ትዳራቸውን ስኬታማ የሚያደርጉት እንዴት ነው?”

 

እናንተም አዲስ ተጋቢዎች ከሆናችሁ ይህን የመሰለ ችግር ገጥሟችኋል? የትዳር ጓደኛችሁ ለጋብቻ በምትጠናኑበት ጊዜ ያልነበሩት ዓይነት እንከኖችና ድክመቶች አሁን ብቅ ብቅ እያሉ እንዳለ ሆኖ ይሰማችኋል? ታዲያ ‘የሚያገቡ ሰዎችን የሚያጋጥሟቸው ብዙ የኑሮ ችግሮች’ የሚያስከትሉትን ጫና መቀነስ የምትችሉት እንዴት ነው?—

 

በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንተና የትዳር ጓደኛህ የጋብቻ ቃል ኪዳን ስለተጋባችሁ ብቻ ስለ ትዳር ሕይወት ሁሉን ታውቃላችሁ ማለት አይደለም። ነጠላ በነበራችሁበት ጊዜ ያዳበራችኋቸው ጠቃሚ የሆኑ ማኅበራዊ ክህሎቶች ይኖሯችሁ ይሆናል፤ በተጨማሪም ለጋብቻ በምትጠናኑበት ወቅት እነዚህ ክህሎቶች ይበልጥ ተሻሽለው ይሆናል። ይሁን እንጂ ትዳር እነዚህን ክህሎቶች በአዲስ መንገድ ይፈትናቸዋል፤ እንዲሁም አዳዲስ ክህሎቶችን ማዳበር ሊጠይቅባችሁ ይችላል። ስህተት ትሠሩ ይሆን? ስህተት እንደምትሠሩ ጥርጥር የለውም። ታዲያ የሚያስፈልጓችሁን ክህሎቶች ልታዳብሩ ትችላላችሁ? እንዴታ!

 

ማንኛውንም ክህሎት ለማሻሻል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጉዳዩን ጠንቅቆ የሚያውቅን አካል ማማከርና የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። በትዳር ጉዳይ ደግሞ ከሁሉ የላቀ እውቀት ያለው ይሖዋ አምላክ ነው። ደግሞም የማግባት ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ የፈጠረን እሱ ነው። ቃሉ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትቋቋሙ ብሎም የመጀመሪያውን ዓመት የትዳር ሕይወታችሁን ስኬታማ በሆነ መንገድ አልፋችሁ ዘላቂ የሆነ ጥምረት እንድትመሠርቱ የሚያስችሏችሁን ክህሎቶች እንድታዳብሩ የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ።

 

አንደኛው ክህሎት፦ የመመካከር ልማድ አዳብሩ

ተፈታታኝ ሁኔታዎቹ ምንድን ናቸው?

በጃፓን የሚኖር ኬይጂ * የሚባል አንድ ባል የሚያደርገው ውሳኔ የትዳር ጓደኛውን  እንደሚነካት የሚዘነጋባቸው ጊዜያት ነበሩ። “ሚስቴን ሳላማክር የሚቀርቡልንን ግብዣዎች እቀበል ነበር” በማለት ይናገራል። “ባለቤቴ በግብዣዎቹ ላይ ለመገኘት እንደማትችል የምገነዘበው ተስማምቼ ከመጣሁ በኋላ ነበር።” በአውስትራሊያ የሚኖር አለን የሚባል አንድ ባል “ወንድ እንደመሆኔ መጠን ስለማደርጋቸው ነገሮች ሚስቴን ማማከር ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር” ብሏል። በአስተዳደጉ ምክንያት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። በብሪታንያ የምትኖረው ዳያንም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟታል። እንዲህ ትላለች፦ “ቤተሰቦቼን ምክር የመጠየቅ ልማድ ነበረኝ። ስለዚህ እንደተጋባን አካባቢ ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ ባሌን ትቼ ቤተሰቦቼን አማክር ነበር።”

 

መፍትሔው ምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ የተጋቡ ሰዎችን እንደ “አንድ ሥጋ” አድርጎ እንደሚመለከታቸው አስታውሱ። (ማቴዎስ 19:3-6) በይሖዋ ዓይን ሲታይ በባልና ሚስት መካከል ካለው ዝምድና የሚበልጥ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ዝምድና የለም! ይህ ዝምድና ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

 

ባልና ሚስት፣ ይሖዋ አምላክ ከአብርሃም ጋር የሐሳብ ልውውጥ ያደረገበትን መንገድ በመመርመር መማር የሚችሉት ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ላይ የተመዘገበውን ታሪክ እስቲ አንብቡ። አምላክ ለአብርሃም አክብሮት እንዳለው ያሳየባቸውን የሚከተሉትን ሦስት መንገዶች ልብ በሉ። (1) ይሖዋ ለማድረግ ያሰበውን ነገር ለአብርሃም ገልጾለታል። (2) አብርሃም ሐሳቡን ሲገልጽ ይሖዋ አዳምጦታል። (3) ይሖዋ ሊወስደው ካሰበው እርምጃ ጋር በተያያዘ አብርሃም ያቀረበውን ጥያቄ በተቻለ መጠን ለማስተናገድ ጥረት አድርጓል። ታዲያ እናንተ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስትማከሩ ይህንኑ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

 

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁን የሚነኩ ጉዳዮችን ስትወያዩ (1) ከተነሳው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለማድረግ ያሰባችሁትን ነገር ግለጹ፤ ይሁን እንጂ ይህን ስታደርጉ እንደ መጨረሻ ውሳኔ ወይም እንደ ግዴታ ሳይሆን እንደ አንድ አማራጭ አድርጋችሁ አቅርቡ። (2) የትዳር ጓደኛችሁ ሐሳቡን እንዲገልጽ ጠይቁ፣ ደግሞም የትዳር ጓደኛችሁ ከእናንተ የተለየ አመለካከት የመያዝ መብት እንዳለው ተረዱ። (3) በተቻለ መጠን የትዳር ጓደኛችሁን ምርጫ በማስተናገድ “ምክንያታዊ” እንደሆናችሁ አሳዩ።

 

ሁለተኛው ክህሎት፦ ዘዴኛ መሆንን ተማሩ

ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው?

ያደጋችሁበት ቤተሰብ ወይም ባሕል ካሳደረባችሁ ተጽዕኖ የተነሳ ምንም ዘዴ ሳትጠቀሙ ሐሳባችሁን ኃይለኝነት በሚንጸባረቅበት መንገድ የመግለጽ ልማድ ይኖራችሁ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በአውሮፓ የሚኖረው ሊያም እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ባደግሁበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሰዎች ዘዴኝነት ይጎድላቸዋል። ሐሳቤን በምገልጽበት ወቅት እንዳመጣልኝ የምናገር መሆኑ ብዙውን ጊዜ ሚስቴን ያስቆጣታል። በመሆኑም ለስለስ ባለ መንገድ የመናገር ልማድ ማዳበር አስፈልጎኛል።”

 

መፍትሔው ምንድን ነው?

የትዳር ጓደኛችሁ እናንተ በለመዳችሁት መንገድ እንድታናግሩት እንደሚፈልግ  አድርጋችሁ አታስቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንድ ሚስዮናዊ የሰጠው ምክር አዲስ ለተጋቡ ሰዎችም ጠቃሚ ነው። “የጌታ ባሪያ ግን ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር . . . ሊሆን ይገባዋል” በማለት ጽፎ ነበር። “ገር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዘዴኛ” ተብሎም ሊፈታ ይችላል። ባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ዘዴኝነት፣ ስሜት ሊጎዳ የሚችልን ሁኔታ አስተውሎ ጉዳዩን ሌሎችን በማያስቀይም መንገድና በደግነት የመያዝ ችሎታ ነው።

 

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በትዳር ጓደኛችሁ ተበሳጭታችሁ ስለ ጉዳዩ በምትነጋገሩበት ጊዜ፣ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሳይሆን ከጥሩ ጓደኛችሁ ወይም ከአሠሪያችሁ ጋር እየተነጋገራችሁ እንዳለ አድርጋችሁ አስቡ። የምትወዱትን ጓደኛ ወይም አሠሪያችሁን በዚያው የድምፅ ቃና ወይም በእነዚያው ቃላት ታናግሩ ነበር? እንግዲያው የትዳር ጓደኛችሁን ከጓደኛችሁ ወይም ከአሠሪያችሁ ይበልጥ በአክብሮትና በዘዴ ልታናግሩ የሚገባው ለምን እንደሆነ አስቡ።

 

ሦስተኛው ክህሎት፦ ከአዲሱ ኃላፊነታችሁ ጋር ራሳችሁን ለማላመድ ጣሩ

ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው?

አንድ ባል መጀመሪያ ላይ የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት መንገድ ሚስቱን የሚያስከፋ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ አንዲት ሚስት ሐሳቧን በዘዴ የመግለጽ ችግር ይኖርባት ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በጣሊያን የሚኖር አንቶኒዮ የተባለ አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ቤተሰቡን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሲያደርግ እናቴን አያማክራትም ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ መጀመሪያ ላይ እኔም በቤተሰቤ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኜ ነበር።” በካናዳ የምትኖር ዴቢ የተባለች ሚስት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴን ዕቃዎቹን እንዳያዝረከርክ እነግረው ነበር። ይሁን እንጂ እንደ አለቃ ሆኜ እናገረው ስለነበር ጭራሽ እልኸኛ ሆነ።”

 

ባል ያለበትን ችግር ለመፍታት ምን ሊረዳው ይችላል?

አንዳንድ ባሎች መጽሐፍ ቅዱስ ሚስት ለባሏ እንድትገዛ የሚሰጠው ምክር፣ ልጅ ለወላጁ መታዘዝ እንዳለበት ከሚገልጸው ሐሳብ ጋር ይምታታባቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ባል ‘ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ በማለት ይገልጻል፤ ስለ ወላጅና ልጅ ግን እንዲህ ብሎ አይናገርም።  ይሖዋ፣ ሚስት የባሏ ረዳት ወይም አጋር እንደሆነች ተናግሯል።  ይሁንና ልጅ ለወላጁ ረዳት ወይም አጋር እንደሆነ አድርጎ የገለጸበት ጊዜ የለም። ታዲያ ምን ይመስልሃል? አንድ ባል ሚስቱን እንደ ልጅ አድርጎ የሚያያት ከሆነ ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት አለው ሊባል ይችላል?

 

እንዲያውም የአምላክ ቃል፣ ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን በያዘበት መንገድ ሚስትህን እንድትይዛት ያሳስብሃል። ሚስትህ (1) ወዲያውኑ ፍጹም በሆነ መንገድ እንድትገዛልህ የማትጠብቅባት ከሆነና (2) ችግሮች በሚነሱበት ጊዜም ጭምር እንደ ገዛ ሥጋህ አድርገህ የምትወዳት ከሆነ የራስነት ሥልጣንህን መቀበል ቀላል

 

ሚስት ያለባትን ችግር ለመፍታት ምን ሊረዳት ይችላል?

አምላክ ባልሽን የአንቺ ራስ እንዲሆን እንደሾመው አምነሽ ተቀበይ። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ባልሽን የምታከብሪ ከሆነ ለአምላክ አክብሮት አለሽ ማለት ነው። የባልሽን የራስነት ሥልጣን የማትቀበይ ከሆነ ግን ለባልሽ ብቻ ሳይሆን ለአምላክና እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች ያለሽን አመለካከት እያንጸባረቅሽ ነው።

A husband and wife washing dishes

ችግር ተፈጥሮ በምትወያዩበት ጊዜ በባልሽ ጠባይ ላይ ሳይሆን በችግሩ ላይ ትኩረት አድርጊ። ለምሳሌ ንግሥት አስቴር፣ ባሏ ንጉሥ አርጤክስስ ፍትሕ እንዲያስከብር ማድረግ ፈልጋ ነበር። በዚህ ጊዜ እሱን ከመንቀፍ ይልቅ ሐሳቧን በዘዴ ገልጻለች። ባሏም ሐሳቧን ተቀብሎ በኋላ ላይ ትክክለኛውን ነገር አድርጓል።  ባልሽ (1) የቤተሰብ ራስ እንዲሆን የተሰጠውን አዲስ ኃላፊነት በብቃት ማከናወን እስኪችል ድረስ ጊዜ የምትሰጪው ከሆነና (2) ስህተት በሚሠራበት ጊዜም ጭምር በአክብሮት የምትይዥው ከሆነ ለአንቺ ያለው ፍቅር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም።

 

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁ እንዲያሻሽል የምትፈልጓቸውን ነገሮች ከመቁጠር ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ልታሻሽሏቸው የሚገቡትን ነገሮች አስቡ። ባሎች፦ የራስነት ሥልጣናችሁን አላግባብ በመጠቀማችሁ ወይም ጭራሹኑ ሳትጠቀሙበት በመቅረታችሁ ሚስቶቻችሁ በሚበሳጩበት ጊዜ እንዴት ማሻሻል እንደምትችሉ ጠይቋቸውና የሚሰጧችሁን ሐሳብ በጽሑፍ አስፍሩት። ሚስቶች፦ ባሎቻችሁ አክብሮት እንዳላሳያችኋቸው በሚሰማቸው ጊዜ ልታሻሽሉት የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ጠይቋቸውና የሚሰጧችሁን ሐሳብ በማስታወሻ ላይ ጻፉት።

 

ከትዳር ጓደኛችሁ የምትጠብቁት ነገር ምክንያታዊ ይሁን

ደስተኛና ሚዛናዊ የሆነ የትዳር ጥምረት ይዞ መኖር የሚቻልበትን መንገድ መማር ብስክሌት መንዳት ከመለማመድ ጋር ይመሳሰላል። ብስክሌት በደንብ መንዳት እስክትችሉ ድረስ አልፎ አልፎ መውደቃችሁ የማይቀር ነገር ነው። በተመሳሳይም በትዳር ውስጥ ተሞክሮ እስክታካብቱ ድረስ ሊያሳፍሯችሁ የሚችሉ አንዳንድ ስህተቶችን መሥራታችሁ አይቀርም።

 

ተጫዋች ለመሆን ጥረት አድርጉ። የትዳር ጓደኛችሁ የሚያሳስበውን ነገር በቁም ነገር ተመልከቱት፤ ስህተት በምትሠሩበት ጊዜ ግን በራሳችሁ ላይ የመሳቅ ልማድ ይኑራችሁ። በመጀመሪያው ዓመት የትዳር ሕይወታችሁ፣ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ የትዳር ጓደኛችሁን ለማስደሰት ጣሩ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ግንኙነታችሁ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ይሁን። እንዲህ ስታደርጉ ትዳራችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ይሄዳል።

 

ምንጭ፡- የወጣቶች ጥያቄ